"በነባራዊው ሁኔታ መሬትን ለውጭ ዜጎች መፍቀድ ተጨማሪ ቤንዚን አርከፍካፊዎችን ከባህር ማዶ መጥተው እንዲቀላቀሉ መፍቀድ ነው"
በምጣኔ ሃብት ባለሞያው አቶ ውዱ ወርቁ ለመሠረት ሚድያ የተላከ
(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀፅ 40 (3) ''መሬት የመንግስትና የህዝቦች ነው'' ይላል። ሀገሬው ወይም ህዝቡ ደግሞ መሬት (ገንዘብ) የደም ስር ነው ይላል። በኢኮኖሚክስም መሬት አንዱ የምርት ምክንያት ነው ይባላል።
ቤት ለመስራት፣ ማዕድናትን ለማውጣት፣ አርሶ ለመብላት (ለግብርና ስራ)፣ ለደን ልማት ወዘተ መሬት ወሳኝ ሃብት ነው። ለኢኮኖሚ እድገት እንደ ቁልፍ መሣሪያ ከምንጠቀምበት አንዱ የመሬት ሃብት ነው።
ይህ ውስን የሆነው የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ተጠብቆና ለምቶ የልማት ቁልፍነቱን እንዲያረጋግጥ የመንግስት የመሬት ፖሊሲ ወሳኝነት አለው። በኢትዮጵያ መሬት ለመንግስትና የህዝቦች ነው የሚለው አደገኛ አገላለፅ ውስን የሆነውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀም እንዳይቻል ጠርፎ የያዛ አሳሪ ህግ ይመስለኛል።
የመንግስት ካድሬዎች በፈለጉ ጊዜ እንዲቸበችቡት የፈቀደላቸው፣ ግለሰቦች መሬትን ከመጠቀም በስተቀር የመሸጥ መለወጥ፣ አስይዞ የመበደር መብትን የከለከለው ህገ መንግስትና የሊዝ አዋጅ መሬት የልማት መፍጠሪያ መሳሪያ ከመሆን ይልቅ የግጭት መንስኤ እንዲሆን አድርጎታል።
በሃገሪቱ ለሰፋው የኢኮኖሚ ኢ-ፍትሃዊነት አባባሹና መነሻውም የመሬት ፖሊሲውና የፖሊሲው አተገባበር ችግር ያለበት መሆኑ ነው። አብዛኞቹ የአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካንና ከፊል የእስያ ሀገራትን ጨምሮ መሬት የግለሰብ እንዲሆን ይፈቅዳሉ።
የዲሞክራሲ ስርዓትን የሚያቀነቅኑ፣ በአለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ የፖሊሲ ተፅኖ ስር የወደቁ ሃገራትም መሬትን ጨምሮ የግል መር የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲከተሉ ይገደዳሉ። በአንፃሩ እንደ ቻይና ያሉ ኮሚኒስት ሃገራት መሬት የጋራ ሃብት እንደሆነና ዜጎች በረጅም ጊዜ ሊዝ እንዲጠቀሙ ብቻ የሚያስገድድ ህግ አላቸው።
አንዳንዶች ደግሞ እንደነ ኢንዶኔዥያ፣ ጂዮርጂያ እና የመሣሰሉት ሃገራት የውጭ ዜጎች በሀገራቸው የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ ፍፁም አይፈቅዱም። ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ መሬትን ለመንግስትና ብሄር ብሄረሰቦች ሠጥታለች። የውጭ ዜጋን ቀርቶ ሃገሬውን ከመጠቀም በዘለለ የመሬት ባለቤትነት መብት ትነፍጋለች።
መሬት የህዝቦች ነው የሚለው አገላለፅ የህዝብ ወኪል ነን ለሚሉ የፖለቲካ ጥገኛ ነጋዴዎች ብልፅግና ቁልፍ መሳሪያ ሆኗቸዋል። ከከተማ የመኖሪያ ቦታ እስከ በረሃማ የእርሻ መሬቶች የቀደሙ የብሄረሰብ ወኪል ነን የሚሉ ጩልሌ ነጋዴዎች የመክበሪያ መሳሪያቸው ሆነዋል።
በሃገሪቱ እየሠፋ ለመጣው የህዝቦች የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያቱም የመሬት ፖሊሲው እንደሆነ በብዙ የዘርፉ አዋቂዎች ዘንድ ተደጋግሞ ይነገራል። ወለጋን ለኦሮሞ፣ መተከልን ለቤንሻጉል አዲስ አበባን ባለቤት አልባ አድርጎ የፖለቲከኞች የመሻኮቻ ምክንያት የሆነው ህገ መንግስት ለወልቃይትና ራያ ምላሽ ስላልሰጠ ለበርካታ ህዝብ እልቂት፣ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ገፊ ምክንያትም ሆኖ ይገኛል።
ይሁንና የወለጋን መሬት ወደ ጫካነት፣ የመተከልን የእርሻ ቦታ ወደ ደንነት የወልቃይትና ራያን መሬቶች ወደ ደም መሬትነት የለወጠ ህገ መንግስት ያላት ሃገር እንደ ምን የውጭ ዜጎችን የመሬት ባለቤት ለማድረግ ይቻላታል?
መቼም የአይ ኤም ኤፍና የአለም ባንክ የሚያስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሀገሪቱን ከገጠማት የዶላር እጥረት ጋር ተጨምሮ ካልሆነ በስተቀር እስከ ማውቀው ድረስ ህገ መንግስታዊ ክልከላው በህገ መንግስት ማሻሻያ አልተነሳም። የውጭ ዜጎችን እንደ ኢትዮጵያዊያን በሊዝ የመጠቀም መብት ለመስጠት ብቻ ታስቦ ነው የሚል ምላሽ የሚሰጠው ከሆነም እጅግ አደገኛ የሙስናና በውጭ ሀገር ዜጎች የመወረር እድልን የሚያሰፋ አካሄድ ነው።
የመሬቱን ባለቤት ሳይሆን ደላላውንና የመንግስት ተሿሚውን በሚያበለፅገው የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ መሬትን ለውጭ ዜጎች መፍቀድ በመሬት ምክንያት የግጭት አዙሪት ውስጥ ላለች ሀገር ተጨማሪ ቤንዚን አርከፍካፊዎች ከባህር ማዶ መጥተው እንዲቀላቀሉ መፍቀድ ነው።
ነፃ የኢኮኖሚ ስርዓት የሚሰራው በኢኮኖሚው ውስጥ የሚገቡ የመንግስት ገቢራዊና ስውር እጆችን መቁረጥ ሲቻል እንጂ መርህ በሌለው አንዱን ነስቶ አንዱን በሚፈቅድ የፖሊሲ ስርዓት ውስጥ ተኩኖ አይደለም። ለሁሉም ሀገሪቱ የህገ መንግስት ማሻሻያ አድርጋ መሬት ለግለሰቦች የሚሆንበትን ጊዜ እናፍቃለሁ።
መረጃን ከመሠረት!



