ኢቢሲ ውስጥ አለ የተባለ የሰራተኞች ፎርጅድ ዶክመንትን ያጋለጠው ግለሰብ 'መንግስትን በሀይል ለመናድ መሞከር' የሚል ክስ ቀረበበት
(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) አንዳንድ ሰራተኞች ፎርጅድ ወይም እውቅና የሌለው የትምህርት ማስረጃ እንዳላቸው ያጋለጠው የተቋሙ ሰራተኛ ከሁለት ሳምንት በፊት መታሰሩን መዘገባችን ይታወሳል።
መሠረት ሚድያ አሁን የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው አቶ ወገን አበበ የተባለው ግለሰቡ ከመኖርያው ዲላ ከተማ በፀጥታ ሀይሎች ተይዞ ወደ ወላይታ ከተማ ከተወሰደ በኋላ 'መንግስትን በሀይል ለመናድ መሞከር' የሚል ክስ ተመስርቶበታል።
የዲላ ከተማ የፀጥታ አካላት አቶ ወገንን 'ከላይ ታዘን ነው' በሚል ምክንያት እንደያዙት እና አሁን ላይ ማንም የሚረዳው በሌለበት እና በማያውቀው ከተማ እንዲታሰር መደረጉን ምንጮቻችን ጠቁመው ነበር።
"ነሀሴ አንድ ቀን ሶዶ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር። መንግስትን በሀይል ለመናድ በሚል ክስ ቀርቦበት የ14 ቀን ቀጠሮ ተጠይቆ ነበር፣ ፍርድ ቤቱ ግን ለ9 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል" ብለው አንድ በወላይታ ሶዶ የሚገኙ ጉዳዩን የሚያውቁ ምንጭ ተናግረዋል።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ በሰጠው የ9 ቀን ግዜ ፖሊስ ሳያቀርበው በዛሬው እለት ማለትም ነሐሴ 7 ወደ ሀዋሳ ከተማ መወሰዱ ታውቋል።
አቶ ወገን በመጀመርያ ከተያዘ በኋላ 'ሀሰተኛ መረጃ አሰራጭተሀል' ሲባል እንደነበርና በ48 ሰዐት ውስጥ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ እንደቆየም ተሰምቷል።
የቀድሞ የኢቢሲ ሰራተኞ የነበረው አቶ ወገን ከዚህ በፊትም ጥር ወር ላይ ታስሮ የሽብር ክስ ቀርቦበት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
በወቅቱ 52 ቀን ታስሮ ጥር 26/2017 ዓ. ም ተለቆ ነበር።
"የተያዝኩት ተወልጄ ባደግኩባት ዲላ ከተማ ነው፣ ከላይ በመጣ ትእዛዝ ተብሎ ቤቴ ተበረበረ። ዲላ 5 ቀን ከታሰርኩ በኋላ ወደ ወላይታ ሶደ ተወሰድኩ፣ 3 ቀን ታስሬ ወደ ሀዋሳ የፌደራል ምርመራ ተወሰድኩ፣ ከዛም አንድ ሳምንት ሀዋሳ ታስሬ ወደ አዲስ አበባ ፌደራል ምርመራ ሜክሲኮ ተወሰድኩ" በማለት ያለፈበትን የእስር ሂደት በወቅቱ ለሚድያችን አስረድቶ ነበር።
መሠረት ሚድያ ጥር ወር ላይ የተመለከተው የክስ ወረቀት እንደሚለው አቶ ወገን በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ቡድን አባሎች ጋር በመቀናጀት እና ቡድኑን በመምራት መጠርመሩን ይገልፃል።
"እኔ አማራ ክልል ሄጄ እንኳን አላውቅም፣ ዘመድም የለኝም" የሚለው አቶ ወገን እንኳን ለተለያዩ ቡድኖች የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ ኢቢሲ ከስራው ካባረረው በኋላ ስራ እንኩዋን እንደሌለው ገልጿል።
ግለሰቡ ከአንድ አመት በፊት የአንዳንድ የኢቢሲ ሰራተኞች የፎርጂድ ዶክመንትን በተመለከተ ካጋለጠ በኋላ ተቋሙ መረጃውን ያወጣብኝ የቀድሞ ሰራተኞዬ "ተአማኒነቴ እንዲቀንስ አድርጓል" በማለት 10 ሚልዮን ብር ካሳ ይክፈለኝ ብሎ ክስ መስርቶም ነበር።
ይሁንና ራሱ ኢቢሲ ከወራት በፊት በተቋሙ ሰራተኞች ላይ ባደረገው የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ ሂደት የ400 ሰራተኞቹ ሰነድ ፎርጂድ/ሀሰተኛ መሆኑን እንዳረጋገጠ አንድ ሾልኮ የወጣ ዶክመንት ጠቁሞ ነበር።
ይህ ሆኖ እያለ የተቋሙ ሀላፊዎች እርምጃ እንዳይወሰድ ይህን መረጃው እንደደበቁ፣ በጥቆማ አቅራቢዎች ላይም ዛቻ እና ማስፈራርያ እያደረሱ እንደኮነ በወቅቱ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለጠቅላይ አቃቤ ህግ የፃፈው ደብዳቤ አሳውቆ ነበር።
*መሠረት ሚድያ*



