አስቸኳይ ፓስፖርት ለማውጣት በአማራጭነት በአካል መስተናገድ ተጀምሯል ከተባለ በኋላ ምን ለውጥ አለ?
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን የዛሬ ሳምንት ገደማ የሰራውን አንድ የምርመራ ዘገባ ተከትሎ አዲስ አበባ ያለው ዋናው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ለአስቸኳይ ፓስፖርት አመልካቾች አዲስ አሰራር ይፋ አድርጎ ነበር፣ ይህም በኦንላይን ብቻ የነበረውን የአዲስ አስቸኳይ ፓስፖርት አገልግሎት በአካልም እንዲሆን ማድረግ ነበር።
በአንዳንድ የተቋሙ ሰራተኞች እየተፈፀመ ያለውን የሙስና ወንጀል በሚድያችን መጋለጥ ተከትሎ ተቋሙ ይህን እርምጃ በይፋ ቢያሳውቅም አሁን ላይ ኦንላይን አልሰራ ብሏቸው በአካል እየሄዱ ያሉ ዜጎች ድብደባ እና እንግልት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ያደረግነው ክትትል ያሳያል።
"በአካል ብትመጡ ትስተናገዳላችሁ ብንባልም ዛሬ አንሰራም ብለው አባረውናል፣ ማባረር ብቻ ሳይሆን በፀጥታ አካላት ዱላም አርፎብናል" ብላ ለመሠረት ሚድያ የተናገረችው አንድ ግለሰብ ናት።
ሌላኛው ተስተናጋጅ ደግሞ "በአካል አስቸኳይ የፓስፖርት ምዝገባ እንዳለ ኢሚግሬሽን ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር፣ ነገር ግን ስንመጣ መግባት አትችሉም ተብለን ሰልፉን በተኑት። ለሊት ነበር የመጣነው እናም ውስጥ ሰው አለ ይሰራላችኃል ተብለን የውሸት ደረሰኝ ተሰቶን 50 ሺህ ብር ከተቀበሉን በኋላ ስልክ አያነሱም፣ ለሌቦች ተጋልጠናል" በማለት የተዳረጉበትን ተጨማሪ ኪሳራ ከነማስረጃው አቅርበዋል።
"140 ቁጥር በሚባል የቢሮ ቁጥር ነው ይህ የተደረገው፣ ኢሚግሬሽኑ ማስታወቂያ አውጥቶ ህዝቡን በአግባቡ ባለማስተናገዱ ይበልጥ በተደራጁ ሌቦች እንድንዘረፍ ተደረግን፣ 50ሺ ብራችንን ተዘርፈን ተመለስን" በማለት ያጋጠማቸውን አጋርተዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዛሬ በዚህ ዙርያ ባወጣው አንድ አጭር መግለጫ "የአስቸኳይ ፓስፖርት ኦንላይን ሲስተም የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጎበት ስራ የጀመረ በመሆኑ ከነገ ጀምሮ ሁሉም አመልካች በኦንላይን በማመልከት በቀጠሮ ቀናችሁ ብቻ ወደ ተቋማችን በመምጣት እንድትስተናገዱ እናሳስባለን" ብሏል።
አክሎም "በኦንላይን መሙላት ያልቻላችሁ አስቸኳይ ጉዳይ ያላችሁ አመልካቾች በአካል መጣችሁ መስተናገድ የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን። ከቀጠሮ ቀናችሁ ውጭ በተቋሙ አካባቢ መቆምም ሆነ አላስፈላጊ እንቅስቃሴ ማድረግ በጥብቅ የተከለከለ ነው" ብሎ በፌስቡክ ገፁ አሳውቋል።
አሁን ማስተካከያ ተደረገበት የተባለው የኦንላይን ሲስተም በአድሚኖቹ በኩል በሚደረግ መመሳጠር ደላሎች ጭምር ተሳትፈውበት እንደሚሰራ የመሠረት ሚድያ ምርመራ ማጋለጡ ይታወሳል።
መረጃን ከመሠረት!




May 19 እስካሁን ሲስተም እየሰራ አይደለም ደላላ ብቻ እንዲሰራ ነው የተፈለገው
May 19 እስካሁን ሲስተም እየሰራ አይደለም ደላላ ብቻ እንዲሰራ ነው የተፈለገው