ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ዘላቂ ለውጥ፡ ክለቦችን ወደ ህዝባዊነት ማሸጋገር እና የፈቃድ አሰጣጥ መመሪያን ማስፈጸም
በዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ ለመሠረት ሚድያ (አራተኛ እና የመጨረሻ ክፍል)
የኢትዮጵያ እግር ኳስን መሰረታዊ ማነቆዎች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች በሚዳስሰው በዚህ ተከታታይ ፅሁፍ ከዚህ በፊት በቀረቡት ሶስት ክፍሎች የሚከተሉት ነጥቦች ተዳሰዋል። እኝህም፦ ክለቦች የአካባቢያዊ መንግስታት (የፋይናንስ) ጥገኛ መሆናቸው፣ የአመራር አደረጃጀት ችግር (የመንግስት እጅ) መኖሩ፣ ተቋማዊ ቁመናቸው ደካማ መሆኑ፣ የበጀት ዕቅድ እና አጠቃቀም ጉድለት መታየት፣ የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነትና ተጠያቂነት መጉደል፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል (አስተዳደራዊ) እጥረት፣ የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር እክል፣ እና የገቢ ምንጮችን መስፋፋት አለመዳበር፣ በሚሉ አንኳር ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው።
እነዚህ እስካሁን የተመለከትናቸው ስምንት አንኳር ነጥቦች፣ የእግር ኳስ ክለቦቻችን ያሉበትን አሳሳቢ ደረጃ ያመላክታሉ። የዛሬው ክፍል አራት (እና የመጨረሻ) ፅሁፍ፣ የሚጀምረው በጥናቱ ከተለዩት ማነቆዎች መካከል ዘጠነኛው ከሆነው ተግዳሮት ይሆናል።
ታዳጊ እና ተተኪዎች ልማት
አብዛኞቹ ክለቦች ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሱት በአንድ የውድድር ዘመን የዋንጫ ወይም የደረጃ ባለቤት ሆኖ ማለፍን እንደሆነ ተሳታፊዎች በስፋት የተጋሩት አተያየት ሲሆን፣ አሰራሩ ከሚያስከትላቸው ተጽዕኖዎች መካከል በረጅም ጊዜ እቅድ ተደረጅተው በታዳጊ እና በተተኪ ተጫዋቾች ልማት ዙሪያ መስራት አለመቻላቸው አንዱ መሆኑ ተጠቁሟል።
በታዳጊ እና ተተኪዎች ልማት ዙሪያ መስራት አድካሚ እና የልማቱን ፍሬ ለማየት ጊዜ እንደሚወስድ ብዙዎቹ ቢያምኑበትም፣ ልማቱ ሊያስገኛቸው ከሚችላቸው ፋይዳዎች መካካል፦ የሚታየውን የደሞዝ ቀውስ ማርገብ፣ የውጭ ተጫዋቾችን ጫና መቅረፍ፣ ብሄራዊ ቡድንን ተስፋ ባላቸው ተጫዋቾች ማገዝ፥ የሚሉት ጠቀሜታዎች በበርካታ የጥናቱ ተሳታፊዎች የተጋሩ እይታዎች ናቸው። እኝህ ጠቀሜታዎች ካላቸው ብሄራዊ ፋይዳ ባሻገር፣ ለዘለቄታዊ ዕድገት የጎላ አስተዋጾ እንደሚኖራቸው ተሳታፊዎች አበክረው ገልጸዋል። በጥናቱ እንደተሳታፉ የባለ ድርሻ አካላት እይታ፣ የጠነከሩ ክለቦች፣ የጠነከረ ሊግ፤ የጠነከረ ሊግ፣ የጠነከረ ብሄራዊ ቡድን ለማስገኘት እንደሚያስችል በመግለጽ፣ በርካቶች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለአገሪቷ እግር ኳስ የበለጠ አስተዋፅኦ እንዲኖረው ለማስቻል፣ ክለቦች ለታዳጊ ተጫዋቾች እድል የሚሰጡበት መስፈርት ተቀርጾ ሊቀርብላቸው ይገባል፣ ሲሉ በመፍትሄ ሃሳብነት አቅርበዋል። የጥናቱ ተሳታፊዎችን እይታ በሚያንጸባርቅ መልኩ፣ አንድ አሰልጣኝ የሚከተለውን አጋርተዋል፦
