የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች እና ተግዳሮቶቻቸው:- ችግርን በትክክል መለየት የመፍትሄው ግማሽ ነው እንዲሉ
በዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ ለመሠረት ሚድያ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ለረጅም አመታት በበርካታ ስር የሰደዱ እና ውስብስብ ችግሮች ተውጠው ለውጥ አልባ ጉዞ ላይ ቆይተዋል። የክለቦቹ ደካማ ተቋማዊ ቁመና፣ ያልተደራጀ ድርጅታዊ (አስተዳደራዊ) መዋቅር እና በሰለጠነ ባለሞያ አለመመራት፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት ጎልቶ የማይታይበት የፋይናንስ አስተዳደር፣ የተደራጀ የበጀት ዕቅድ አለመከተል፣ እና ለበጀት አጠቃቀም ጉድለት በተደጋጋሚ መጋለጥ፣ የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር ዙሪያ ግልጽነት መጉደል፣ የገቢ ምንጭ የማስፋፋት ተነሳሽነት አለመኖር፣ የብሄር መገለጫ መሆን፣ ለታዳጊ እና ተተኪ ተጫዋቾች ልማት አናሳ ትኩረት መስጠት፣ የተሟሉ የመለማማጃ እና መጫወቻ ሜዳዎች/ ስቴዲየሞች እጥረት፣ የአካባቢያዊ መንግስታት የፋይናንስ ጥገኛ መሆን፣ እና የአካባቢያዊ መንግስታት ጣልቃ ገብነት በቦርድ አመራር አደረጃጀት ውስጥ ጎልቶ መታየት ፣ ከክለቦቹ ስር የሰደዱ ችግሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በተጨማሪ ክለቦቹ ያለባቸው የፖለቲካ ጫና፣ ለከፍተኛ የመፍረስ/የመቋረጥ ዕድል መጋለጥ፣ በቡድን እንጂ በክለብ መዋቅር አለመደራጀት፣ ጊዜያዊ ስኬት/ሜዳ ላይ ያተኮረ አሰራር በስፋት መስፈን፣ በክለቦች መካከል (መንግስትና ህዝባዊ) የባለቤትነት ይዞታ ወጥነት ልዩነት፣ የብቃት እንጂ የስራ ፈቃድ ይዞ አለመስራት፣ የተመጣጠነ ተቋማዊ ቁመና አለመኖር፣ ራዕይን የሰነቀ እቅድ አለመንደፍ እና በረጅም ዕቅድ አለመመራት፣ ውሱን ተራማጅ አስተሳሰብ በክለቦች ዘንድ መኖር፣ እና የደጋፊ ምዝገባ ስርዓት በተደራጀ መልኩ አለመመቻቸት የክለቦቹ ተጨማሪ እክሎች ናቸው።
ለመሆኑ እነዚህ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ምንድናቸው? በዚህ ፅሁፍ ጥልቅ ጥናት ላይ የተመረኮዘ የመፍትሄ ምክረ ሀሳቦች ተጠቁመዋል። ጥልቅ ጥናቱ፣ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባለቤትነት፣ በፊት ኮርነር ስፖርት ኮንሰልታሲ አስተባባሪነት እና በዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የቡድን መሪነት ሁለት ዓመት በፈጀ ጥናት የተመላከቱ መሆናቸውን መጥቀስ አግባብ ይሆናል። ከ140 ሀገራት በላይ ተሞክሮን ያካተተ፣ ሀገር አቀፍ አህጉራዊ አለም አቀፋዊና የፊፋ ፖሊሲ ተሞክሮዎች የተመለከተ፤ የህግ ማእቀፎችን ያጣቀሰ፣ ከ200 በላይ የምርምር ጥናት ፅሁፎችን ያማከረ፣ እና ቀጥተኛ ተፅዕኖ ካላቸው ከ90 በላይ የአገራችን ባለሞያዎች ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቆችን ያካተተ፣ ጥልቅ ሰፊና ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናት እና አገር በቀል የልማት ፍኖተ ካርታ ያቀረበ የምርመራ ውጤት ነው።
