(መሠረት ሚድያ)- ሰላም፣ ሰላም። ለነገሩ ሰላም በሌለበት ሁኔታ “ሰላም” ብሎ መጀመር ራስን ማታለል፣ ሕዝብን መሸንገልና መንግሥትንም እውነታውን በትክክል እንዳያይ ማድረግ ነው።
እዚህ ስለ ሰላም ስናገር ጦርነትንና ግጭትን ብቻ አልጠቅስም። የውስጥ ሰላምን፣ የሕሊና እረፍትን፣ የአእምሮ መረጋጋትንና በነገው ቀን ላይ ያለንን ተስፋም ጭምር ነው የማወራው።
የዓለም ጤና ድርጅት የጤና ትርጓሜም ይህንኑ ያስታውሰናል፤ ጤና ማለት ከበሽታ ነፃ መሆን ብቻ ሳይሆን አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና ማኅበራዊ ደኅንነት መኖርንም ያካትታል። እንግዲህ በዚህ መለኪያ መሠረት በአገራችን ስንቶቻችን ጤነኞች ነን? “እኔ ጤነኛ ነኝ” ብሎ በእርግጠኝነት የሚመልስ ሰው ስንት ይሆን? የሰው ልጅ በውጭ በጤና ያለ ቢመስልም፣ በውስጡ በጭንቀት፣ በፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ እየተሰቃየ ከሆነ በእውነት ጤነኛ ነውን?
ይህንን ጥያቄ የማነሳው በቅርቡ ተደጋጋሚ የሰላም መታወክና የኑሮ ጫና በሕይወቴ ላይ ተፅዕኖ ስላሳደሩ ነው። እኔና ባለቤቴ ከ15 ዓመት በፊት የመጀመሪያ ዲግሪያችንን በጥሩ ውጤት አግኝተናል። ባለቤቴ የግቢውን ዋንጫ ያነሳች ሲሆን፣ እኔም የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኜ ነበር። ከ10 ዓመት በፊት ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪያችንን አግኝተን፣ ሁለታችንም በፌዴራል መንግሥት ተቋም ውስጥ በመሥራት አገራችንን እያገለገልን የምንገኝ ከፍተኛ ባለሙያዎች ነን።
ይሁን እንጂ፣ ይህን ያህል ዓመታት ተምረን፣ ሠርተንና አገራችንን አገልግለን እንኳን፣ የራሳችን የሆነ መኖሪያ ቤት የለንም። የልጆቻችንን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላትም እየተቸገርን ነው። እስከ ዛሬ ድረስ ከመደበኛ ሥራችን በተጨማሪ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን የኑሮ ክፍተታችንን ለመሙላት ሞክረናል። ግን የኑሮ ውድነቱ ከገቢያችን አቅም በላይ እየሆነ መጥቷል፤ ወገባችንን አጎብጦ መቋቋም የማንችልበት ደረጃ ላይ እያደረሰን ነው።
የችግሩን ክብደት ለመረዳት ቀላል ምሳሌ እንውሰድ። በአዲስ አበባ ዳርቻ በሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ያልተጠናቀቁ ባለ አንድ መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤቶች እንኳን በወር ከ30,000 እስከ 35,000 ብር እየተከራዩ ነው። የመብራት ወጪም በወር ቢያንስ 2,000 ብር እንደሚደርስ ይነገራል፤ ይህም በእጥፍና በሦስት እጥፍ ሊጨምር እንደሚችል የሚነገር ሲሆን፣ የውሃ፣ የምግብ፣ የትምህርት፣ የትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎችንም መጨመር አለብን። ከዚያ በኋላ የመንግሥት ሠራተኛን ደመወዝ አስቡ። ገቢና ወጪ በዚህ መጠን ሲራራቁ፣ ሰው እንዴት የተረጋጋ ሕይወት ሊኖር ይችላል?
አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ይህን ሁሉ ወጪ እየተሸከመ፣ በተጨማሪም የነገው ሁኔታ ምን እንደሚሆን መተንበይ በማይቻልበት የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ምን ያህል ሊቋቋም ይችላል? ሰላሙን ሲያጣ፣ ጤናው ሲታወክ፣ የሥራ ተነሳሽነቱና የቤተሰቡ ደኅንነትስ ምን ይሆናሉ?