"እግር ኳስ የ10 እና የ15 ዓመት ስራ ነው። በአንድ አመት የሚመጣ ለውጥ የለም። ነገር ግን፣ ተተኪ ማፈራት የክለቦች ግዴታ ሊሆን ይገባል። በእኛ አገር፣ ሃምሳ ሚሊዮን ብር ተመድቦ የፖለቲካ ተሿሚ ክለቡን እንዲመራ ይደረጋል፣ ተሿሚው የሚያስፈጽመው የአካባቢውን ፖለቲካዊ ፍላጎት እንጂ፣ ክለቡን እንዴት አድርጌ ላሳድገው፣ ሜዳውን መቼ ማስገባት እንደሚቻል ልንቀሳቀስ፣ ታዳጊዎችን እንዴት ላደራጅ፣ ወዘተ የሚል አይደለም። በወጣቶች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት፣ በረጅም ጊዜ የሚወጣን ወጪ በእጅጉ ይቀንሳል። ነገር ግን ራዕይ ያለው አመራር ያስፈልጋል። ሞያውን የሚያውቅ ሲሆን፣ ግብ ማስቀመጥ ይችላል፣ ግቡን ይዞ የመንግስት አመራርን ማሳመን ይችላል" ብለዋል።
በመፍትሄ ሃሳብነት ከቀረቡት ምልከታዎች መካከል ውድድሮችን ማስፋፋት፣ አካደሚዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ ፌዴሬሽኑ እና ሊጉ በትብብር በልማቱ ዙሪያ መስራት፣ የክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያን በአግባቡ መተግበር የሚሉ ይገኙበታል። እኝህን በተለያዩ የጥናቱ ተሳታፊዎች የተጋሩ ምክረ ሃሳቦች፣ በጥናቱ የተሳተፉ አንድ መምህር ያካፈሉበት ምልከታ ሰብሰብ አድርጎ ያቀርበዋል፦
"[የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ]፣ 16 ክለብ ይዞ ራሱን ለችግር ከማጋለጥ ይልቅ የጠሩ 8 ወይም 10 በክለብ ፈቃድ መመሪያ ላይ የተቀመጠውን የታዳጊዎች ልማት መስፈርትን የሚያሟሉ ክለቦችን ይዞ መጓዙ ይመረጣል። የፈቃድ አሰጣጥ መመሪያው መፈጸሙ ራሱ ክለቦች የታዳጊ እና የሴቶች ክለቦች እንዲኖራቸው ያስችላል። ላሉት ታዳጊዎችም፣ ውድድሮችን ማብዛት እና ማስፋት ያስፈልጋል ከ23 ዓመት በታች ላሉ ታዳጊዎች። ለዚህም፣ የእግር ኳስ ፌደሬሽንና ሊግ ካማፓኒው በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ውድሮች ዙሪያ የሚኖራቸው የስራ ግንኙነት ሊጠናከር ያስፈልጋል። ክለቦች ደግሞ በትክክለኛው የእድሜ ክልል ያሉ ተጫዋቾችን ማፍራት አለባቸው፣ መዋቅራዊ አደረጃጀታቸውም የግድ መስተካከል አለበት”፤ ብለዋል።
ከታዳጊዎች ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የሴቶችን ውድድሮች በሚመለከት፣ የተወሰኑ ተሳታፊዎች እይታቸውን ያካፈሉ ሲሆን፣ የሴቶች ወድድር በአለም ዓቀፍ ደረጃ በልማት ስር እየተተገበረ እንደሚገኝ እይታቸውን ያካፈሉት ተሳታፊዎች ጠቁመው፣ ፌዴሬሽኑ በመስኩ እንዲሰማራ ጠይቀዋል። በርግጥ፣ የጥናቱ ተሳታፊዎች እንዳመለከቱት፣ ፊፋ ‘የሴቶች እግር ኳስ ልማት ፕሮግራም’ የሚል አዲስ መርሃ ግብር እ.ኤ.አ. በመስከረም 2020 ጀምሯል፡፤ በዚህ ፕሮግራም፣ የሴቶች ሊግ ለማከናወን ለሚፈልጉ የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ጠይቋል
