የኢትዮጵያ ማዳበርያ ፋብሪካ የመገንባት ህልም እና ያልተፈታው የጎርድያን ቋጠሮ
በቶፊቅ ተማም ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- ኢትዮጵያ ለግብርና ልማት የተሰጠች እድሜ ጠገብ ሀገር ስትሆን ህዝቦቿም የብዙ ሺህ አመታት ልምድ ያላቸው ገበሬዎች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስታቱም ሣይቀር የህልውናቸው መሰረት ግብርና ላይ የተንጠለጠለ ሆነው ቆይተዋል።
አገሪቱ አብዛኛውን የአለም ክፍል ብዛሃ-ህይወት ሀብት ማስተናገድ ትችል ዘንድ ምቹና በአይነቱ ተፈጥሯዊ የአየርና ስነ-ምህዳር ተሰጥዕ አላት፡፡
በዚህም ሳቢያ የተለያዩ ስነ ምህዳራት መናኻሪያ ልትባል የሚያስችላት የብዛሃ-ህይወት አይነቶች ባለቤት፣ እንዲሁም ዛሬ የአገሬው የህልውና ምንጭ የሆኑትን ጤፍ፤ ስንዴን፣ በቆሎ፣ ጥራጥሬ፣ አትክልቶችን ጨምሮ በእምቅ ቦታነት አላምዳ የምታስተናግድ ምድር ናት፡፡
ምንም እንኳ ሀገሪቱ ለግብርና የተስማማች ያልታረሰ ሰፊ መሬት ሰፋፊ ወንዞች ጅረቶች ቢኖሯትም የሀገሪቱ ግብርና ዘመናዊ በሆነ መልኩ ባለማደጉ ሳቢያ አርሶ አደሩ ያመረተው ምርት ከራስ ምግብነት በዘለለ መጠቀም ያልተቻለ ሲሆን አርሶ አደሩም ካመረተው ምርት ሰባ አምስት በመቶ የሚሆነው ለራሱ እና ለቤተሰቡ ለምግብነት የሚያውልና ለእለት እና ለግል ፍጆታ ብቻ የሚውል /Subsistence Oriented/ ሲሆን ለዚህም ዋናው ምክንያት በሀገሪቱ በሰፊው ከሚዘወተረው ኋላ ቀር እና ያልዘመነ የግብርና ስርአት በተጨማሪ አርሶ ሰደሩ ለግብርናው የሚጠቀመው የእርሻ የጀርባ አጥንት የሆነው ማዳበርያ በቂ እና ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ማዳበርያ አለማግኘት ነው ፡፡
በሀገሪቱ የሚታየውን የማዳበርያ ችግር በቅጡ ለመቅረፍ ብሎም በምግብ ራሷን ለማስቻል በማዳበርያ የታገዘ ዘመናዊ እርሻ ለማስፋት በማሰብ በኢሉባቡር ዞን ያዩ ወረዳ አጨቦና ሰምቦ የገበሬ ማህበር ላይ የያዩ ማዳበርያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ተቋራጭ በሆነው በብሄራዊ የብረታ ብረት ምህንድስና ኮርፖሬሽን /METEC/ አማካኝነት ገንብቶ በሁለት አመት ውስጥ ሊያስረክብ በ 11 ቢሊየን ብር ውል ቢያስርም የታለመትን ግብ ሳያሳካ በርካታ ቢሊየን ብሮች አባክኖ በአካባቢው የነበሩ አርሶ አደሮችን ህይወት ሊቀይር ቀርቶ አርሶ አደሮችን ጦም አሳድሮ ለፋብሪካ ግንባታ የተገዙ ቁሳቁሶች ተዘርፈው እንዲሁም ነዋሪዎች ከቀያቸው ከማፈናቀል ባለፈ ለዚህ ያልተሳካ ፕሮጀክት ሰባት አመታት ባክነውበታል።
ይህንኑ በሀገር ውስጥ ተቋራጭ ሊሳካ ያልቻለ ፕሮጀክት ለመጨረስ ከአውሮፓ እና እስያ ካሉ ኩባንያዎች ጋር በሽሙር ማህበር / joint Venture / ለመጨረስ ቢታሰብም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የያዩ ማዳበርያ ፋብሪካ ግንባታ አለመሳካትን ተከትሎ ኢትዮጵያ በየአመቱ ቢሊየን ብሮች እያወጣች ማዳበርያ ከምትገዛት የሰሜን አፍሪካዋ ሞሮኮ የሚገኘው የፎስፌትና ኬሚካል አምራች ከሆነው ካምፓኒ /OCP/ ጋር ማዳበርያ ፋብሪካ ለመገንባት ከሞሮኮ መንግስት ጋር ስምምነት ቢደረግም በአመት 3.8 ሚሊየን ቶን ማዳበርያ ለማምረት ውጥን የተያዘለት እንዲሁም የሀገሪቱን የማደበርያ ፍላጎት ያሟላል ተብሎ አስቀድሞ ብዙ የተነገረለት የማዳበርያ ፋብሪካ ግንባታ ሳይሳካ ቀርቷል።