ጥናቱ በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰ ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለመፈተሽ የተደረገው ጥናት ውጤት ለአንባቢያን በዚህ ተከታታይ ጽሁፍ ተቀናብሮ ይቀርባል። ጥናቱ በተጠቀሱት መረጃ እና ማስረጃዎች ላይ የተተራሰ ሲሆን በተለይ የክለቦችን ነባራዊ ሁኔታ ለመፈተሽ በዘርፉ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ባላቸው ከ90 በላይ ባለሞያዎችን ያሳተፈው ዳሰሳ ላይ ያተኩራል። ከፌዴሬሽኑና ሊጉ አመራሮችና ክለብ ስራ አስኪያጆች ጀምሮ እስከ ተጫዋቾች፣ ደጋፊዎችና ስፖርት ጋዜጠኞች ድረስ በጥናቱ ተሳትፈውበታል። የተሰበሰቡት መረጃዎች የክለቦችን ተግዳሮቶች በግልጽ ለይቶ ለማውጣት አስችሏል። በዚህ ክፍል ጥቂቶቹን እንመለከታለን።
የአካባቢያዊ መንግስታት (የፋይናንስ) ጥገኛ መሆን የአካባቢያዊ መንግስታት ከለቦችን ይዘው ለረጅም ዓመታት መቆየታቸው በጥናቱ ተሳታፊዎች ምስጋና ተችሮታል። በእኩሌታውም፣ በፕሪሚየር ሊጉ ውስጥ ያሉ ክለባትን ድርጅታዊ አቋም በሚመለከት በሰፊው በተሳታፊዎቹ የተነሳው ስጋት፣ አብዛኞቹ ክለቦች የመንግስት ጥገኛ መሆናቸው ነው። እንደየባለ ድርሻ አካላቱ እይታ፣ ክለቦች የመንግስት ጥገኛ መሆናቸው ከአሳደራቸው ተጽዕኖዎች መካከል፦ ዋስትና የሌላቸው እንዲሆኑ፣ ራሳቸውን ችለው እንዳይቆሙ፣ በፖለቲካ ሰዎች እንዲመሩ፣ እና ህዝባዊ መሰረት እንዳይዙ አድርጓቸዋል። እንደ በርካቶቹ ተሳታፊዎች ምልከታ፣ ክለቦች በበጀት፣ በአመራር፣ በአደረጃጀት፣ በሰው ሃይል የመንግስት ጥገኛ ሆነው መቆየታቸው ስፖርቱን እስካሁን ለተጓዘበት ርቀት ለማስኬድ ያስቻለ ቢሆንም፣ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው መመራታቸው ለክለባቱ ብቻ ሳይሆን ለሊጉ ህልውና ቀጣይነት ስጋት መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸዋል። በአለው አሰራር፣ የአካባቢ መንግስት ክለቦችን ይቆጣጠራል፣ ይከታተላል፣ ድጋፍ ያደርጋል፣ ኦዲት ያደርጋል፡፡ ይህም፣ የሃላፊነት መጣረስን ከማስከተሉ ጎን ለጎን የአብዛኞቹ ክለባት የለት ተለት እንቅስቃሴ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን በቀላሉ የሚጋብዝ ሆኖ የተደራጀ መሆኑን በጥናቱ የተሳተፉ የባለ ድርሻ አካላቱ በስፋት የተጋሩት አተያየት ነው። በተያያዘም፣ የክለባት ህልውና በአካባቢመንግስት አመራሮች ይሁንታ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ለመፍረስ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸው ተነግሯል።