ምክረ ሃሳብ፦ ክለቦች በታዳጊ እና ተተኪ ተጫዋቾች ላይ ኢንቨስት ማድረጋቸው፣ የመንግስት የፋይናንሰ ድጋፍ ሊቀንስ በሚችልባቸው ወቅቶች ጫናን ለመቆጣጠር ወይም የመንግስት የፋይናንሰ ድጋፍ ቢቋረጥ ህዝብ ውስጥ ገብተው ለመትረፍ ያግዛቸዋል። ለዚሁም፣ እንደ ምሳሌ፣ ፕሪሚየር ሊጉ ከንግድ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር እና የራሱን ገንዘብ ኢንቨስት አድረጎ በጋር ሃብት የሚተዳደር የታዳጊዎች አካዳሚ እንዲከፍት ይመከራል። “ሐለመ አካዳሚ”በሚል በተባባሪ የንግድ ኩባንያዎች ስም አካዳሚዎቹ ሊጠሩ ይችላሉ። ለጥቆማ ያህል፣ በሚከተሉት የኢኮኖሚ ሴክተሮች የሚንቀሳቀሱ ኩባኒያዎች በተለያዩ አገሮች በተመሳሳይ ትብብር ሲሳተፉ ይስተዋላል። እነዚህም፦ አየር መንገድ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ባንኮች፣ ኢንሹራንስ፣ ቢራ እና ለስላሳ መጠጥ አምራቾች፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ የሲሚንቶ እና ጎማ አምራቾች፣ ሆቴሎች፣ የበይነመረብ እና የስልክ አገልግሎቶች፣ ኮንስትራክሽን እና ሪል እስቴት፣ እና የመኪና አምራቾች ናቸው። እንደተጓዳኝ አማራጭ፣ ፕሪሚየር ሊጉ ሲድ ፈንድ በማዘጋጀት ከግል ኢንቨስተሮች ጋር በመተባበር የታዳጊዎች ልማት /youth development/ አካዳሚዎችን መክፈት ሌላው አማራጭ ነው። በዚህ ረገድ በርካታ በተሞክሮነት የሚነሱ አካዳሚዎች ሲኖሩ ከነዚህ መካከል የባርሴሎና አካዳሚ፣ ሳውዝሃምፕተን አካዳሚ እና ማንቸስተር ዩናይትድ አካዳሚ መጥቀስ ይቻላል።
የተሟሉ የመለማማጃ ሜዳዎች እና ስቴዲየሞች
የተሟሉ የመለማማጃ ሜዳዎች እና ስቴዲየሞች እጥረት፣ ለሊጉ ስኬታማነት ማነቆ ከሚሆኑ ነባራዊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ መሆኑ በስፋት ተነስቷል። በበርካታ የጥናቱ ተሳታፊዎች በአንክሮ የተመከረው፣ ከተሞች ከህዝብ ትብብር ጋር አቅምን ያገናዘቡ የመጫዎቻ ሜዳዎችን መገንባት እንዳለባቸው ነው። የተወሰኑ ተሳታፊዎችም፣ አላማውን ለማሳካት የክለቦች የፈቃድ አሰጣጥ መመሪያን መተግበር ሁነኛ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለመለማማጃ ሜዳዎች እና ስቴዲየሞች ግንባታ መጉደል ምክኒያት እንደሆኑ የተነሱ በርካታ ምክኒያቶች ሲኖሩ በተደጋጋሚ ከተጠቀሱት መካከል፡- በስቴዲየም ግንባታ ዙሪያ የግንዛቤ እና የአስተሳሰብ ክፍተት መኖሩ፤ የመለማማጃ ቦታዎች እና ስታዴየሞች ለስፖርቱ ልማት ያላቸውን ዋጋ በአግባቡ ያለመረዳት፣ እና የተጫዋቾች አካላዊ ብቃት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በአግባቡ ያለመገንዘብ የሚሉት ይገኙበታል።
እኝህን በተደጋጋሚ በጥናቱ ተሳታፊዎች የተነሱ እይታዎችን በሚወክል መልኩ አንድ የክልል የስፖርት ኮሚሽነር የሆኑ ተሳታፊ የሚቀጥለውን አካፈለዋል፦
"የኢትዮጵያ ክለቦች ማለት የረባ ቤት ሳይኖራቸው ቅንጡ የቤት እቃ የሚገዙ ናቸው። የረባ መለማመጃ ሜዳ ሳይኖራቸው በሚሊዮኖች ለተጫዋቾች የሚከፍሉ ናቸው። በሌላ አገላለጽ፣ አንድ ማህበረሰብ ልጆቹን ትምህረት ቤት ሳይልክ፣ ከዛ ማህበረሰብ የተማረ ሰው እንደመጠበቅ ማለት ነው። ... ያለ መለማማጃ ሜዳዎች እና ተጓዳኝ መሰረት ልማቶች አንድ ቡድን የተሟላ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለማሳየት አይችልም። አንድን ስፖርት፣ ስፖርት የሚያደርገውም መሰረተ ልማቱ ነው። ከብሄራዊ ቡድናችንም ቢሆን ውጤት የምንጠብቀው መጀመሪያ ታዳጊዎችን ሊያፈሩ የሚችሉ ሜዳዎች እና አደረጃጃቶች ስንዘረጋ ነው። ... ያልዘራኸውን አታጭድም፣ እና ሊጉ አቅጣጫ ማስያዝ የሚችልበት ቦታ ላይ ነው ያለው" ብለዋል።