ሌላው ከማዳበርያ ጋር ተያይዞ ብዙም ያልተባለለት እና ያልተሳካው ፕሮጀክት በአፍሪካ ከሞሮኮ ፤ አልጄሪያ፤ ግብፅ እና ኮንጎ ቀጥሎ ሰፊ የፖታሽ ክምችት ያላት ኢትዮጲያ በአፋር ክልል የሚገኘውን ፖታሽ ተጠቅሞ የተለያዩ ውህድ ማዳበርያ /belended Fertilizers/ እቀምማለሁ ብሎ የተነሳው ኦላና ፖታሽ የተባለው ኩባንያ ሲሆን ስራውን በአግባቡ ሳይከውን ለያራ ኢንተርናሽናል አስረክቦ ከሀገር ወጥቷል።
ከኦላና ፖታሽ ስራውን የተቀበለውና በሀገሪቱ ማዳበርያ በማቅረብ የሚታወቀው ኩባንያም በወቅቱ በሀገሪቱ የነበረውን የፀጥታ ችግር ምክንያት አድርጎ ስራውን አቁሟል።
ሀገሪቱ የግብርናውን ዘርፍ ወደፊት አራምዶ የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥ በማሰብ የማዳበርያ ፋብሪካ ለመገንባት የጀመረችው ጥረት በተለይ አስቀድሞ መሰራት ያለበትን እና በርካታ በተለይ የኬሚካል ምህንድስና ምሁራንን እና ሌሎችን ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን ያደረገው አመታትን የፈጀ የቅድመ ግንባታ የአዋጭነት የጥናትን ጨምሮ (በዚህ ዙርያ ጥቅምት 13 2015 በሪፖርተር አስተያየት አምድ በኤሜሬትስ ፕሮፌሰር በላይ ወልደየስ የቀረበውን ፅሁፍ መመልከት ይቻላል) እስካልተሳኩ የማዳበርያ ፋብሪካ ግንባታ ሙከራዎች ድረስ ከሀያ አመታት በላይ የፈጀ ጥረት ቢደረግም እስከ አሁን እውን መሆን አልቻለም።
ይህ የማዳበርያ ፕሮጀክት አለመሳካት ብሎም በሀገሪቱ ከአመት አመት እየጨመረ የመጣ የማዳበርያ ፍላጎት መኖር እንደሀገር ከውጭ የሚገባው ማዳበርያ በየአመቱ 10 በመቶ እንዲጨምር ምክንያት ሲሆን ይህን ተከትሎ በተለይ ለማዳበርያ ግዥ የሚወጣው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መንግስት ወደ ማዳበርያ ፋብሪካ ግንባታ ፊቱን እንዲያዞር አስገድዶታል።
ለዚህም በሱማሌ ክልል ስትራቴጂካዊ በሆነ ስፍራ ላይ በኢትዮ ጅቡቲ ኮሪደር በጎዴ አዲስ የማዳበርያ ፋብሪካ ለመገንባት ንብረትነቱ የናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ ከሆነው ዳንጎቴ ግሩፕ ጋር ማዳበርያ ፋብሪካ ለመገንባት ጥረት ተጀምሮ በአሁኑ ወቅት ግንባታውን ለመጀመር የመጨረሻው ምእራፍ ላይ መሆኑን መንግስት አስታውቋል።
ለኢትዮጲያ አፈር ዋናዋናዎቹ ተፈላጊ ንጥረ ነገሮች ናይትሮጂን፤ ፎስፌትና ፖታሽ ሲሆኑ እነዚህን ንጥረ ነገሮች በኬሚካል ማደበርያ መልክ ለማግኘት ዋናው አሞኒያ /ናይትሮጂን እና ሀድሮጂን/ የሚባሉትን ጋዞች ከተፈጥሮ ጋዝ ሲገኙ ይህን የተፈጥሮ ጋዝም ከጎዴ የሚገኝ ሲሆን ፖታሽ ደግሞ ከአዋሳኙ አፋር ክልል የሚገኝ በመሆኑ የማዳበርያ ፋብሪካው የሚያስፈልጉትን ዋነኛ ሰግብአቶች በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያስችል መልካም አጋጣሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ የማዳበርያ ፋብሪካ ተገንብቶ ወደ ስራ ሲገባ በተለይ ማዳበርያ ከውጭ ለማስመጣት የሚወጣውን ውስን የሆነውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ረገድ የሚኖረው ጥቅም አሌ የማይባል ሲሆን በሀገር ውስጥ ማዳበርያ መመረቱ አርሶ አደሩ በአነስተኛ ወጪ ማዳበርያ እንዲገዛ ሲያስችለው፣ በተለይ ከውጭ ሀገራት በሚገዛበት ወቅት ከማዳበርያ ዋጋ በተጨማሪ ወደ ሀገር በማስገባት የሚወጣው ከፍተኛ የትራንሰፖርት ወጪ /freight cost/ ማዳበርያው ላይ የሚደመር በመሆኑ ይህ የማዳበርያ መግዧ ዋጋን በእጅጉ የሚያንር ይሆናል።
በተቃራኒው ማዳበርያ በሀገር ውስጥ ቢመረት ይህ የትራንስፖርት ወጪ ማዳበርያ ላይ የማይጨመር በመሆኑ የማዳበርያ ዋጋ ይቀንሳል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማዳበርያ ዋጋ በመናሩ አርሶ አደሩ በፊት ይጠቀም የነበረውን የማዳበርያ መጠን በግማሽ ለመቀነስ የተገደደ ሲሆን ይህም ምርታማነትን በእጅጉ ይቀንሳል። ማዳበርያ እዚህ ቢመረት አርሶ አደሩ አሁን ከሚገዛው ማዳበርያ በርከት አድርጎ እንዲገዛ በመግዛት የተሻለ ምርታማ ሆኖ ገቢውን እንዲጨምር ሲያስችለው በአሁኑ ወቅት ያለው በሀገሪቱ የኬሚካል ማዳበርያ የመጠቀም ምጣኔ 35 ኪሎ ግራም በሄክታር ሲሆን ይህም 50 ኪሎ ግራም በሄክታር እንዲሆን አፍሪካ ህብረት ካስቀመጠው አነስተኛ ስታንዳርድ ያነሰ ነው።
ይህ የማዳበርያ ፋብሪካ ግንባታ አሁን ያለውን የኬሚካል ማዳበርያ የመጠቀም ምጣኔ ከፍ በማድረግ ሀገሪቱ እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በማዳበርያ አጠቃቀም ደረጃዋን እንድታሻሽል ያስችላል፡፡ የዚህ ማዳበርያ ፋብሪካ መገንባት በአካበቢው ጥቅም ላይ ያልዋሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደርጋል።
ፋብሪካው የሚገነባበት ቦታ ለኢትዮ ጅቡቲ ድንበር ቅርብ በመሆኑ ለግንባታ የሚያስፈልገውን ግብአት በአግባቡ ለማስገባት እንዲሁም ወደፊት መሸጥ ካስፈለገ ለሱማሊያ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን መሸጥ ሲያስችል በዋነኛነት በተለይ ከዚህ ማዳበርያ ፋብሪካ ግንባታ የሀገሪቱ ወጣቶች የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ሲጠበቅ ለገጠሩ አርሶ አደር ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በተጨማሪ የከተማ ግብርና እንዲስፋፋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ሀገሪቱ ማዳበርያ በራሷ ማምረት ከቻለች በማዳበርያ ግዥ ወቅት የሚያጋጥሙ የተለያዩ ችግሮች ትፈታለች። በዋነኛነት በሻጭ ሀገራት ይሁንታ ላይ የተመሰረተ ጉዳዮች ለአብነት ያህል ከውል በኃላ ዋጋ መጨመር፣ የማዳበርያ አቅርቦት በተመለከተ ደግሞ በሀገሪቱ በአብዛኛው የሚያስፈልገው የዳፕ እና ዩሪያ ማዳበርያ ቢሆንም ሻጮች NPS እና NPSB /Nitrogin,phosphrous,sulphur,Boron/ የተሰኙትን ማዳበርያዎች እንድንገዛ የሚያስገድዱበት ሁኔታዎች ያጋጥማሉ።
