በሚዛን አማን ከተማ በተገነባው አየር ማረፊያ ዙርያ ያሉ ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ይዘው ጎዳና ሊወጡ መሆኑን ተናገሩ
(መሠረት ሚድያ)- በ2014 ዓ.ም በሚዛን አማን ከተማ ለአየር ማረፊያ ግንባታ የቦታ ክለላ ሲደረግ ንብረታቸው ከሚነሳባቸው መካከል የተቆጠሩ ነዋሪዎች እስካሁን ድረስ በቦታው ተጨማሪ ንብረት እንዳናፈራም፣ ያለውንም እንዳናነሳ ተከልክለን ቆይተናል በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።
አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ነዋሪ "2018 ዓ.ም ላይ ሆነን 2014 ዓ.ም በተገመተው የንብረት ግምት የካሳ ክፍያ እንክፈላችሁ ይሉናል፣ ይህ ግምት የብር ዋጋ ከመጋሸቡ በፊት የነበረ ነው" ይላሉ።
መሠረት ሚዲያ የተመለከታቸው የሰነድ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት አንድ ቤት በግቢ ውስጥ ካለው አትክልት ጨምሮ ከ320 ሺ እስከ 450 ሺ ብር ተገምቷል። ሌላኛው ለሚድያችን ቃላቸውን የሰጡ ነዋሪ እንደተናገሩት ከሆነ ከዚህም ያነሰ የካሳ ክፍያ የተገመተላቸው አሉ።
"በ250 ሺ ብር ምን እናደርጋለን፣ በዚህ የኑሮ ውድነት እንኳን ቤት ልንሰራበት ቀርቶ የአመት ኪራይ እንክፈል እንኳን ብንል አይበቃንም" ብለዋል።
በተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀረቡት ነዋሪዎች ተለዋጭ መሬት በማካካሻነት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር፣ ይሁንና የአየር ማረፊያው ማኮብኮቢያና መቆጣጠሪያ ክፍል ግንባታ ሲሰራ ከፊሎቹ ተነስተው ካሳ የተሰጣቸው ሲሆን የተቀሩቱ ግን ካሳውም ምትክ ቦታውም ሳይሰጣቸው ባሉበት እንድትቆዩ የሚል ደብዳቤ ተሰጥቷቸው ቆይተዋል።
አሁን ግን በድንገት የካሳ ክፍያው ተሰጥቶ ባልተጠናቀቀበት እና ምትክ መሬት የተባለው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የነበረ ስፍራ ቆሻሻው ሳይነሳ፣ ጫካውም ሳይመነጠር በዚህ ሰባት ቀን ንብረታችሁን አንስታችሁ ወደ አዲሱ ቦታችሁ ሂዱ ተብለናል ይላሉ ነዋሪዎቹ።
"ማስታወቂያ ተለጥፎ ነው ያየነው፣ አየር ማረፊያው ተመርቆ ሥራ ሊጀምር ነው፣ በዚህ ሰባት ቀን ውስጥ ልቀቁ ተብለናል" ሲሉ ለመሠረት ሚዲያ ተናግረዋል።
ሌላኛው ነዋሪ "ሚዛን አማን የቤት ኪራይ አናገኝም፣ ብናገኝም ውድ ነው፣ ልጆቻችንን ይዘን የት እንድንገባ ነው በሰባት ቀናት ውስጥ ልቀቁ የምንባለው ይላሉ። እስካሁን የካሳ ገንዘባችንም አልተሰጠንም፣ ልጆቻችንን ይዘን ወደጎዳና ልንወጣ ነው" ሲሉ በምሬት ገልፀዋል።
-መሠረት ሚድያ-