በተመሳሳይ፣ በስቴዲየም ግንባታ ዙሪያ የተዛነፈ አረዳድ መኖሩን በርካቶች ያነሱት ሲሆን የብዙዎቹ ተሳታፊዎችን ሃሳብ በሚያንጸባርቅ መልኩ አንድ አሰልጣኝ እንደሚከተለው እይታቸውን አካፍለዋል፦
"[ሠረሸ] ከተማ ስቴዲየምን ብታይ ብዙ ገንዘብ ወጥቶበታል፤ ግን አላለቀም። ነገር ግን እስካሁን የወጣበት ገንዘብ ሁለት ካፍ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች የሚያሟሉ ስቴዲየሞችን ማሰራት ይችላል። ችግሩ ስለ ስቴዲየም ያለው የግንዛቤ እና የአስተሳሰብ ክፍተት ነው። ስቴዲየም ሲባል ግዙፍ ስቴዲየም መሆን የለበትም። አቅምን ያመጣጠኑ ስቴዲየሞች ሁሉም ክለቦች መገንባት ይችላሉ። ልምድ ለማየት አውሮፓ መሄድም አያስፈልግም፣ ሩቅ ሳይኬሄድ፣ ጎረቤት አገር ሱዳን ያሉ እነ አል ሜሪክ፣ አል ሂላል ያሏቸውን፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ያሉ የመለማመጃ ሜዳዎችን ማየት ይረዳል" ሲሉ እይታቸውን አካፍለዋል።
በመፍትሄ ሃሳብነት ከቀረቡት ምልከታዎች መካከል የክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያን መተግበር በአጽዕኖት የተነገረ ሲሆን፣ በጥናቱ የተሳተፉ አንድ መምህር ያካፈሉት ምልከታ ምክረ ሃሳቡን ሰብሰብ አድርጎ ያቀርባል፦
“የኢትዮጵያ ክለቦች ያሉበት ደረጃን ለመመዘን በክለብ ላይሰንሲንግ እንኳ ማንዳቶሪ / አስገዳጅ/ የሆነውን የመጫወቻ ሜዳ ያለሟሉ መሆናቸውን ማየት ይበቃል። ሊጉም መስፈርቶችን እንዲሟሉ የማድረግ አቅሙም ብቃቱም አለው። በጊዜ ሂደትም ተጠያቂነቱ ወደ አክሲዮን ማህበሩ መምጣቱ አይቀርም። የመመሪያውን መስፈርቶች ደረጃ በደረጃ ማሟላት የግድ ይላል” ሲሉ የችግሩን ጥልቀት ገልጸዋል።
ምከረ- ሃሳብ፦ በስታዲየም ግንባታ ዙሪያ አስቀድሞ መቀረፍ ያለበት የተዛነፈ አመለካከት ነው። የጥናቱ ቃለ-መጠይቅ ተሳታፊዎች እንዳመላከቱት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ስቴዲየም የሚለው ጽንሰ ሃሳብ እጅግ ግዙፍ ግንባታ ከሚል እይታ ጋር በቅርበት የተቆራኘ መሆኑን ነው። ነገር ግን፣ ሊጤን የሚያስፈልገው ጉዳይ የተለያዩ አይነት እና ለተለያዩ አላማዎች የሚውሉ ስቴዲየሞች መኖራቸውን ነው። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው፣ በሰሜን አሜሪካ ያሉ አነስተኛ የእግር ኳስ ሜዳዎችን መመልከት ይረዳል። በስቴዲየሞች ዙሪያ በአገሪቷ ውስጥ ያለውን የተዛነፈ ግንዛቤ ማስተካከል፣ ውሳኔ ሰጭዎች ላይ የሚኖረውን ጫና በመረጃ ላይ የተንተራሰ እንዲሆን በማገዝ፣ ክለቦች አቅማቸው የሚፈቅደውን የራሳቸውን ወይም የከተማቸውን ስታዲየም በተወሰነ አመት ውስጥ የመገንባት እድላቸውን ተስፋ ሰጪ ብሎም ተግባራዊ ያደርገዋል።
መቀረፍ ካለበት የተዛነፈ ግንዛቤ ጎን ለጎን ሊታሰብ የሚጋባው የስቴድዮም ግንባታ በተለያየ መልኩ ሊደገፍ እንደሚችል ነው። በዚህ ረገድ፣ በተለያዩ አገሮች እንደሚተገበረው ለስታዲየም ግንባታ የሚሆን ገንዘብ የሚሰባሰብባቸው መንገዶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ ለረጀም ጊዜ የሚቆይ የስታዲየም ስም መጠሪያን መሸጥ፣ የስታዲየም መቀመጫ የባለቤትነት ሽያጭ፣ የግንባታ የባለቤትነት አክሲዮን ሽያጭ (ብሎም፣ ስታዲየሙ ከሚያገኘው ገቢ ባለአክሲዮኑ ተጠቃሚ መሆን)፣ የስታድየም የተለያዩ ክፍሎችን ለተለያዩ ድርጅቶች መሸጥ (የዳላስ ካው ቦይስ ልምድ)፣ ስቴዲየሞች ከተገነቡ በኋላ ለተለያዩ ዝግጅቶች ማከራየት፣ በዙሪያው ያሉ ክፍሎች ለንግድ ድርጅቶች በሊዝ ገቢ የሚያስገቡበት መንገድ መቅረጽ የሚሉ ይገኙበታል
