ሽሮ ሜዳ አካባቢ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ተገድቧል፣ በርካታ የፀጥታ አካላት ይታያሉ፣ የተከሰተው ምንድን ነው?
(መሠረት ሚድያ)- በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ "ሽሮ ሜዳ" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተገኝ ባልቻ (ኦሮሮ) የተባለ ወጣት በአንድ የፖሊስ አባል በትናንትናው ዕለት ተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ማለፉን መሠረት ሚዲያ ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከቅርብ ወዳጆቹ ሰምቷል።
ሟች ተገኝ ባልቻ ቀደም ሲል በሽሮ ሜዳ አካባቢ ስኬታማ የነጠላ ነጋዴ እንደነበርና ራሱንና ቤተሰቡን ከመደገፍ አልፎ ለጓደኞቹና ለተቸገሩት ደራሽ እንደነበር ይነገራል። ይሁን እንጂ በልማት ምክንያት የንግድ ሱቁ በመፍረሱና ንብረቱ በመጥፋቱ ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራና ለስነ-ልቦና ቀውስ መዳረጉን ግለሰቡን የሚያውቁት ለሚድያችን ዛሬ ተናግረዋል።
ይህንን ተከትሎ በገባው ከፍተኛ ቁጭትና ንዴት ውስጥ ሆኖ፣ ከአንድ ወር በፊት "ሞተር ተራ" ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከአንድ የፖሊስ አባል ጋር በፈጠረው አለመግባባት ለቀናት ታስሮ እንደነበር ታውቋል።
የእስር ቤት ስቃይ እና የአባት ሞት
ወጣቱ በቁጥጥር ስር ውሎ በነበረበት ወቅት አባቱ ከዚህ አለም በሞት የተለዩ ሲሆን፣ ተገኝ የአባቱን የቀብር ስነስርዓት እንኳን ሳይታደም በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ ሀዘኑን እንዲያሳልፍ መገደዱ ታውቋል። ከሳምንታት በፊት በዋስትና ተፈቶ የአባቱን መቃብር በመጎብኘት ሀዘኑን እየተወጣ ባለበት ወቅት ነው ድንገተኛው የግድያ ጥቃት የደረሰበት።
የግድያው ሁኔታ
"ትናንት ሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ተገኝ ከጓደኞቹ ጋር በለመደበት ስፍራ ተቀምጦ እያለ በፓትሮል መኪና የመጡ የጸጥታ አካላት "ለጥያቄ ትፈለጋለህ" በሚል ወደ ሽሮ ሜዳ (02 ጣቢያ) ወሰዱት" የሚሉት አንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ቀደም ሲል ከሟች ጋር ፀብ ነበረው የተባለው የፖሊስ አባል በጣቢያው በር ላይ በነበረበት ወቅት ሽጉጡን አውጥቶ አራት ጊዜ በመተኮስ ወጣቱን ህይወቱን እንዲያልፍ ካደረገ በኋላ ከአካባቢው መሰወሩ ተነግሯል።
"ሽሮሜዳ ትላንት አንድ የጋሞ ተወላጅ በፖሊሶች ተገድሎ በመሞቱ አካባቢው ውጥረት አለ፣ መንቀሳቀስ አልቻልንም።
መኪና ማለፍ ተከልክሏል፣ ሰፈሩ በሙሉ በፖሊስ ተከቧል፣ ለቀስተኛው ግድያውን ሲቃወሙ እየተሰሙ ነው" የሚሉት ሌላኛው ስሜ አይጠቀስ ያሉ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።
"ፍትህ እንፈልጋለን"
የአካባቢው ነዋሪዎችና የሟች ወዳጆች በድርጊቱ እጅግ ማዘናቸውንና ድርጊቱን የፈጸመው የህግ አስከባሪ በህግ እንዲጠየቅ ድምፃቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
"የሰው ልጅ ነፍስ ዋጋ እያጣ ነው" የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ መንግስት በህግ ስም የሚፈጸሙ መሰል ጥቃቶችን እንዲያስቆም ጠይቀዋል።
መሠረት ሚዲያ ጉዳዩን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የፖሊስ አካላት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ይገኛል።
| መሠረት ሚድያ |



ያሳምማል
ብልጽግና ይህ ነው።