እነዚህ ማዳበርያዎች የኢትዮጲያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ባስጠናው ጥናት መሰረት የአፈር አሲዳማነትን የሚጨምሩ እና ለኢትዮጲያ አፈር የማይመቹ መሆናቸውን በጥናቴ አረጋግጫሁ ያለ ሲሆን ከዚህ ባለፈ አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ከደረጃ በታች /Substandard/ የሆኑ ማዳበርያዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ሲያደርግ ወደብ ላይ በሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ሳቢያ የሚከሰት የማዳበርያ አቅርቦት መዘግየት በዚህም አብዛኛው ገበሬ የዘር መዝርያ ወቅት እያለፈበት ለከፋ ችግር ሲጋለጥ በተደጋጋሚ ተስተውሏል።
እነዚህ እና መሰል ጉዳዮች ማዳበርያ ከውጭ በማስገባት ሂደት ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶች ናቸው።
የማዳበርያ ፋብሪካው መገንባት በራሱ በግንባታ ሂደት እና ከግንባታ መጠናቀቅ በኋላ በተለይ ለአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል ሲፈጥር በሌላ በኩል መንግስት ለማዳበርያ ቀድሞ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በጀት መድቦ ማዳበርያ ካስገባ በኋላ በሚኖሩ ለውጦች ሳቢያ እንዲሁም እጅግ ተለዋዋጭ በሆነው የማዳበርያ ዋጋ ሳቢያ ለማዳበርያ ድጎማ /subsidy/ ተጨማሪ በጀት የሚመድብ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ፋብሪካ ከተገነባ ይህ በጀት በእጅጉ ሊቀንስ ይችላል። ለአብነት ያህል አምና 15 ቢሊየን ብር ዘንድሮ 8.5 ቢሊየን ብር መንግስት ለማዳበርያ ድጎማ ወጪ አድርጓል።
ከላይ እደተጠቀሰው በሀገራችን የማዳበርያ ፋብሪካ ለማቋቋም በዋነኛነት ሾተላይ የሆነው ጉዳይ በማዳበርያ ፋብሪካ ወቅት ግንባታ በአለም አቀፍ ደረጃ በቂ አቅምና ልምድ ያለው ድርጅት አለማሳተፉ እንዲሁም ለዚህ እጅግ ውስብስብ እና ትልቅ ወጪ ለሚጠይቅ / Capital Intensive/ ለሆነ ፕሮጀክት በተለይ በምህንድስና/ Engineering/ ፤በአለም አቀፍ ግዥ/ International procurement/ ፤እና ግንባታ /construction/ ማለትም የሲቪል እና የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታዎች ላይ ልምድ ያላቸው /EPC Contractors/ አለማሳተፍ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
የአሁኑን የማዳበርያ ፋብሪካ ግንባታ እጅግ ተስፋ ሰጪ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ለሀገራችን ተስማሚ የሆኑትን ዩርያ እና ዳፕ ማዳበርያ አምራች የሆነውና በአፍሪካ በርካታ የማዳበርያ ፋብሪካ ግንባታዎች ላይ የተሳተፈውና የገነባው የዳንጎቴ ግሩፕ አካል የሆነው የዳንጎቴ ማዳበርያ በተለይ በናይጄርያ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ተጠቅሞ ዩርያ ማዳበርያ አምርቶ ከናይጄርያ በተጨማሪ ወደ ሌሎች ሀገሮች መላክ ከመቻሉ ባለፈ በዚህ ግንባታ ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆኑ የማዳበርያ ፋብሪካው እንደ በፊቶቹ በጅምር እንደማይቀር በብዙዎች ተስፋ ተጥሎበታል።