ማጠቃለያ
የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ:- የኢትዮጵያ ክለቦች ችግር በጥሞና ሲጤን ዞረው የሚያርፉት የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ መስፈርቶች ላይ ነው። ከሰው ሃይል እስከ መሰረተ ልማት እስከ ፋይናንሰ አስተዳደር እስከ ስፖርታዊ ጉዳዮች እና ህግ ነክ ጉዳዮች ድረስ፤ ክለባት የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ መስፈረቶች እንዲያሟሉ መጫን ለእግር ኳሱ እድገት ቁልፍ መፍትሄ ነው። የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ መስፈርቶች ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ሰው ሃይል ብቃት፣ ፋይናንስ አያያዝ እና ተጠያቂነት፣ መለማመጃ እና መጫወቻ ሜዳ፣ ህጋዊ ተቋምነት፣ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን ለእግር ኳሱ እድገት ቁልፍ መፍትሄው የክለቦችን ላሰንሲንግን በአግባቡ ማስፈጸም እንደሆነ በዚህ ጥናት ድምዳሜ ላይ መድረስ ተችሏል። በመሆኑም፣ የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ያለውን ዘርፈ ብዙ እና ዘላቂ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለተግባራዊነቱ ለእግር ኳሱ አመራር ሃላፊነት ያለበት አካል መትጋቱ የእግር ኳስን እድገት በተሻለ መሰረት ላይ ማኖር ነው። በአጭሩ፣ የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያው መስፈርቶችን ማሟላት ለክለቦች ዘላቂ እድገት ቁልፍ መፍትሄ ነው። የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያውን ማስፈጸም ለዘላቂ እድገት ቁልፍ መፍትሄ ሆኖ ለተግባራዊነቱ የሌሎች የባለድርሻ አካላትን እገዝ ማግኘት የግድ ይለዋል። የብሄራዊ ፌዴሬሽኑን እና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፉን ድጋፍ ሊያገኝ ይገባል።
ክለቦችን ወደ ህዝባዊነት መቀየር:- ሌላው ጥቅል ምልከታ፣ ክለቦችን ወደ ህዝባዊነት መቀየር ነው። ክለቦችን ወደ ህዝባዊነት ለመቀየር እና ለተፈጻሚነቱ የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ እና በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ድጋፍ ማግኘቱ የግድ ይላል። በተለይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ፣ የአገሪቷ ህግ ብሎም የብሄራዊ ስፖርት ፓሊሲው የሚያዘውን የክለቦች አደረጃጀት ለመተግበር ትክክለኛው የመንግስት አካል በመሆኑ፣ የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ሙሉ ድጋፍ መኖር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ እንደየጥናቱ ተሳታፊዎች ምልከታ፣ መንግስት ለክለቦች