የባንክ ሰራተኞች አዲስ ደንበኛ እንዲያመጡ የሚደርስባቸው ጫና እና የስነ ልቦና በደል ሲዳሰስ
በፍቃዱ ኤርሱሞ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- አሁን አሁን አሳሳቢ እየሆነ፣ ብዙ ሰዎች ያላስተዋሉት እንዲሁም የሚዲያ ሽፋን ያልተሰጠው ነገር ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ የመጣው የባንክ ሰራተኞች በደል ነው። ይህን አስተያየቴን ለህዝብ እና ለሚመለከተው አካል አድርሱልኝ።
ወደ ጉዳዩ ስገባ፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሴክተር በርካታ ችግሮች ያሉበት እንደሆነ ይታወቃል። ከነዚህ ውስጥ የባንኮች አሁናዊ የስራ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ውስጥ ገብቷል።
በርካታ የግል ባንኮች ብድር እያበደሩ አይደለም፣ በየመንደሩ እንደ አሸን የፈላው ባንክ ሁሉም በሚባል ደረጃ የተወሰነ ተመሳሳይ አገልግሎት (ቁጠባ፣ ሀዋላ እና የውጭ ምንዛሪ) ለመስጠት በርካታ ቅርንጫፎች ከፍተው እየሰሩ ይገኛሉ። በሚገርም ሁኔታ ብድር በመቆሙ አብዛኞቹ ባንኮች ብዙ ቅርንጫፎቻቸው ኪሳራ ውስጥ ገብተዋል።
ጥቂት የማይባሉ ባንኮች ቀደም ሲል ለሰራተኞቻቸው ይሰጡ የነበረውን የቤት መግዣ እና መስሪያ ብድር ጭምር ካቆሙ ሶስት እና ከዚያ በላይ አመታት አስቆጥረዋል።
እኔ በዋናነት መጻፍ የፈለኩት እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለ ነገር የግል ባንኮች ሰራተኞች ላይ ከዲስትሪክት ጀምሮ በየቀኑ እየተደወለ አንዳንዴም ወደ ቅርንጫፎች እየመጡ ሰራተኞቹ ማድረግ የማይችሉትን ትዕዛዝ በመሥጠት ያን ካላደረጉ ደግሞ ከደሞዛቸው ጀምሮ ብዙ ቅጣቶች እንደሚጠብቃቸው እያስፈራሩ ብቻም ሳይሆን እያደረጉትም ይገኛሉ።
እንዲያመጡ ከሚጠበቅባቸው ነገሮች:
1. እንደየ ባንኩ ሁኔታ በየሳምንቱ ከ200,000 ብር እስከ 300,000 ብር የሚቆጥቡ ደንበኞችን አምጡ ወይም ያሉ ደምበኞች እንዲቆጥቡ አድርጉ፣
2. በየቀኑ ከ15-20 የሚደርሱ አዳዲስ ደንበኞችን እንዲያመጡ ይገደዳሉ ይሄም እንደየ ባንኩ ሊለያይ ይችላል።
በጣም አሳሳቢ ነገሩ ይህንን ካላደረጉ የሚደርስባቸው የአለቆቻቸው ጩኸት፣ ማስፈራሪያ አለፍ ሲልም የደመወዝ ቅጣት እና ከደረጃቸው (መደብ) ዝቅ ብለው እንዲሰሩ ማድረግ እና ከሚሰሩበትና ከሚኖሩበት አከባቢ በጣም እሩቅ ወደሆኑ አካባቢዎች የማዘዋወር እርምጃዎች ናቸው።
የኔ ጥያቄ፣ ባንኮች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው እየቀነሰ ሀብት መፍጠር ባልቻሉበት ሁኔታ፣ ሁሉም ባንኮች ከላይ የጠቀስኳቸውን ተመሳሳይ ውስን አገልግሎቶች እየሰጡ ባሉበት ሁኔታ ሰራተኞቹ ያን ያህል ገንዘብ ያለውን ነጋዴም ሆነ ባለሀብቶች ከየት እንዲያመጡ ነው?
በየሳምንቱ ሚሊዮኖች የሚቆጥብስ ባለሀብት ፈጥረናል? ምን አልባት አዲስ አበባ ላይ በዚህ ልክ ማግኘት ቢቻል እንኳን ከባንክ እና ከቅርንጫፍ ብዛት አንጻር ይሄን ማሳካት ሳይሆን ማቀድ በራሱ እብደት አይሆንም ወይ?
