"በአርሲ ምድር በተደጋጋሚ የሚስተዋለው በደልና ግፍ በሁላችንም ልቡና ውስጥ እስከ መቼ የሚል የቁጭት እና የሐዘን ጥያቄን ፈጥሯል"- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በአርሲ ሀገረ ስብከት ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በምዕመናን እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የደረሰውን አሰቃቂ እና ዘግናኝ ጥቃትን በተመለከተ ይፋዊ መግለጫ አውጥተዋል።
ፓትርያርኩ በመግለጫቸው ላይ "በአርሲ ሀገረ ስብከት በአሴኮ፣ በሸርካ፣ በሙግቶ፣ በበሌ እና በመንዲዳ ወረዳዎች በመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችንና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ስለደረሰው አሰቃቂ ጥቃት የሰማነው በተሰበረ ልብ ነው" በማለት የተሰማቸውን ጥልቅ ገልጸዋል።
ይህ ጥቃት ለዘመናት አብሮ በመኖር እሴት በምትታወቀው አገር ላይ የተፈጸመ ታላቅ በደል መሆኑን በማስገንዘብ በተለይም ታሪካዊ ቅርሶች እና የሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት በተመለከተ "የእምነት ነጻነት ተደፍሮ መቶ ዓመታት ያስቆጠረው የጠለታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በተቃጠለበት፣ እንዲሁም የኮሬ ኪዳነ ምሕረትና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በተዘረፈበት በዚህ ክፉ ቀን፣ በርካታ ምእመናን በግፍ መታረዳቸውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከቀያቸው መፈናቀላቸው ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘነ ክስተት ነው" ብለዋል።
አክለውም የችግሩን ስፋት ሲያብራሩ "የሰላም፣ የፍቅርና የታሪክ ማኅደር የሆነችው ቤተ ክርስቲያን በምድረ በዳ ውስጥ ያሉትን ምእመናን በምታጽናናበት በዚህ ወቅት ራሷ በፈተና ውስጥ ሆና ከመቆዘምም በላይ በአርሲ ምድር በተደጋጋሚ የሚስተዋለው በደልና ግፍ በሁላችንም ልቡና ውስጥ እስከ መቼ የሚል የቁጭት እና የሐዘን ጥያቄን ፈጥሯል" ብለዋል።
በመሆኑም ፓትርያርኩ ለመንግስት እና ለጸጥታ አካላት ባስተላለፉት ቀጥተኛ መልእክት "ይህ መከራ እያበቃ ሳይሆን እየሰፋ በመምጣቱ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅና ሰላምን የማስፈን አደራ የተጣለባችሁ የጸጥታ አካላትና የየደረጃው ኃላፊዎች ከምንም በላይ ታሪክ የሚጠይቃችሁ በሥልጣን ዘመናችሁ ለዜጎች ደኅንነት በምትከፍሉት ዋጋ ነውና ይህንን የጥቃት ሰንሰለት በማስቆምና ወንጀለኞችን ለሕግ በማቅረብ ከታሪክ ባለዕዳነት ትድኑ ዘንድ በቤተ ክርስቲያናችን ስም አጥብቀን እናሳስባለን" ሲሉ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። በመጨረሻም "በየአካባቢው የምትገኙ ምእመናንና መላው ኢትዮጵያውያንም በወንድማማችነት መንፈስ ተጋግዛችሁ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና በጸሎት ከቤተክርስቲያናችን ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን" በማለት አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ይህ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስቸኳይ መግለጫ የወጣው በተለይም በመሠረት ሚዲያ እና በሌሎችም መገናኛ ብዙኃን በአርሲ ዞን በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ተከታታይ ጥቃት በስፋት እየተዘገበ ባለበት ወቅት ነው።
በቅርብ ጊዜያት የወጡት ተከታታይ የመሠረት ሚዲያ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የታጠቁ ኃይሎች በሸርካ፣ መርቲ እና ሌሎችም የአርሲ ወረዳዎች ውስጥ በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠረ እና የተደራጀ ጥቃት በተደጋጋሚ ፈጽመዋል።
የዐይን እማኞችን ጠቅሰው የወጡት ዘገባዎች እንደሚያስረዱት ምዕመናን በገበያ ቦታ ላይ ለግብይት በወጡበት፣ በመንገድ ላይ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ሲጓዙ፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እያሉ፣ እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሃይማኖታዊ አምልኮ በማካሄድ ላይ እያሉ ጭምር ኢላማ ተደርገው በግፍ ተገድለዋል።
በጥቃቱ ዙርያ በመንግስት ሚድያዎች እስካሁን አንድም መረጃ ለህዝብ ያልቀረበ ሲሆን በመንግስት ባለስልጣናትም የተባለ ነገር የለም።
| መሠረት ሚድያ |


