'ትግራይ ክልል ተመርቶ ሲጓጓዝ የነበረ የፋኖ ዩኒፎርም' በሚል ማህበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጨው ምስል ከቆየ ዜና የተወሰደ መሆኑ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ በርከት ያሉ የፌስቡክ አካውንቶች እና ገጾች መነሻዉን መቐለ አድርጎ ሲጓጓዝ የነበረ የፋኖ ታጣቂ ቡድን ዩኒፎርም በቁጥጥር ስር ውሏል የሚል መረጃ እና ምስሎችን እያጋሩ ነበር።
"እነዚህ ማህበራዊ ትስስር ገጾች እና አካውንቶች በርከት ያሉ ቦንዳ ጥቅሎች እና የዕቃ ጭነት ተሽከርካሪ ከፊል አካልን የያዙ ምስሎችንም አጋርተዋል" ያለው ኢትዮጵያ ቼክ የተባለው የመረጃ ማጣርያ ተቋም በተጨማሪም በቁጥጥር ስር የዋለዉ ዩኒፎርም ትግራይ ክልል ውስጥ በአልመዳ ጨርቃጨርቅ የተመረተ እንደሆነ እነዚህ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ጠቅሰዋል ብሏል።
ምስሎቹን ካጋሩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ‘Mahari T Hagos’ የሚል ስም ያለው የፌስቡክ ገጽ አንዱ ሲሆን ከ90 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መረጃውን መልሰው አጋርተዉታል። በተመሳሳይ 'ዲጂታል ኢትዮጵያ' የተባለ ገፅ አጋርቶት ነበር።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሎቹ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሎቹ ሰሞኑን የተነሱ እንዳልሆኑ አረጋግጫለሁ ብሏል። ምስሎቹ ትግራይ ክልል ተመርቶ ሲጓጓዝ የነበረ የፋኖ ዩኒፎርምን እንደማያሳዩም መረጃ አጋርቷል።
"ምስልን በምልሰት መፈለጊያን መተግበርያ በመጠቀም ባደረግነው ማጣራት ምስሎቹ ከ4 ዓመታት በፊት የተነሱ ሲሆኑ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከሆሳዕና ከተማ በቡታጅራ መስመር አድርጎ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሊገባ የነበረ ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ ልባሽ ጨርቆች ምስል ነው" በማለት የመረጃ ማጣርያ ተቋሙ ማስረጃውን አቅርቧል።
ይህን ኮንትሮባንድ በፌደራል ፖሊስ ፀረ-ኮንትሮባንድ አባላት ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን መረጃዉን እና ምስሎቹንም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጳጉሜን 2 ቀን 2013 ዓ.ም በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ አጋርቶ ነበር፡ https://www.facebook.com/share/1BHC495gAY/?mibextid=wwXIfr
የቆዩ እና ከአውድ ውጭ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ በማለት ኢትዮጵያ ቼክ መልዕክቱን አስተላልፏል።
-መሠረት ሚድያ-



