መምህራን ዛሬ በመላው አዲስ አበባ በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ምን ጥያቄዎችን አነሱ?
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎች በመላው ሀገሪቱ የመብት እና የዳቦ ጥያቄ በማንሳት በመላው ኢትዮጵያ በቅርብ አመታት ታይቶ የማይታወቅ የተናበበ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፣ ለመንግስት የሰጡት የ30 ቀን ቀነ ገደብም አብቅቶ የከፊል አድማ እያረጉ ይገኛሉ።
ይህ የጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ እንደ መምህራን፣ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች ወዘተ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እንዳይተላለፍ አንዳንድ ጥረቶች እየተደረጉ እንዳሉ ሚድያችን ያደረጋቸው ዳሰሳዎች ያሳያሉ።
ከእነዚህም አንዱ በመምህራን ላይ ያተኮረ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በዛሬው እለት 'የማይቀርበት እና አስቸኳይ' ያለውን ስብሰባ ከመምህራን ጋር ሲያደርግ ውሏል።
እነዚህ ስብሰባዎች ላይ ስልክም ሆነ ምንም አይነት የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎችን ይዞ መግባት እንደማይቻል በመንግስት ሀላፊዎች ቢገለፅም መሠረት ሚድያ አንዳንድ የድምፅ ቅጂዎች እና የፅሁፍ መልእክቶች ደርሰውታል።
የውይይቱ ርዕስ ምን ነበር?
ስብሰባዎቹን ከተሳተፉ መምህራን ያሰባሰብናቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የውይይቱ ርዕስ "ትውልድ በመምህር ይቀረጻል፣ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል" የሚል ነበር።
ለምሳሌ በአንድ የስብሰባ አዳራሽ የተገኙት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሀላፊው ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ባቀረቡት ሰነድ ላይ ብልጽግና በትምህርት ዘርፍ የተሳኩ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉት ጠቅሰው እነዚህም የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት፣ የዜጎችን መብት ማረጋገጥ፣ የፌደራላዊ ስርዓትን ማጠናከር እና የፖለቲካ አካታችነት መፍጠር ናቸው ብለዋል።
ዶ/ር ዘላለም ያጋጠሙ ችግሮችን ሲያነሱም የፖለቲካ ጽንፈኝነት፣ ከአስተሳሰብ ትርክት ይልቅ በነጠላ ትርክት ላይ ማተኮር፣ የነፃነት መብትን ያለአግባብ መጠቀም የሚሉ እንደነበሩ መምህራን ለሚድያችን ተናግረዋል።
መምህራን በበኩላቸው የደሞዝ ማነስ፣ የቤት ኪራይ ውድነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የአስተዳደር ችግር ወይም ቢሮክራሲ፣ የግብር መብዛት እና ሌሎች ጥያቄዎችን ማንሳታቸው ታውቋል።
በሌላ አንድ ስብሰባ ላይ ደግሞ ማስፈራርያ አዘል መልዕክቶች ከመንግስት አካላት ሲተላለፍ እንደነበር፣ መንግስትን ለመገዳደር ለሚሹ አካላት መምህራን መጠቀሚያ መሆን እንደሌለባቸው እና በተደራጀ ተቃውሞ ላይ ተሳትፈው የሚገኙ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው እንደተነገራቸው ለሚድያችን ገልፀዋል።
ፎቶ ፋይል
መረጃን ከመሠረት!




''ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም! ''አሉ።
ከመገረምና መታዘብ ውጭ ምን ይባላል ወገን?