በዚህም የተነሳ፣ ክለቦች የአካባቢ መንግስት ጥገኛ መሆናቸው ለአክሲዮን ማህበሩ ቀጣይ እድገት ስጋት መሆኑ በበርካቶች ተነስቷል። በጥናቱ የተካፈሉ ተሳታፊዎች ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻልበት ደረጃ፣ ክለቦች ህዝባዊ መሰረት ሊኖራቸው እንደሚገባ በአጽዕኖት ገልጸው፣ መንግስት ለክለቦች (የቀን ተቀን እንቅስቃሴ) የሚያደርገው ድጋፍ ቀስ በቀስ እየቀነሰ እንዲሄድና ትኩረቱ መሰረታዊ የሆኑ የእግር ኳስ ስፖርት መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ላይ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ ክለቦች በመንግስት ሹመኞች የበላይነት መመራታቸው፣ የአስተዳደር ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን፣ በተለይ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆናቸውን የጥናቱ ተሳታፊዎች በስፋት አንስተዋል።
የመንግስት ጥገኝነትን መሰረታዊ ችግር በሚመለከት የተለያዩ ነገር ግን የተዛመዱ አተያየቶች የተጋሩ ሲሆን፣ አንድ የጥናቱ ተሳታፊ የሆኑ የወቅቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራር ያቀረቡት ምልከታ የብዙዎችን እይታ የሚያንጸባርቅ ነው፦
"ክለቦች የመንግስትን እጅ እየጠበቁ ነው የሚኖሩት። የሚደረግላቸው ድጎማ ከአስፋልት፣ ድልድይ፣ ኮንዶሚኒየም፣ ጤና ጣቢያ ከደሃው ህዝብ ተቀንሶ ከሚሰበሰበው ነው። በአንድ ወቅት በብሄራዊ ደረጃ መንግስት ካልፈለገ ክለቦች ባጠቃላይ ሊፈርሱ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አሁን ላይመስል ይችላል እንጂ፣ ሊጉ ይህን ችግር በድፍረት ካልቀረፈ በስተቀር ዋነኛ እንቅፋቱ ይሆናል። ክለቦች ህዝባዊ መሆን “ ሲሉ አካፍለዋል።
ምክረ-ሃሳብ፦ ክለቦችን ከመንግስት ጥገኝነት ለማላቀቅ፣ በዋናው ጥናት ዝርዝር ምክረ-ሃሳቦች ቀርበዋል። ለመጠቆም ያህል በዋናነት ቀጣዮቹ ምክረ-ሃሳቦች በጠቋሚነት ተነስተዋል።
ክለቦችን ህዝባዊ ማድረግ (የተመዘገበ ደጋፊ 30%፣ ህዝብ 40%፣ እንዲሁም መንግስት 30% ድርሻ መያዝ)፣ በአንድ የውድድር ዘመን ሊጉን የሚቀላቀል ክለብ ማስጨረስ፣ በክለቦች ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ እና የታደሰ አመለካከት ማስረፅ፣ ድርጅት በራእይ፣ ተልዕኮ፣ ስትራተጂ እና ዕቅድ መመራት ስላለበት፤ ክለቦች የጠራ ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ እና የ5 -10 ዓመት እቅድ ነድፈው እንዲያቀርቡ ማድረግ
የአመራር አደረጃጀት ችግር (የመንግስት እጅ)
የክለቦቹ አመራሮች ላይ ሰፊ እና ተመሳሳይነት ያለው ስጋት በጥናቱ ተሳታፊዎች ተጠቅሷል። ለአብነት ያህል የቦርድ አመራር አባላቱ የአካባቢያዊ ፖለቲካ ሹመኞች መሆናቸው፣ በአብዛኛው በስፖርቱ መስክ አናሳ እውቀት ያላቸው አመራሮች በአባልነት የታቀፉበት መሆኑ፣ ውክልናቸው የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርጉ የመንግስት ቢሮ ተወካዮች ላይ ያተኩረ መሆኑ፣ የፖለቲካ ጫና በሚበዛባቸው አመራሮች መመራታቸው፣ ወዘተርፈ የሚሉ ይገኙበታል። በተለይ፣ ክለቦች በአብላጫው ከከተማ እስከ ክልል የመንግስት ባለስልጣናት በላይነት የሚመሩበት አሰራር መኖሩን የጥናቱ ተሳታፊዎች በስፋት ያነሱ ሲሆን፣ የክለብ ስራ አስኪያጆች የማስፈጸም ሚና እንጂ የመወሰን ስልጣን እንደማይሰጣቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ሆኖም