የመረጃ ነፃነትን ለማረጋገጥ የተረቀቀው አዋጅ የግል ሚድያዎችን እና የተጋባዥ እንግዶችን ነፃነት በተጋፋ መልኩ በዝግ ውይይት ተደረገበት
(መሠረት ሚድያ)- የመንግስትን አሰራር ግልጽነት ለማረጋገጥ እና የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት በተግባር ለመተርጎም በሚል የተዘጋጀው አዲሱ "የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ" ራሱ መረጃን በከለከለና የፕሬስ ነፃነትን በገደበ ሁኔታ ውይይት እንደተደረገበት ታወቀ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "የህዝብ ይፋዊ ውይይት" በሚል በጠራው በዚህ መድረክ ከተመረጡና አስቀድመው ከተፈቀደላቸው ግለሰቦች ውጪ ሌሎች እንዳይሳተፉ የተከለከሉ ሲሆን የተገኙት ሚዲያዎችም ዘገባ እንዳይሰሩ ታግደዋል።
ከግል ሚድያዎች ኢቢኤስ ብቻ ተጋብዞ እንደነበር ታውቋል።
"በምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዘጋጅነት ዛሬ ግንቦት 5 ቀን 2018 ዓ.ም. የተካሄደው የውይይት መድረክ ይፋዊ የህዝብ ውይይት የሚል ስያሜ ቢሰጠውም አፈጻጸሙ ግን እጅግ የተገደበ እና ከህዝብ እይታ የራቀ ነበር" ያሉት አንድ በስብሰባው ተሳታፊ የነበሩ ምንጫችን ናቸው።
በጉዳዩ ላይ በቀጥታ የሚመለከታቸው የተወሰኑ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የሙያ ማህበራት ተወካዮች በውይይቱ ላይ እንዲገኙ ቢደረግም ጋዜጠኞቹ የውይይቱን ሂደት በድምጽም ሆነ በምስል ቀርጸው ለህዝብ እንዳያቀርቡ ጥብቅ ክልከላ ተደርጎባቸዋል።
ባለሙያዎቹ በመድረኩ ላይ የተገኙት በታዳሚነት ብቻ እንጂ በጋዜጠኝነት ሙያቸው ዘገባ ለመስራት እንዳልሆነም ተነግሯቸዋል።
ይህ ክልከላ የተፈጸመው ራሱ ረቂቅ አዋጁ ከመንግስት አሰራር ላይ "የሚስጥራዊነት ባህልን" ለመስበር የወጣ መሆኑ በተነገረበት መድረክ ላይ መሆኑ የዝግጅቱን ታላቅ ተቃርኖ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል።
ለውይይት በቀረበው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ሰነድ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው አዲሱ ህግ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በመንግስት ተቋማት ዘንድ የተንሰራፋውን መረጃን የመደበቅ ባህል በማስወገድ፣ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትን እና የህዝብን መረጃ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ነው።
ማብራሪያ ሰነዱ አክሎም ከ17 ዓመታት በፊት ወጥቶ የነበረው የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በዋናነት ሳይተገበር የቀረበትን ምክንያት ሲያብራራ "በመንግስት አሰራር የሚንጸባረቀውን የሚስጥራዊነት ባህል ማስወገድ የሚያስችል ግልጽ አሰራር አለመዘርጋቱ እና የመንግስት አካላት የመልካም ገጽታ ግንባታ ስራ የሚሰራው መረጃን በመደበቅ ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት በመያዛቸው ነው" ይላል።
ይሁን እንጂ ይህንኑ "ሚስጥራዊነትን እንስበር" የሚል ማብራሪያ የያዘን ረቂቅ አዋጅ ራሱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚስጥር እና ከተመረጡ ሰዎች ጋር ብቻ መወያየቱ አግራሞትን ፈጥሯል።
"የህዝብ ይፋዊ ውይይት" ተብሎ በተጠራ ስብሰባ ላይ፣ የህዝብ አይን እና ጆሮ የሆኑት ሚዲያዎች ዘገባ እንዳይሰሩ መከልከላቸው፣ የአዋጁ አላማ ዜጎችን መረጃ ለማስታጠቅ ነው ወይስ መረጃን ይበልጥ ለመገደብ?" የሚል ጠንካራ ጥያቄን አስነስቷል።
መሠረት ሚዲያ የተመለከተው የምክር ቤቱ ይፋዊ የጥሪ ደብዳቤ እንደሚያሳየው ኮሚቴው ለተቋማት በላከው ደብዳቤ ላይ "በስብሰባው የሚሳተፉ የስራ ኃላፊዎችን ዝርዝር አስቀድማችሁ አሳውቁን" በማለት ጥብቅ የሆነ የቅድመ-ምዝገባ አካሄድን ተከትሏል።
በተለምዶ በዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ውስጥ "የህዝብ ውይይት" ሲባል ማንኛውም ጉዳዩ ያገባኛል የሚል ዜጋ፣ ተመራማሪ፣ የሚዲያ ተቋምም ሆነ የሲቪክ ማህበረሰብ በነጻነት ተገኝቶ ሀሳቡን የሚሰጥበት፣ እንዲሁም በቀጥታ ስርጭት ለህዝብ የሚተላለፍ መሆን ሲገባው፤ የዚህ ረቂቅ አዋጅ ውይይት ግን በኮታ እና በቁጥጥር ስር ውሎ አልፏል።
በቦታው የተገኙ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ለመሠረት ሚዲያ በሰጡት አስተያየት ይህ ዓይነቱ አግላይ አካሄድ በረቂቅ አዋጁ ላይ እምነት እንዳይጣልበት ያደርጋል ብለዋል። አዋጁ በቀጥታ የሚነካው ጋዜጠኞችንና መረጃ ፈላጊውን ማህበረሰብ ሆኖ ሳለ የውይይቱ ሂደት ራሱ የመረጃ መብት ጥሰት የታየበት መሆኑ በቀጣይ ህጉ ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ በመንግስት ተቋማት ዘንድ ሊያጋጥም የሚችለውን ፈተና ገና ከወዲሁ የሚያሳይ ማሳያ ነው በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
መረጃን ለህዝብ ክፍት ለማድረግ የሚወጣ ህግ ከህዝብ እይታ ተደብቆ በዝግ በር መወያየቱ የኢትዮጵያ የመረጃ ነፃነት ጉዞ አሁንም "ከወረቀት እና ከንግግር" ባለፈ በተግባር እጅግ ፈታኝ እንደሆነ የሚያሳይ ሆኖ አልፏል።
| መሠረት ሚድያ |


