አዲሱን የቴዎድሮስ ካሳሁን ዘፈን ሲያዳምጡ ተገኙ የተባሉ ከመቶ በላይ ወጣቶች አዲስ አበባ ውስጥ መታሰራቸው ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ዘፈን መውጣቱን ተከትሎ ከሚያዚያ 8 ቀን 2018 ዓ/ም ምሽት ጀምሮ የመንግስት የፀጥታ አካላት ባደረጉት አሰሳ የፊታችን ግንቦት ወር የሚካሄደውን ምርጫ ለማስተጓጎል አዲሱን ዘፈን እንደ አመፅ መቀስቀሻ ተጠቅመውበታል በሚል በርካታ ወጣቶች መታሰራቸውን ሚድያችን ሰምቷል።
ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የመንግስት የመረጃ ምንጭ ለመሠረት ሚድያ እንዳረጋገጡት ከትናንት ምሽት ጀምሮ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ የፀጥታ ግብረ-ኃይል በመዲናዋ ሰፊ አሰሳ እያረጉ ይገኛሉ።
"በከተማው ውስጥ በሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች ምን ያህል ተጠርጣሪዎች እንዳሉ እርግጠኛ ባልሆንም በፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ስር ባለው የምርመራ ክፍል ውስጥ ሰማንያ ወጣቶች ታስረዋል" ያሉት ምንጫችን በአዲስ አበባ ፖሊስ በተለምዶ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ደግሞ 25 ወጣቶች በድምሩ 105 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ መሆኑንም አክለዋል።
አብዛኛዎቹ በቅርቡ እንደሚለቀቁ ተስፋ አለኝ ያሉት አንድ የምርመራ ቡድኑ አባል ደግሞ “ዘፈኑን ለአመፅ መቀስቀሻ ለማዋል መሞከራቸው እንጂ መንግሥት ከዘፈኑ ጋር ችግር የለበትም” ብለው ለሚዲያችን ገልፀዋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት አብዛኛዎቹ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ናቸው ያሉት ጠቋሚያችን በዘፈን ስም ለአመፅ ተነስ እያሉ መቀስቀስ ወንጀል መሆኑን ገና ያልተረዱ ልጆች የፈፀሙት ድርጊት ነው ብለዋል።
በዛሬው ዕለት ዛሬ በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተማ በርካታ ወጣቶች እንደታፈሱ በርካታ መረጃዎች ለሚድያችን ደርሰዋል።
"ከቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ጋር በተያያዘ የህዝብ አመፅ እንዳይነሳ በመፍራት ነው የወሰዷቸው። ጎሮ አካባቢ የሚኖረውን አጎቴን ቤቱ ሰተት ብለው ገብተው ነው ይዘውት የሄዱ። ሜክሲኮ አካባቢ ነው ወስደው ያጎሯቸው" በማለት አንድ የከተማው ነዋሪ ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የቴዎድሮስ ካሳሁን ዘፈን ትናንት ከወጣበት ዕለት ጀምሮ ሌሊት በከተማዋ ባልተለመደ መልኩ ረዘም ያለ ፍተሻ ሲካሄድ ማደሩን የመሠረት ሚዲያ ምንጮች ጠቁመዋል።
-መሠረት ሚድያ-