እያደረገ ያለው የገንዘብ ድጋፍ ለዜያዊ ቁመና ፋይዳ ያለው ቢሆንም፣ እግር ኳሱን አስተማማኝ፣ ጠንካራ፣ እና ዘላቂ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ ክለቦች በህዝብ ባለቤትነት ይዞታ ላይ የተመረኮዘ አደረጃጀት እንዲያገኙ መደረጉ በጥናቱ ተሳታፊዎች በሰፊው፣ በተደጋጋሚ፣ እና በአጽዕኖት የተነሳ ምክረ ሃሳብ ነው። በተያያዘም፣ ለውጡ መተግበሩ፣ የክለቦች ተቋማዊ ህልውና እና እጣ ፋንታ ከመንግስት አመራሮች ፍላጎት እና ይሁንታ ተላቆ፣ በራሳቸው በበቁ ተቋማት ጥምረት የሚገነባ ሊግ ለማደራጀት እንደሚያስችል የባለ ድርሻ አካላቱ አመላክተዋል። ልብ እንዲሉ፣ የክለቦች የህዝባዊ አደረጃጀት ይዘት መያዝ ለጥቂት ክለቦች የሚተው ሳይሆን፣ ከሁሉም ሊጉን የሚቀላቀሉ ክለቦች የሚጠበቅ መሆን አለበት። ለዚሁም፣ የተወሰኑት በመንግስት በጀት ድጎማ የተጫዋቾችን ደሞዝ የሚያንሩበት እና ሌሎች የህዝባዊ ክለብ መሰረት ይዘው በመጓዝ ዘላቂ ስኬት ላይ አተኩረው እንዲሰሩ መጠበቅ ፈታኝ እንደሚሆን ተደጋግሞ ተጠቁሟል። የክለቦች ህዝባዊ መሆን ሌላው ጠቀሜታው፣ ክለቦች ከስፖርቱ እድገት ጋር የተመጣጠነ፣ ገቢያው የሚፈቅደው፣ እና አቅማቸውን የሚመጥን እውነተኛ ክፍያ ለተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የሚያቀርቡበት የፋይናንስ ግልጽነት እና የወጪ ተጠያቂነት መፍጠር ያስችላል። እንዲሁም፣ በአለው አካሄድ፣ ክለቦች የመንግስት በጀት ጥገኛ መሆናቸው አማራጭ ገቢ ምንጭ ማግኛ ዘዴዎችን እንዳይፈይዱ ስለሚያደርጋቸው፣ ወደ ህዝባዊነት መቀየራቸው በክለቦች የዕለት ተለት ስራ የተሰማሩ ሰራተኞች ዘንድ መነሳሳት እና ፈጠራ የታከለበት የአሰራር ስርዓት የመፍጠር ሃይል መኖሩ እና ራሳቸውን በዘላቂነት ለማቆየት የገቢ ምንጭ የማስፋፊያ ስራ ለመስራት ያነሳሳል።
በመጨረሻ፦ በተከታታይ ፁሁፎቹ የተዳሰሱስት ተግዳሮቶች እንዳሉ ሆነው በአለፉት 6 ዓመታት ችግሮቹን ባለው አቅም ለመፍታት ለሞከረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አድናቆት ሊቸረው ይገባል። እንዲሁም ፕሪሚየር ሊጉ እንዲጀመር ያስቻሉት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እና ፕሬዚደንቱ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከአለበት ችግር ወጥቶ እንዲለማ በዚህ ተከታታይ ፁሁፉ የቀረቡት እና ሌሎች ተጓዳኝ ተግዳሮቶች ሙሉ በሙሉ ሊቀረፉ ይገባል። ዋነኛ መፍትሄውም ለለውጥ ክፍት የሆነ አተያየት መኖር እና ቁርጠኝነት ነው።
ስለ ፀሀፊው፦ ዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ በአሜሪካ ሜሪላንድ ታውሰን ዩኒቨርስቲ የስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ እንዲሁም በጀርመን ሙኒክ ቢዝነስ ስኩል የ5 ዶክትሬት ተማሪዎች አማካሪ ናቸው። ዶ/ር ጋሻው በስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ዙሪያ በርካታ መፅሀፍትን የፃፉ አለም አቀፍ ተቋማትን የሚያማክሩና የሚያስተምሩ ምሁር ናቸው። እስካሁን 10 መፅሀፍትን አሳትመዋል። በስፖርት ማኔጅመንት ላይ ያተኮሩ ከ100 በላይ የሳይንሳዊ ምርምር የህትመት ውጤቶችን ለአንባቢዎች አቅርበዋል።




