የተካረረው የአማራ ባንክ ሰራተኞች እና የባንኩ አመራሮች ውዝግብ
(መሠረት ሚድያ)- በቅርብ አመታት ወደ ስራ ከገቡ ባንኮች አንዱ የሆነው አማራ ባንክ ከሰራተኞቹ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ እንዳለ የተለያዩ ጥቆማዎች ያሳያሉ። በርካታ የባንኩ ሰራተኞችም ለመሠረት ሚድያ እየላኩት ያለው መረጃ ይህንኑ ያሳያል።
ጉዳዩ በዋነኝነት 'ቃል የተገባልን የደመወዝ ጭማሪ አልተፈፀመልንም' የሚል ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም ሰራተኞቹ በባንኩ አመራሮች ላይ ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
"እኛ የአማራ ባንክ ሰራተኞች ባንኩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በደስታና በከፍተኛ ፍላጎት ባንኩን ተቀላቅለን እየሰራን እንገኛለን። አብዛኛው ሰራተኛ ከሌሎች ባንኮች ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅሞችን በመቀነስ እንዲሁም የተሻለ የስራ ቦታ ትቶ የመጣ ነው" የሚሉት አንዱ የባንኩ ሰራተኛ ናቸው።
"ነገር ግን ባንኩ ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጭማሪ ያላደረገ በመሆኑ ኑሮን መቋቋም አቅቶናል። በተለይ ከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ባንኩ ለሠራተኛው ምንም አይነት ደንታ የሌላቸው እና ባንኩንም ወደፊት እንዳይራመድ እያደረጉት ነው" በማለት ተናግረዋል።
አክለውም "ሁልጊዜ የሰራተኛ ደመውዝ መዋቅር ተሰርቶ አልቋል እየተባልን ሶስት ዓመት አለፈ፣ ለዚህ ችግር መባባስ አንዱ የከፍተኛ አመራሩ በየጊዜው መቀያየር አንዱ ነው" በማለት ያስረዳሉ።
ሌላ የባንኩ ሰራተኛ ደግሞ "ከሞቀ ቤታችን ለምሳሌ ከንግድ ባንክ፣ ከአቢሲኒያ ባንክ፣ ከአዋሽ ባንክ እና ከተለያዩ ግዙፍ ባንኮች ወጥተን አማራ ባንክ የገባን ሲኒየር የባንክ ሰራተኞች ይሄው ፍዳችንን እየበላን ነው" በማለት ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።
"ከሚፈጸምብን ግፎች በትንሹ አንደኛ ባንኩ ገና ሲከፈት ከዛሬ 3 አመት ከ4 ወር በፊት ጀምሮ ከንግድ ባንክ በ2 አመት የስራ ልምድ የገባን ሰራተኞች አማራ ባንክ ስንቀጠር 15 ሺህ ነበር ደሞዛችን፣ ዛሬም ይሄው ከ3 አመት በኋላም ደሞዛችን ያው ነው" ያሉ ሲሆን የኑሮ ውድነቱ ባለፉት ሶስት አመታት በእጅጉ የጨመረ ቢሆንም እስካሁን የደሞዝ ጭማሪም ሆነ ሌላው ቀርቶ የሰራተኛ ብድር እንደሌለ ያነሳሉ።
"ቦነስ የሚባል ነገር ጭራሽ የለም፣ እኛም አንጠብቅም። በቃ ፍዳችንን በላን፣ ባንኩ በ3 አመት ውስጥ ይሄው 3 ፕሬዝደንት ቢቀያይርም ምንም ጠብ የሚል ነገር የለም" ብለዋል።
እኚህ ሰራተኛ በሁለተኝነት የሚያነሱት ከ 2 ወር በፊት በሚዲያ አማራ ባንክ ደሞዝ ሊጨምር ነው ተብሎ ስለተነገረው ጉዳይ ነው።
"አዲስ አበባ ላይ የቤት አከራዮቻችን ደሞዝ ተጨምሮላችኋል፣ እኛም የቤት ኪራይ ጨምረናል ብለው 9 ሺ ብር አስገብተውብናል። ይባስ ብለው አሁን ጭራሽ ስብሰባ ላይ ጭማሪ የሚባል ነገር የለም፣ ባንኩ አትርፏል ቢባልም እስከዛሬ [በጦርነት ቀጠናዎች] የተዘረፈውን ገንዘብ መተኪያ ነው የሚደረገው ተብሏል" ይላሉ።
አንድ ሌላ ሰራተኛ ደግሞ "ጸጥ ለጥ ብለህ ስራ፣ ያለበለዚያ ለሚዲያ እተነፍሳለሁ ካልክ ትባረራታለህ እያሉ ሰራተኛውን እያስፈራሩ ነው። ንግድ ባንክ ሆነን የገዛነውን ሱፍ ለብሰን መቀየሪያም መግዛት ስላልቻልን እላያችን ላይ ማለቁ ነው" ብለዋል።
"ሶሻል ሚዲያ ላይ ኮመንት አርገሃል ተብዬ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለዛዉም ከፍተኛ ከሚባሉ የሰዉ ሀይል አስተዳደር ሀላፊ ከብዙ ዛቻ ጋር ነዉ የተሰጠኝ፣ በጣም አጣብቂኝ ላይ ነን። የደሞዝ ጭማሪ ወሬው ለሚዲያ ሽፋን ከተነገረ በኋላ ስንጠይቅ መልስ የለም። ይሄን ስፅፍላችሁም በታላቅ ፍርሃት ዉስጥ ሆኜ ነዉ" በማለት ተናገረዋል።
መሠረት ሚድያ እነዚህን የሰራተኞች ጥያቄ በመያዝ የአማራ ባንክ ፕሬዝደንት የሆኑትን ዶ/ር ዮሀንስ አያሌውን አናጋግሯል።
"እውነት ነው፣ አዲሱን ድርጅታዊ አወቃቀር ተከትሎ ሀምሌ ወር ላይ አዲስ የደሞዝ እርከን ተፈቅዷል፣ ይህም ሰራተኞች እንዲያውቁት ተደርጓል" በማለት ዶ/ር ዮሀንስ ያስረዳሉ።
"ነገር ግን ይህን አዲስ የደሞዝ እርከን ተግባራዊ ለማድረግ አዲስ የሰራተኞች የስራ መደብ ድልድል (redeployment) ማድረግ ይጠበቅብናል። ድልድል ሲሰራ ደግሞ ግዜ ይወስዳል፣ አሁን እሱን እየሰራን እንገኛለን" በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።
ይህ ድልድል የሰራተኛ ቅነሳ ያስከትል እንደሆነ በሚድያችን የተጠየቁት ዶ/ር ዮሀንስ "የሚቀነስ ሰራተኛ አይኖርም፣ በስራ ዘመኔ ሁሉ ስቃወመው የኖርኩት የሰራተኛ ቅነሳ ጉዳይ ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ይሁንና የሰራተኛ ድልድሉ መቼ ያልቃል ለሚለው ጥያቄ "መገመት ያስቸግራል" የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
-መሠረት ሚድያ-