ግን፣ ክለቦች በአደረጃጀታቸው ራሳቸውን መቻል እንዳለባቸው በአጽዕኖት ተመልክቷል። ተያይዞም፣ የክለቦችን የአመራር አደረጃጀትን በሚመለከት መንግስት እና የአካባቢያዊ መንግስት ባለስልጣናትን ለየቶ ማየት ሊጤን የሚሻው ጉዳይ መሆኑንም የተወሰኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች የተጋሩት እይታ ነው። ለነዚህ ተሳታፊዎች፣ ክለቦች የመንግስት ጥገኛ እንዲሆኑ የሚፈለገው የግድ መንግስት ሳይሆን የአካባቢው የመንግስት ባለስለስልጣን ፍላጎቱን ለማስፈጸም ስለሚጠቀምበት እንደሆነ አካፍለዋል። በእኩሌታውም፣ ለከተማቸው ነዋሪ የእግር ኳስ ክለቦቻቸው ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ተረድተውም ከልብ በመነጨ ተነሳሽነት ቡድኖቻቸውን የሚደግፉ አስተዳዳሪዎች እና ከንቲባዎች መኖራቸውንም የጥናቱ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል።
የክለቦችን የአመራር አደረጃጀት ችግር በሚመለከት፣ ከእግር ኳስ ፊዴሬሽን በኩል የተሳተፉ አንድ የባላድርሻ አካል የግል እይታቸውን ያካፈሉበት አገላለጽ የብዙዎችን አተያየት የሚወክል ነው። ተሳታፊው እንዳስቀመጡት፦
"ከስራ አስኪያጅ ቅጥር እና የቦርድ አሰያየም ጀምሮ፣ ሙያዊ የሆነ ጉዳይ ከማስቀደም ይልቅ ፖለቲካዊ ተልዕኮን የሚያስፈጽም ውክልና ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ቦርዶችን የሚመሩት የከተማው ከንቲባ ወይም የዞን አስተዳደር ናቸው። አባላቱም፣ የፖለቲካ ተሹዋሚዎች ስለሚሆኑ ጠጋ ብሎ ጊዜ ሰጥቶ ከመምራት እና ከማገዝ አኳያ ክፍተት አለ፡፡ ስለዚህ ሙያዊነትን የተከተለ የቦርድ አመራር አባላት ብዙዎቹ ክለቦች የላቸውም" ሲሉ እይታቸውን አካፍለዋል።
ክለባቱ የመንግስት ጥገኛ ሆነው እና በፖለቲካ ጫና ውስጥ የሚኖሩ መሆኑን የጥናቱ ተሳታፊዎች በስፋት ጠቁመው፣ እንዲሁም ወጥ የሆነ የባለቤትነት ይዞታ በክለቦች መካከል አለመኖሩን (መንግስት እና ህዝባዊ) በማንሳት፣ ክለቦችን ወደ ህዝባዊነት መቀየር እንደሚገባ በተደጋጋሚ እና ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በተሳታፊ የባለ ድርሻ አካላቱ ተነስቷል።
ምክረ ሃሳብ፦ የጥናቱ ተሳታፊዎች በስፋት እንዳነሱት፣ ክለቦች የመንግስት ጥገኛ መሆናቸው እና የሚመሯቸው የመንግስት ባላስልጣናት መቀያየር የረጅም ጊዜ ራዕይ ሰንቀው እንዳይንቀሳቀሱ ከገደቧቸው ምክኒያቶች መካከል አንዱ ነው። በመሆኑም የክለቦች የቦርድ አባላት የአንድን ክለብ የእድገት አቅጣጫ እንዲሁም ህልውና የሚወስኑ በመሆናቸው፣ ከመንግስት ውክለና በተጨማሪ በማህበረሰቡ እና በደጋፊዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው አባላት እንዲካተቱ ማድረግ ስፖርቱን በበላይነት የሚመለከተው አካል ሃላፊነት ነው። በደጋፊዎች እና በማህበረሰቡ የተወከሉ የቦርድ አባላት፣ በተሻለ ሁኔታ ክለቦች የረጅም ጊዜ ራዕይ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ዕድል ይኖራቸዋል።
