ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማይወክሉን ግለሰቦች ጋር ውይይት ሊያደርጉ ነው በማለት የጤና ባለሙያዎች ቅሬታቸውን አሰሙ
(መሠረት ሚድያ)- በርካታ ቀናትን ካስቆጠረው የጤና ባለሙያዎች የስራ የማቆም አድማ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርብ ቀናት ከተወሰኑ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ሊያደርጉ መሆኑ ታውቋል።
ይሁንና እነዚህ 'ተወካይ' ተብለው ከጠ/ሚሩ ጋር ውይይት ሊቀመጡ እየተዘጋጁ ያሉ ባለሙያዎች የአብዛኛውን የጤና ባለሙያ ጥያቄ የማያስተጋቡ እና ለመንግስት ቅርበት ያላቸው ሆን ተብሎ እየተመለመሉ መሆናቸውን መሠረት ሚድያ የደረሰው ቅሬታ ያሳያል።
"ስብሰባው እየተዘጋጀ ያለው ከመላው ሀገሪቱ ከተውጣጡ የፓርቲ አባላት ከሆኑ ባለሙያዎች ጋር ነው፣ ይህን ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያውቅ ይገባል" በማለት ለሚድያችን አስተያየት የሰጡት አንድ የጤና ባለሙያዎግ እንቅስቃሴ አስተባባሪ ናቸው።
የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማህበር በቴሌግራም ቻናሉ ላይ ባደረገው መጠይቅ (poll) 94 ፐርሰንት የሚሆኑት ባለሙያዎች በቀጣይ ሊደረግ የታሰበው ስብሰባ እንደማይወክላቸው በምርጫቸው አሳይተዋል።
"እስከመቼ በይስሙላ ስብሰባና ውይይት ህዝብን ለመሸወድ ይሞከራል? ለማንኛውም ደህና ተከፍሎን እና መሰረታዊ ነገር ተሟልቶልን ሳይሆን በብዙ የኢኮኖሚ ሀሳብ ጭንቀት ውስጥም ሆነን ሳንታክት በፍቅር እያገለገልንህ ያለህ ህዝብ ሆይ እውነታውን እወቅልን" በማለት በዚህ ዙርያ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አክለውም "በቀጣይ ቀናት ማንኛውም ከጤና ባለሙያ ጋር ተሰበሰብኩ ተብሎ የሚሰራ የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ በሙሉ እውነተኛውን፣ የተቸገረውን፣ የራበውን ጥያቄ እየጠየቀ ያለውን የጤና ባለሙያ እንደማይወክል ህዝባችን እንዲያውቅልን እንፈልጋለን። እርካታ ምግብ አይሆንም። በችግራችን ጊዜ ለራሳችንም፣ ለልጆቻችንም ሊደርስልን አልቻለም። የቤት ኪራይ አይከፍልም። ከመታረዝ አያድንም። አድምጡን። ስሙን። ከሚወክሉን የEHPM የቦርድ አባላት ጋር ብቻ ለመወያየት ፈቃደኛ ሁኑ" ብለዋል።
ፎቶ: ፋይል
መረጃን ከመሠረት!



