የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከሰሞኑ በሰሜን ወሎ በነበረ ውጊያ የቆሰሉ የመንግስት ወታደሮችን ከፋኖ ሀይሎች መረከቡን አስታወቀ፣ ምርኮኞችንም ጎብኝቻለሁ ብሏል
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ በአማራ ክልል በመንግስት ወታደሮች እና በፋኖ ሀይሎች መሀል በተለይ ሰሜን ወሎ አካባቢ በተደረገው ውጊያ በርካቶች ህይወታቸው እንዳለፈ፣ ሌሎች ደግሞ ቁስለኛ እንደሆኑ መረጃዎች ሲወጡ ነበር።
የፋኖ ሀይሎች በስፍራው ድል በመቀናጀት እንደ መርሳ ያሉ ቦታዎችን እንደተቆጣጠሩ ሲገልፁ መንግስት በበኩሉ የኤርትራ መንግስት እና ህወሀት ለፋኖ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር በማለት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፃፈው ደብዳቤ ከሷል።
መሠረት ሚድያ የተመለከተው እና በዛሬው ዕለት በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኩል የወጣ መግለጫም ይህን ያጠናክራል።
ኮሚቴው በመግለጫው በሰሞኑ ውጊያ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን ገልፆ ለተጎዱ ሰዎች ህክምና ማድረጉን እና ምርኮኞችን መጎብኘቱን ገልጿል።
ይህን ተከትሎም የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ባለፉት ስድስት ቀናት ሁለት ቡድኖችን ወደ ላልይበላ እና ወልድያ አካባቢ መላኩን ገልፆ መድሀኒቶችን ማከፋፈሉን እና ለ250 የቆሰሉ ሰዎች ቀዶ ጥገና ማድረጊያ የሚሆን ቁሳቁስ ማቅረቡን አስታውቋል።
“መስከረም 28 ቀን ድርጅታችን 16 ከፍተኛ ጉዳት ያጋጠማቸውን እና ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ካሉበት ቦታ አውጥቷል። ፋኖ እነዚህን ወታደሮች ለቀይ መስቀል አስረክቧል፣ ከዛም ወታደሮቹ ወደ ወልዲያ ከተወሰዱ በኋላ ለመንግስት ሀይሎች ተሰጥተዋል" በማለት መግለጫው ይፋ አርጓል።
አክሎም ትናንት መስከረም 29 ደግሞ የቀይ መስቀል ሰራተኞች በሰሜን ወሎ በፋኖ ሀይሎች ቁጥጥር ስር ያሉ ምርኮኞችን/ታሳሪዎችን ጎብኝቷል ብሏል።
በላልይበላ የነበረው የቀይ መስቀል ቡድን መሪ ማርቲን ትሀልማን "ከሰሞኑ በሰሜን ወሎ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል" በማለት ሙጃ እና ኩልመስክ በተባሉ ቦታዎች የተመለከቱን አጋርተዋል።
ማርቲን በአማራ ፋኖ የተያዙ ተዋጊዎችን መጎብኘታቸውን ገልፀው ያሉበትን ሁኔታ ማየታቸውን እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ንግግር ማድረግ እንዲችሉ ሙከራ መደረጉን ጠቅሰዋል።
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በሰሜን ወሎ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል የቡድን መሪው ገልፀው በአማራ ክልል በሚካሄደው ጦርነት ላይ የሚሳተፉ አካላት ለአለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግ ተገዢ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
-መሠረት ሚድያ-