እሩቅ ቦታዎች የተመደቡ ሰራተኞች እየደረሰባቸው ያለው ሰቆቃ ቀላል አይደለም፣ በተለይ የቤተሰብ ኃላፊነት ያለባቸው 3 እና 4 ልጆች ያሉአቸው አቅመ ደካማ ወላጆቻቸውን የሚጦሩ ሰራተኞች ቤተሰባቸውን ለመበተን ካልሆነም በሁለት ቦታ ቤት ተከራይቶ ለአላስፈላጊ ወጭ መዳረግና በመጨረሻም ተስፋ ቆርጦ ስራ እስከመልቀቅ እየደረሱ ያሉበት ሁኔታ እያየን ነው።
ለአብነትም ቤተሰብ ያላቸው ሆነው ከሆሳዕና ወደ ሞያሌ፣ ጅንካ እና አርባ ምንጭ የተወሰዱ ሰራተኞችን በቅርበት አቃለሁ። ለከፍተኛ ማህበራዊ ችግር ተጋልጠዋል።
ሌላኛው በጣም አሳዛኙ ነገር በየቀኑ Marketing ውጡ ተብለው በየገበያውና ሰው በተሰበሰበት ቦታ ሁሉ ሱፍ ለብሶ ዘንጦ አካውንት ክፈቱ እያለ የሚለምን ባንከር ማግኘት የተለመደ ነገር ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚደርስባቸው የስነልቦና ቀውስ በአካልም፣ ፀሀይና ዝናብ ሳይሉ እየዞሩ የሚደርስባቸውን ችግር መገመት ከባድ ነው። በጣም ከባዱ ደግሞ በተለይ በአዲስ አበባ እና ሌሎች አካባቢዎችም ጭምር የባንክ ሰራተኞች የተለያዩ የንግድ ቦታዎች እና ሆቴሎች እንዳይገቡ መለጠፍና በጥበቃ ሰራተኞቻቸው መከልከል እየተለመደ መጥቷል።
ይህም ብቻ አይደለም ምን አልባት እናንተም ገጥሟችሁ ይሆናል በየመንገዱ እያስቆሙ መንገደኞች እያማረሩ ማየትም የተለመደ ነገር ነው።
ስለዚህ ሴክተሩ የተለየ የመንግስትን ትኩረት የሚሻ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ለዚህ ችግር መፍትሔ እንዲያፈላልግ አድርሱልኝ።
መረጃን ከመሠረት!




ይሄ ጉዳይ ከተነሳ ተጨማሪ ምርመራና ዘገባ ያስፈልገዋል ይሄ ብቻ አይደለም ። እኔ እምሰራበት ባንክ ለ ድስትሪክትና ለ ዋናው መስሪያቤት ከፍተኛ ኃላፊዎች እስከ ብር 20,000,000.(ሀያ ሚሊዮን) የሚደርስ አድቫንስ ተፈቅዶላቸው አድስ አበባ ላይ ቤት ያልገዛ ችፍ ዳይሬክተርም ሆነ የድስትሪክት ኃላፊ የለም። ከዚህ በተጨማሪም አስመጪና ላኪ እስከመሆን የደረሱ አሉ በሽንኩርትና መሰል የግብርና ዘርፎችም ኢንቨስት እስከማድረግ የደረሱ አሉ። ይህ ሁሉ እሚሆነው የቅርንጫፍ ሰራተኞች በሚሰበስቡት የደንበኞች ተቀማጭ ገንዘብ ነው። በዛ ላይ የቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች በስራቸው ያለን ሰራተኛ ስም ማጉደፍም ሆነ ማሳመር ይችላሉ። የቅርንጫፍ ስራ አስኪያጁ ያልተመቸውን ወይም በግሉ እሚጠላውን ሰራተኛ በ 1 ደብዳቤ ብቻ ለድስትሪክቱ በመላክ ማስባረር ሁሉ ይችላል። ይህ ሁሉ እሚሆነው አሁን ባለሁበት ባንክ በተለይም ደግሞ ደሴ ድስትሪክት ነው። ሌሎችም ተጨማሪ ጉዳዮች አሉ email አደርጋለሁ።
እኔን ከጎንደር ወደ አይራ ጎሊሶ ሲያዛውሩኝ፣፣ስራ ለመልቀቅ ተገደድኩ ፣ ያለብኝን የባንክ እዳ ለመዝጋት ቤቴን ሽጭ ኪራይ ላይ ነኝ ከ 3 ልጆቼ ጋር ።