'ፊንቴክ ኢንቨስትመንት' ከመኪና ገዢ ደንበኞቹ በርካታ የተታለናል አቤቱታ ቀረበበት
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ በሀገራችን ከፍተኛ የሚድያ ሽፋን ካገኙ እና በርካታ ታዋቂ አርቲስቶች እና ግለሰቦች ከተሳተፉበት ክንውን አንዱ የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ናቸው።
ተቋሙ በጋዜጣዊ መግለጫዎቹ መኪኖችን ለማስረከብ ከጅቡቲ ወደ ገላን እና ቃልቲ ለማጓጓዝ ዝግጅት መጠናቀቁን ቢገልፅም ደንበኞች ግን ጉዳዩ ሌላ እንደሆነ በመናገር ለሚድያችን የ 'ተጭበርብረናል' እና 'ተጉላላን' አቤቱታ አቅርበዋል።
እነዚህ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደንበኞች እንደሚሉት የመኪና አስመጪው ከ450 በላይ ከሆነ ሰው ከእያንዳንዱ 1.3 ሚልዮን ብር (በአጠቃላይ 600 ሚልዮን ብር ገደማ) ከተቀበለ በኋላ እያንገላታቸው ይገኛል።
ይህ ድርጅት የBYD ሲገል ሞዴል የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በግማሽ ዋጋ ቅድመ ክፍያ ማለትም በ950,000 ብር በ3 ወር ውስጥ አምጥቼ ካስረከብኩ በኋላ ቀሪውን ክፍያ በአምስት ዓመት ያለወለድ በየወሩ መክፈል እንደሚቻል መግለፁም ሚድያችን የተመለከታቸው የውል ሰነዶች እና በተለያዩ ሚድያዎች ያስነገራቸው ማስታወቂያዎች ያሳያሉ።
"ከጥቅምት 2017 ዓ.ም ጀምሮ 192 ለሚጠጉ ተመዝጋቢዎች ብቻ መኪናውን ሠጥቷል። ሆኖም ግን ሌሎቻችን ከተመዘገብንና የሚጠበቅብንን ክፍያ ከከፈልን ከዘጠኝ ወር በላይ ያለፈን ቢሆንም መኪናችንን ሊያስረክቡን አልፈለጉም ወይም አልቻሉም" የሚሉት ደንበኞች በዚህም ምክንያት መኪናችንን ስጡን ብለው ተሰብስበው ቦሌ ሜጋ ሱር ኮንስትራክሽን አጠገብ ከሚገኘው ቢሯቸው ድረስ በተደጋጋሚ ሄደው ሲጠይቁ በተናጠል እንጂ በጋራ አናናግርም በማለት ሣያናግሩ ለረዥም ግዜ መቅረታቸው ታውቋል።
"በቅርቡ ተመልሰን ሄደን ካላናገሩን ከቢሮ እንደማንወጣ ሲረዱ እና ግፊቱ ሲበዛባቸው ቀጠሮ ሠጥተውን በሌላ ቀን አናግረውናል። በቀጠሮአችን ቀን ቀርበን በእኛ በኩል የሚጠበቅብንን ግዴታ በውላችን መሠረት የተወጣን ስለሆነ እና መኪናችን መረከብ የሚገባን ቀን ያለፈ በመሆኑ ስጡን ብለን የጠየቅናቸው ሲሆን ለጠየቅናቸው ጥያቄ በቂ መልስ መስጠት አልቻሉም፣ ይልቁንም አትሠባሠቡ አደጋ ያጋጥማችዋል በማለት አስፈራርተውናል" ብለው ተናግረዋል።
እነዚህ ደንበኞች ድርጅቱ እየሠራቸው ያሉ የማጭበርበሮች ስራዎች ናቸው ያሏቸውን ሲገልፁ:
- "ድርጅቱ ማጭበርበሩ የሚጀምረው ከማስታወቂያው ሲሆን ይሄም ግማሽ ክፍያው 950,000 ብር ብቻ ነው እያሉ ቢያስተዋውቁም የታርጋና የኢንሹራንስ 130,000 ብር እና የተጨማሪ እሴት ታስክ 285,000 ሲጨመር የመኪናው ጠቅላላ ዋጋ ከ1,350,000 ብር በላይ ነው፣ ለቫት ክፍያው ደረሰኝ አይሰጡም"