አሁንም ቢሆን ይህን ፋብሪካ ለመገንባት 40 ወራት ወይም 3 አመት ገደማ ተጠናቆ ይመረቃል እየተባለ ከአሁኑ በየሚዲያው እየተገለፀ ይገኛል።
ከቀደምት ተመሳሳይ ግንባታዎች እንዳየነው የያዩ ማዳበርያ በሁለት አመት ያልቃል ተብሎ ከስሞ እንደቀረ የሚታወስ ሲሆን በቅርቡ የሚመረቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 5 አመታት ያልቃል ቢባልም ሶስት እጥፍ ጊዜን ወስዶ በአስራ አምስት አመት ሊጠናቀቅ ከጫፍ ደርሷል።
አሁንም ቢሆን በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን በዋነኛነት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል የሚጠይቅ / Energy Intensive / ፕሮጀክት ከመሆኑ አንፃር ያልተቆራረጠ የሀይል አቅርቦት በአግባቡ አቅርቦ እና ሌሎች ግብአቶችን አሟልቶ የሌት ተቀን ክትትል እና ርብርብ ማድረግ ያሻል።
መንግስት የፋብሪካውን የማምረት አቅም / planting Capacity/ እንዲሁም የአስተዳደር ሁኔታና የሀገሪቱን ድርሻ አሳውቆ የሚያቀርበውን የማዳበርያ መጠን ከሀገሪቱን የማዳበርያ ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር አስታርቆ ቀጣይ የመፍትሄ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል።
ይህ ሰፊ የካፒታል አቅም የሚጠይቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት በተለይ በፋይናንስ ረገድ እጅጉን መደገፍ እና መጠናከር ያለበት መሆኑ እሙን ነው ለዚህም ብሄራዊ ባንክ ያዘጋጀው ሀገራዊ የግብርና ፋይናንስ ትግበራ ፍኖተ ካርታ/National Agri Finance Implementation Road Map /በአግባቡ መተግበር የሀገሪቱን የግብርና ሴክተር በዋነኛት ማዳበርያን በተመለከተ በከፍተኛ ደረጃ በፋይናንስ እንደ ሚደግፈው ንግድ ባንክ ሁሉ ሌሎች የሀገሪቱ የፋይናንስ እና የኢንደስትሪ ተቋማት ይበልጥ ሊደግፉት ይገባል።
ሀገሪቱ የምግብ ሉአላነቷን ሙሉ ለሙሉ ለማረጋገጥ ሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ካለው ማዳበርያ ሶስት እጥፍ ማዳበርያ ማቅረብ እንደሚገባ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ከውጭ የፋይናንስ አካላት እንደ አለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን፤ የአለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ በቂ ድጋፍ በመጠየቅ እንዲሁም በሀገር ውስጥ የግሉን ዘርፍ በንቃት በማሳተፍ ለማዳበርያ ፋብሪካው ግንባታ እና ቀጣይ የማስፋፍያ ስራዎች የሚሆን የሀብት ማሰባሰብ ላይ በትኩረት ስርቶ ከሚገነባው ፋብሪካ የተሻለ ድርሻ መያዝ ይጠበቅበታል::
****መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።መረጃን ከመሠረት!





