ፌደራል ፖሊስ ለፓስፖርት ከፍተኛ ብር በመቀበል ህገወጥ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ኢንተርኔት ቤቶች ላይ ድንገተኛ ዘመቻ በማረግ በርካቶችን መያዙ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን በቅርብ ወራት በተደጋጋሚ ባቀረባቸው ዘገባዎቹ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ባሉ የኢሚግሬሽን ቢሮዎች እና በተባባሪዎቻቸው አማካኝነት ስለሚፈፀም ህገወጥ ድርጊት ማስነበቡ ይታወሳል።
የተወሰኑ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኞችና ደላሎች ተመሳጥረው ድርጊቱ ላይ መሰማራታቸውን መሠረት ሚድያ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ማጣራቶች አረጋግጦ ነበር።
ከተቋሙ ግቢ ውጪ ያሉ አካላት እና የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ተመሳጥረው ለአስቸኳይ ፓስፖርት እስከ 40 ሺህ ብር እያስከፈሉ ሲሆን በተቋሙ ውስጥ ከሚሰሩ አንዳንድ የአይቲ ባለሙያዎች ጀምሮ እስከ አመራሮች የሚሳተፉበት ኔትወርክ በመዘርጋት ሲስተሙን ከእነርሱ ጋር ተመሳጥረው የሚሰሩ ግለሰቦች ብቻ ማግኘት እንዲያደርጉ በማመቻቸት እንደሚሰሩ ዘግበን ነበር።
አሁን የደረሰን መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ፌደራል ፖሊስ ከባለፈው ሀሙስ እለት ጀምሮ በተለይ በአዲስ አበባ እና ሀዋሳ ከተሞች ላይ ከፍተኛ ዘመቻ በማካሄድ እነዚህን በህገወጥ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር አውሏል።
በዚህ ዘመቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች እንደተያዙ የታወቀ ሲሆን ይህም በአይነቱ ግዙፍ የነበረ እና ጠንካራ ኦፕሬሽን እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል።
“በክልል ከተሞች ጭምር በኦፕሬሽኑ ላይ የተሳተፉት የፌደራል ፖሊሶች ነበሩ፣ በቁጥር 3,800 ገደማ ሰዎች ተይዘዋል" በማለት አንድ የመረጃ ምንጭ ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና፣ መሠረት ሚድያ የሲስተም አድሚኖች እየተሳተፉበት ከደላሎች ጋር እንደሚሰሩበት ያጋለጠው ድረ-ገፅ በአዲስ መተካቱ ታውቋል።
አዲሱ ድረ-ገፅ https://www.immigration.gov.et/ ሲሆን የቀድሞውን ሲስተም በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተክቶ እንዲሰራ እንደሚደረግ ታውቋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከዚህ በፊት ሲጠቀምበት ከነበረው የኦን ላይን አፕሊኬሽን በተጨማሪ አዲሱን የኢ ፓስፖርት የኦን ላይን አፕሊኬሽን በመጠቀም ህዝቡ ማመልከት እንደሚችል ከዛሬ ጀምሮ ማሳወቅ ጀምሯል።
መረጃን ከመሠረት!