ይህ ሰው ነገን በተሻለ ሁኔታ ለመኖር፣ አገሩን ለማገልገልና ቤተሰቡን ለመደገፍ በማሰብ ከ20 ዓመት በላይ ዕድሜውን በትምህርት ያሳለፈ ነው። አሁን ግን ሕይወት የተገላቢጦሽ ሆናበት፣ ምኞቱ ሲመክንና ተስፋው ሲሟጠጥ፣ ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለልጆቹ ምግብ፣ ልብስና የወደፊት ሕይወት ይጨነቃል። ገቢው ከወጪው ጋር ሳይጣጣም ሲቀር፣ ነገ ምን እንደሚፈጠር ሳያውቅ፣ ብዙ ሌሊቶችን በሐሳብና በጭንቀት ያሳልፋል። ይህ ጭንቀት የግለሰቡ ብቻ ችግር አይደለም፤ የቤተሰቡን፣ የሥራ ቦታውንና በሰፊውም የማኅበረሰቡን ደኅንነት የሚነካ ጉዳይ ነው።
ስለዚህ መንግሥት ሆይ፣ የአንተም ሆነ የማኅበረሰቡ አገልጋይ የሆነውን የመንግሥት ሠራተኛ ተመልከት፤ ሁኔታውን አጢን። የሚያገኘው ደመወዝ ከዕለት ተዕለት የኑሮ ወጪ ጋር ምን ያህል እንደሚመጣጠን በተጨባጭ መርምር። ቢያንስ ከሥራ ውሎ የሚያርፍበት፣ ለቀጣዩ ቀን የሚያቅድበትና የሚዘጋጅበት ተመጣጣኝ የኪራይ ቤት እንኳን እንዲያገኝ የሚያስችሉ ዘላቂ መፍትሔዎችን አመቻች። ይህ ለሠራተኛው የሚደረግ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን፣ ለሕዝብ አገልግሎት ጥራትና ለአገር ልማት የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነው።
ሠራተኛው ከከባድ የኑሮ ጭንቀት ተላቆ በአእምሮ ሰላም ሲሠራ፣ ሥራውን በተሻለ ትኩረትና ኃላፊነት ይወጣል። ቤተሰቡም የተሻለ ደኅንነት ያገኛል፤ ሕዝቡም የተሻለ አገልግሎት ይቀበላል። የሕዝብ ቅሬታ እንዲቀንስና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የሚያግዙ ሁኔታዎችም ይፈጠራሉ።
በመጨረሻ፣ ሰላም ማለት ጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም። ሰላም ማለት ሰው በአእምሮ ተረጋግቶ፣ በክብር ኖሮ፣ ለራሱና ለቤተሰቡ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ሲችል ነው። ስለዚህ “ሰላም አለ” ከማለታችን በፊት፣ ሰዎች በልባቸው ሰላም አግኝተዋልን? በኑሯቸው ተረጋግተዋልን? ለነገ ተስፋ አላቸውን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን።
እውነተኛ ሰላም የሚጀምረው የሰውን ሕይወት፣ ክብርና ደኅንነት ከልብ ማስቀደም ስንችል ነው።
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
| መሠረት ሚድያ |



አባ ገ/ሃና አልፈው ሲሄዱ አንድ ትልቅ የጤፍ ክምር ያዩና የማነው ብለው ሲጠይቁ
የአያ እንቶኔ ይሏቸዋል።
"ክምሩ የአምና/last year/ ካልሆነ ግሩም ነው" አሉ ይባላል!
የአምና ማለት ባለቤቱ ተቸግሮ የክምሩን ያክል ተበድሮ በልቱዋል! ምርቱ ሲወቃ ሙሉ በሙሉ እዳውን ለመክፈል ነው የሚውለው! የእሱ አይደለም ማለት ነው።
ኢትዮጵያን የአምና አድርገዋታል! ተሸጣ ተጠጥቶባታል!
ኮሚክ ነች😂
አስተያቱ የጸሃፊውን ብቻ ያንጸባርቃል
ጸሃፊው ማነው? ስም የለም
እናማ ጸሃፊው እሱ እራሱ ነው