"አልረሳነውም"- በአርቲስት አቤል ሙሉጌታ ላይ የተሰነዘረው የህዝብ አስተያየት
በጉዱ ካሳ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- ሙዚቃ የፍቅር ማድመቂያ እና የጦር ሜዳ ማማሟቂያ ሆኖ ሲያገለግል በቆየባት ሀገር ድምፃዊ አቤል ሙሉጌታ በቅርቡ እራሱን በውዝግብ ውስጥ አግኝቷል።
አቤል አዲስ የዘፈን አልበሙ መለቀቁን ይፋ ያደረገው ሃምሌ 11 ቀን 2017 ነበር። በሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ የአልበሙ መለቀቅ በህዝብ ዘንድ መልካም አስተያየትን ይዞ በመጣ ነበር።
ይሁንና ከፌስቡክ እና ከቲክቶክ እስከ ቴሌግራም አስተያየት የሚሰጡ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች "እናስታውሳለን" በማለት ለአርቲስቱ ግልጽ መልእክት አስተላልፈዋል።
በአርቲስቱ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ አስተያየት የሰጡ አብዛኞቹ ተከታዮች አዲሱን የሙዚቃ አልበም አልተቀበሉም።
ብዙዎች አልበሙን የተቃወሙት በዜማዎቹ ወይም በግጥሙ ሳይሆን፣ አቤል በፖለቲካና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ከዚህ ቀደም ይዞት በነበረው አቋም ነው።
ከሶስት አመት በፊት ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) "ናዕት" ወይንም "እያመመው መጣ" የተሰኘ ነጠላ ዜማ ለቆ ነበር።
ይህ ዘፈን በሀገሪቷ ውስጥ ያለውን የብሄር አገዛዝ እና ያስከተለውን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ችግሮች የሚነቅፍ ነው። ይህን የቴዲ አፍሮ ዘፈን ተከትሎ ድፃዊ አቤል ሙልጌታ ለቴዲ ምላሽ ለመስጠት አልፎም ለገዢው ቡድን ድጋፉን ለመቸር "ከዳር ቆሞ" የሚል ዘፈን ለቆ ነበር።
ዘፈኑ የቴዲን ትችት የሚነቅፍ ሲሆን መተቸት ቀላል እንደሆነ፣ ለትውልድ የሚተርፍ ስራ መስራት ግን ከባድ እንደሆነ ይገልፃል።
ኢትዮጵያ በፖለቲካ ውዥንብር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሞራል ፈተና ውስጥ እየኖረች ያለች አገር ናት።
መፈናቀል፣ ብሔር ተኮር ጥቃት፣ የኢኮኖሚ ድቀት ፣ የዋጋ ንረት፣ የእርስ በርስ ግጭት ፣ የሚዲያ አፈና ወዘተርፈ እያስተናገደች በምትገኘው አገር ብዙዎች የመሪዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን በእውቅና አናት ላይ ያሉ ሰዎችን የሞራል ልኬታቸውን እንዲጠይቁ አስገድዷቸዋል።
አንድ የኪነ ጥበው ሰው ህዝብ ላይ በደል ያደረሰን አገዛዝ ሲደግፍ ወይንም ከአገዛዙ የተለያዩ ጥቅሞን ሲያገኝ የሞራል ልኬቱ የቱ ጋር እንደሆነ በግልፅ ያሳያል።
የህዝብን ብሶት ወደጎን ብለው ህዝብን ሲበድሉ ከነበሩ አገዛዞች ጎን ቆመው የነበሩ በርካታ የኪነ ጥበብ ሰዎች ነበሩ፣ አሉም።
በደል የደረሰበት ህዝብ በምላሹ የሚሰጣቸውን ክብር እና አድናቆት ያነሳል፣ ስራዎቻቸውንም ባለመስማት ተቃውሞውን ያሰማል።
በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የተጠበቀ ነው። ቢያንስ በመርህ ደረጃ አርቲስቶችን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ይህን መብት የተጎናፀፉ ናቸው።
ሙዚቀኞች ያላቸውን የትኛውንም አቋም የማንፀባረቅ መብት ያላቸው በመሆኑ ዝም ሊሰኙ አይገባም። ነገር ግን እውነትን በስልጣን ላይ ላሉት በመናገር እና ህዝብ ችግር ላይ ባለ ጊዜ ከገዥ መንግስትጋር በመስማማት መካከል ልዩነት አለ።
አንድ ሰው ህዝብ ስቃይ ውስጥ ባለ ግዜ ከህዝብ ጎን ቆሞ መናገር ባይችል የስልጣን ውዳሴ ከመዘመር ዝምታ የበለጠ ጥበብ ነው። ታሪክ ይህንን ደጋግሞ አሳይቷል።
በተለያየ ግዜ ሙያቸውን አደጋ ላይ ጥለው ከህዝቡ ጎን የቆሙ አርቲስቶች በህዝብ ተከብረው ቆይተዋል። በተቃራኒው በጭቆና ወቅት ከአገዛዞች ጎን የቆሙ የኪነ ጥበብ ሰዎች በህዝብ ውድቅ መደረጋቸውን ታሪክ ደጋግሞ አሳይቷል። አገዛዞች ይቀያየራሉ፣ መንግስታቶች ይተካሉ። ህዝብ ግን ሁሌም እንደቀጠለ ነው።
የህዝብ ቁስልን እና ህመምን መስማት ለማይችል ጥበበኛ ይልቁንም ሆዳቸውን ለመሙላት ሲሉ ከጨቋኝ ገዥ ጎን ለሚቆሙት ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ "አንገት ከሚሰበር ባይበላስ ቢቀር" ብሎ ጨርሶታል።
****መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
መረጃን ከመሠረት!