ለዚህም የክለቦች የቦርድ አባላት ስብጥር (ከከንቲባ፣ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ፣ የጤና ቢሮ ሃላፊ እና የጸጥታ ሃላፊ፣ ከሚለው ጊዜያዊ ስኬት ላይ ካተኮረ አስተሳሰብ ወጥተው) ቢያንስ የ½ኛው የቦርድ አባላት ቁጥር በደጋፊዎች/በማህበረሰቡ በሚመረጡ (በመስኩ ሞያ የሰለጠኑ እና በህዝቡ ታአማኒነትን ያተረፉ) አባላት እንዲመራ በሊግ ደረጃ ደንብ እንዲወጣ ይመከራል። በዚህ ረገድ፣ ፊፋ ስፖርቱን ከፖለቲካ መለያየትን በሚመለከት የሚያሰፈረውን ደንብ በመከተል መተግበር ይቻላል። ከተለያየ የህብረተሰቡ ክፍል የተውጣጡ የአመራር አባላት፣ ከሚቀያየሩ የፖለቲካ ሹመኞች በተሻለ ክለቦችን የመምራት እድል ይኖራቸዋል።
ተቋማዊ ቁመናቸው ደካማ መሆኑ
የክለቦቹ ነባራዊ ችግሮች ተብለው በጥናቱ ተሳታፊዎች ከተነሱት መካካል ተቋማዊ ቁመናቸው ደካማ መሆኑ ሌላኛው ነው። አብዛኞቹ ክለቦች፣ አደረጃጀታቸው መዋቅር ተዘጋጅቶለት፣ ጽህፈት ቤት ኖሯቸው፣ ህጋዊ ፈቃድ አግኝተው፣ በመዋቅሩ መሰረት የሰው ሃይል ተመድቦ የተዋቀሩ አለመሆኑን (የሆኑትም አጥጋቢ አንዳልሆነ) የጥናቱ ተሳታፊዎች በስፋት ገልጸዋል። በመሆኑም፣ በተቋማዊ ቁመናቸው ምክንያት የክለቦች ቀጣይነት የስጋት ምንጭ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል በበርካታ ተሳታፊዎች ተነስቷል። ተቋማዊ ቁመናን በተመለከተ በበርካታ ተሳታፊዎች ከተነሱት ተዛማጅ የአክሲዮን ማህበሩ ነባራዊ ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል። እነኝህም፦ ለሰፋ የመፍረስ ዕድል የተጋለጡ መሆናቸው፣ በቡድን እንጂ በክለብ መዋቅር አለመደራጀታቸው፣ በጊዜያዊ ስኬት ወይም በዋንጫ ላይ ያተኮረ አሰራር በስፋት መስፈኑ፣ ራዕይ የሰነቀ እቅድ አለመንደፍ እና በእቅዱ አለመመራት፣ ውሱን ተራማጅ አስተሳሰብ በክለቦች ዘንድ መኖሩ፣ የብቃት ማረጋገጫ እንጂ ህጋዊ የስራ ፈቃድ ይዘው አለመስራታቸው፣ በክለቦች መካከል የተመጣጠነ ተቋማዊ ቁመና አለመኖሩ፣ በክለባቱ መካከል ራሱን የቻለ ሰፊ ልማታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልዩነት መፈጠሩ፣ እና የደጋፊ ምዝገባ ስራዓት በተደራጀ መልኩ አለመመቻቸቱ የሚሉ ናቸው።
በአንድ ተቋም ግንባታ ሂደት ውስጥ መሰረታዊ ከሆኑ ድርጅታዊ ግብአቶች መካከል በህጋዊ የስራ ፈቃድ መንቀሳቀስ፣ በመተዳደሪያ ደንብ መገዛት፣ በጠቅላላ ጉባኤ መመራት፣ እና ቢሮ እና በመስኩ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማሟላት ዋነኞቹ ናቸው። ሆኖም ግን፣ በፕሪሚየር ሊጉ ስር ያሉ አብዛኞቹ ክለቦች እነዚህ መሰረታዊ ግብዓቶች የሚጎላቸው መሆኑን የጥናቱ ተሳታፊዎች በስፋት ያነሷቸው ጉድለቶች ናቸው። በነዚህ አራት መሰረታዊ ግባቶች ዙሪያ በርካታ እይታዎች የተጋሩ ሲሆን፣ ቀጥለው የቀረቡት ምልከታዎች በርዕሰ ጉዳዮቹ ዙሪያ አተያየታቸውን የተጋሩ ተሳታፊዎችን እይታ የሚወክል ነው። የክለብ አስተዳደር የሆኑ አንድ ተሳታፊ ያካፈሉት ምልከታ ብዙዎች የክለቦች የስራ ፈቃድ ዙሪያ የሚስተዋሉትን ጉድለቶች ያንጸባርቃል፦