- "ውል ስንፈራረም ውሉ ውስጥ በተካተተ አንቀጽ ላይ መኪናውን በውላችን መሠረት ሳያቀርቡ ቢቀሩ የመልካም አፈፃፀም ዋስትና ከፀሐይ ኢንሹራስ አ/ማ በእያንዳችን ስም ዋስትና ስለሚገባልን የከፈልነውን የብር መጠን 10% ተጨምሮ እንደሚሠጠን ተዋዉለን የነበረ ቢሆንም ይሄው 9 ወር ሙሉ ኢንሹራንሡም የለም፣ የመኪናውም ነገር የውሀ ሽታ ሆነ። ፀሐይ ኢንሹራስ አ/ማ ሄደን ስንጠይቅ የፋይናንስ አፈፃፀማቸውን አይተን ሪስክ ስላለው ውላቸን አቋርጠናል በማለት አብራርተው ገልጸውልናል።"
- ግንቦት 9/2017 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ እስከ ውል ቁጥር ከ193-650 ድረስ ያላችሁ መኪናችሁ መጥቷል፣ በሣምንት ጊዜ ውስጥ እናስረክባችኃለን በማለት ባሳወቁን መሠረት መጀመሪያ ከከፈልነው ከ950,000 ብር በተጨማሪ የታርጋና የኢንሹራንስ 130,000 ብር የተጨማሪ እሴት ታስክ 285,000 በአጠቃላይ እያንዳንዳችን 415,000 ብር እያንዳንዳችንን ያስከፈሉን ቢሆንም ምንም የገባ ሆነ የተረከብነው መኪና ሳይኖር 3 ወር ሞላን።"
የድርጅቱ ባለቤት ማንነትን በተመለከተ ለማወቅ ባደረግነው ጥረት የሚታወቁ ባለቤቶቹ ሁለት ሲሆኑ አንደኛ አቶ ግርማይ ገ/ማርያም የተባሉ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም በደቡብ አፍሪካ የዓለም ዋንጫ ሠዎችን እልካለሁ ብለው ገንዘቡን ይዘው ጠፍተው በኢንተርፖል አማካኝነት ከጀርመን ሀገር ተይዘው የመጡ ግለሠብ መሆናቸው ታውቋል።
ሁለተኛው አቶ ዳንኤል ዮሐንስ የተባሉት ደግሞ ሄሎ ታክሲ በሚል ስም ከ5,000 በላይ ሠዎች ላይ ገንዘብ ሠብስቦ ብዙ ሠዎችን ያጉላላ ግለሰብ መሆኑ ታውቋል።
"እኛ እንዲህ አይነት ችግር ያለባቸው መሆኑን ብናውቅ አንመዘገብም ነበር። እስካሁን የሠጡት መኪና 192 ሆኖ እያለ በተለያየ ሚዲያ እየቀረቡ ከዚህ ቁጥር በላይ አስመጥተው እንዳስረከቡ ይገልፃሉ። አንድ ጊዜ 250 ሌላ ጊዜ 500 መኪኖችን ሠጥተናል በማለት ያወናብዳሉ። ነገር ግን ወረፋ ይዘን ቁጥር ተሠጥቶን ከምንጠባበቅ ሰዎች ውስጥ እስካሁን 192 ብቻ መኪኖች ማስረከባቸውን ራሣቸው አምነው ለኛ ነግረውናል" በማለት ደንበኞቹ ተናግረዋል።
"በቃ ገንዘባችንን መልሡልን እና እንውጣ ስንላቸው ደግሞ ወድያው መመለስ አይፈልጉም። አዲስ ሠው ሲመዘገብ ነው የምንመልስላችሁ እንጂ ገንዘብ የለም በማለት የራሣችንን ገንዘብ ለመውሠድ ከአንድ ወር በላይ እያመላልሱ እያጉላሉን ይገኛሉ። ይህን ያህል ጊዜ አጉላልተውም ሲመልሡም መጀመሪያ የከፈልነውን ገንዘብ ብቻ ይመልሣሉ፣ ውሉ ላይ የተቀመጠውን ቅጣት እንኳን አይሠጡም" በማለት አንድ ደንበኛ ጉዳዩን አብራርተዋል።
በዚህ ድርጅት ላይ አምባሣደር ተብለው የተሠየሙት ብዙ አርቲስቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች ናቸው።