"አብዛኞቹ ከለቦች ፈቃድ እንዳላቸው ቢጠየቁ መልሳቸው ‘አዎ’ ነው የሚሆነው። ግን ብዙዎቹ ያላቸው እንደኛ ከከተማቸው ስፖርት ኮሚሽን ወይም ከክልል የተጻፈ ደብዳቤ እና ከፌዴሬሽን የምናገኘው ሰርተፊኬት ነው። ነገር ግን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ከለቦች ከሁለቱ በስተቀር የመንግስት በመሆናቸው የራሳቸው ፈቃድ ኖሯቸው እንዲደራጁ አልተደረገም። የመንግስት በመሆናቸውም ማረጋገጫ አምጡ ቢባል በየትኛውም ጊዜ ደብዳቤ ለማጻፍ የትኛውም ክለብ ችግር የለበትም። ግን የመንግስት ክለባት የስራ ፈቃድ የላቸውም" ብለዋል።
በተመሳሳይ፣ ጠቅላላ ጉባዔ በክለቦች አመራር ዙሪያ ያለውን ሚና በሚመለክት የጥናቱ ተሳታፊዎች ያጋሩትን አተያየቶች፣ የባህል እና ስፖርት ሚንስትር መስሪያ ቤትን ወክለው ከተሳተፉ ባለሞያ መካከል አንዱ ያቀረቡበት መንገድ ያንጸባርቀዋል። ባለሞያው እንዳስቀመጡት “አንድን ድርጅት፣ እንደተቋም ውጤታማ የሚያደርገው ተቋማዊ ቁመናው ነው፡፡ በአግባቡ ጠቅላላ ጉባዔው ተገናኝቶ፣ በታቀደለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔውን አድርጎ፣ ስራ አስፈፃሚውን የሚገመግም የአሰራር ስራዓት ለብዙዎች ክለቦቻቸን እንግዳ ነው። በዘፈቀደ የተደራጁ ናቸው” ብለዋል።
ምክረ ሃሳብ፦ ፕሪሚየር ሊጉ፣ በስሩ ያሉ ክለባት ቢያንስ መሰረታዊ የድርጅት መዋቀር ተከትለው አስፈላጊውን የሰው ሃይል፣ የጊዜ ተመን በጅቶ፣ ደረጃ በደረጃ እንዲያሟሉ ሊጠበቅባቸው ይገባል። በክለቦች ተቋማዊ ቁመና የግንባታ ሂደት ውስጥ፣ ሃላፊነት ያለበት የስፖርቱ ከፍተኛ አመራር አካል ክትትል ሊያደርግ እና አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያቀርብ ይገባል። ድጋፉ፣ አቅጣጫ በማመላከት፣ በማማከር፣ ከሌሎች የተሻሉ ክለቦች ትምሀርት መቅሰም የሚችሉበትን ምህዳር በማመቻቸት ሊቀርብ ይችላል። ለምሳሌ፣ በቀላሉ የተደራጀ መተዳደሪያ ደንብ የሌለው ክለብ፣ ከሌሎች የተሻለ መተዳደሪያ ደንብ ካላቸው ክለቦች ሰነዱን ተውሰው የራሳቸውን እንዲቀርጹ ከማገዝ ሊጀምር ይችላል። በተቋማዊ ግንባታ ውስጥ፣ የአሰራር ስርዓትን መዘርጋት የስኬት መሰረት በመሆኑ፣ ክለቦች የአሰራር ስርዓትን የሚያሰፍኑ የተለያዩ መመሪያዎች (ለምሳሌ፦ የስነ ምግባር፣ ፋይናንስ፣ ህክምና፣ ወዘተ) ሊቀርጹ ይገባል። ልብ አንዲሉ በዋናው ጥናት ዝርዝር ምክረ፡ሃሳቦች በዚህ አጀንዳ ላይ ቀርቧል።
ማስታወሻ፦ የኢትዮጵያ ክለቦች ችግሮች ብዙ ናቸው፤ በዚህ ጥናት ዳሰሳ ተደርጎባቸዋል፤ የመፍትሄ ጥቆማዎችም ቀርበዋል። ጽሁፉ በተከታታይ ክፍሎች የተሰናዳ ነው። ሌሎቹን የክለቦቹን ተግዳሮት በክፍል ሁለት እንመለከታለን:: ስለ
ፀሀፊው፦ ዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ በአሜሪካ ሜሪላንድ ታውሰን ዩኒቨርስቲ የስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ እንዲሁም በጀርመን ሙኒክ ቢዝነስ ስኩል የ5 ዶክትሬት ተማሪዎች አማካሪ ናቸው። ዶ/ር ጋሻው በስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ዙሪያ በርካታ መፅሀፍትን የፃፉ አለም አቀፍ ተቋማትን የሚያማክሩና የሚያስተምሩ ምሁር ናቸው። እስካሁን 10 መፅሀፍትን አሳትመዋል። በስፖርት ማኔጅመንት ላይ ያተኮሩ ከ100 በላይ የሳይንሳዊ ምርምር የህትመት ውጤቶችን ለአንባቢዎች አቅርበዋል።