ሚድያችን እንደተመለከተው መንሱር ጀማል፣ ሠራዊት ፍቅሬ፣ ሠለሞን ቦጋለ፣ ይገረም ደጀኔ እና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች በዚህ መልኩ ድርጅቱን ለህዝብ እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
"ታዋቂ ሰዎቹ ስንደውልላቸው ስልክ አያነሡም፣ መልሶ ለመደወልም ፈቃደኛ አይደሉም። አንዱ የብራንድ አምባሳደር ስልክ አንስቶ እኔ ምንም ማድረግ አልችልም የእኛን የአምባሣደሮችን መኪናም በጭቅጭቅ ነው የሠጡን ማለት ገልፃልናል" የሚሉት ተበዳዮች ናቸው።
"በዚህ ምክንያት የብዙ ሠው ሕይወት እተበላሸ ይገኛል። የጣት ቀለበቱን ሽጦ የከፈለ አለ፣ የእናቱን ወርቅ የሸጠ አለ። ራይድ የሚሰራበትን እና ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበትን ቪትስ ሸጦ የከፈለ አለ። በአጠቃላይ በዚህ ኑሮ ላይ ያለችንን ትንሽ ነገር አስረክበን የከበደው እና የተመሠቃቀለበት ህይወት እየመራን እንገኛለን። ከጥቅምት 2017 ጀምሮ 3 ሥራ አሰኪያጆችን ቀያይረዋል። በተለያዩ ሚድያዎች የሚገኙ ጋዜጠኛችን በተለይ የአብርሀም ግዛውና እሱ የሚዘውራቸውን ጋዜጠኞችንና ሌሎች በገንዘብ በመያዝ መልካም ነገር ብቻ እንዲናገሩ እያደረጉ ይገኛሉ" ብለው የአበል ክፍያ ለሚድያዎች የተከፈለበትን ዶክመንት ለሚድያችን ሰጥተዋል።
ጉዳዩን ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ማለትም ለአዲስ አበባ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ፣ ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ቢሮ፣ የአስመጭነት ፈቃድ ለሚሠጡ ተቋማት እና ለሌሎች በዚህ ዘርፍ ለሚሠሩ መሥሪያ ቤቶች በዝርዝር ያመለከቱ ቢሆንም ምንም ጠብ የሚል መልስ እንዳልተሰጣቸው ታውቋል።
ፊንቴክ ኢንቨስትመንት 200 ቢዋይዲ ሲገልና 58 ኢቱ በድምሩ 258 የኤለክትሪክ መኪኖችን ለማሰረከብ ከጅቡቲ ወደ ገላንና ቃልቲ ለማጓጓዝ ዝግጅት መጠናቀቁን የድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች ከቀናት በፊት በስካይላት ገልፀው ነበር።
ሚድያችን ድርጅቱን በዚህ ዙርያ ለማናገር ቢሞክርም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
-መሠረት ሚድያ-







Ke ambassador dina mufti gon yetekemetew eye glass yaregew nw balebetu daniel yebalal 2012 lay hello taxi belo temesasay behone huneta siyachbereber nber I'm a victim of hello taxi
ኤሊያስ የምትሰራው ስራ በጣም በጣም ትልቅ እና ሕዝብን ሊያነቃ እንዱሑም መንግስት