በእጮኛው ሞት ተጠርጥሮ እስር ላይ የነበረው አርቲስት አንዱአለም ጎሳ ማምሻውን በዋስ መፈታቱን ጠበቃው ተናገሩ
(መሠረት ሚድያ)- አርቲስት አንዱአለም ጎሳ በእጮኛው ቀነኒ አዱኛ ሞት ተጠርጥሮ ከመጋቢት 2/2017 ዓ/ም ጀምሮ እስር ላይ ይገኝ እንደነበር ይታወሳል።
አርቲስቱ ዛሬ ማምሻውን በ50 ሺህ ብር ዋስ ተለቆ ወደ ቤቱ እንደገባ ጠበቃው አቶ ሊበን አብዲ ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
አቶ ሊበን ለፌደራል የመጀመርያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አንደኛ ደረጃ ችሎት ያቀረቡት አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ተቀባይነት አግኝቶ አርቲስቱ በዋስ መውጣቱን ተናግረዋል።
"ዛሬ አመሻሹን 11 ተኩል ገደማ ተለቋል። አቃቤ ህግ በተሰጠው 15 ቀናት ውስጥ ክስ መመስረት አልቻለም፣ ይሁንና ደንበኛዬ ከቅዳሜ ጀምሮ እስር ላይ ቆይቷል። ስለዚህ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ መስርተን በዋስ ተለቋል" በማለት ጠበቃው ለሚድያችን ተናግረዋል።
የአርቲስቱን መለቀቅ ተከትሎ አሁን የአቃቤ ህግን ውሳኔ እየጠበቁ መሆናቸውን ጨምሮ ገልጿል።
የድምጻዊው አንዱአለም ጠበቃ ከዚህ በፊት “ቀነኒ በርካታ ጊዜ ራሷን ለማጥፋት መሞከሯን ከማስታወሻዋ ላይ ተገንዝቤያለው” ብለው ነበር። ይሁንና ይህ አባባል በርካቶችን ጥርጣሬ ላይ የጣለ ሆኖ ቆይቷል።
ሚድያዎች የአንዱአለም ጎሳን ጉዳይ ለመዘገብ ችሎት እንዳይገቡ የተከለከሉ ሲሆን በምክንያትነት የተቀመጠውም የተሳሳተ መረጃ እያሰራጩ ነው የሚል ነበር።
ከዚህ በፊት ዐቃቤ ሕግ መረጃዎችን ለማደራጀትና የምርመራ ውጤቶችን ለማቅረብ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎቹን እንዲያቀርብ መዝገቡን ለምርመራ ለሚያዚያ 9 ቀን 2017 ተቀጥሮ እንደነበር ይታወሳል።
በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ሰንሻይን ቤቶች ፊት ለፊት ከሚገኘው ውዳሴ ህንፃ ላይ ነዋሪ የነበረችው ሟች ወ/ሮ ቀነኒ አዱኛ ዋቆ መጋቢት 01 ቀን 2017 ዓ/ም ከሌሊቱ 10፡00 ሠዓት አካባቢ ከቤቷ የማብሰያ ክፍል በኩል ካለው በረንዳ 5ኛ ፎቅ ላይ ወድቃ ተገኝታ ለህክምና እርዳታ ወደ ያኔት ሆስፒታል እየተወሰደች ባለበት ወቅት ህይወቷ ማለፉ ይታወሳል።
ቀነኒ አዱኛ በወቅቱ ከበረዳ ላይ በወደቀችበት ሰዓት ፖሊስ በቤቱ ውስጥ የነበረውን ባለቤቷን ድምፃዊ አንዷለም ጎሳን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ ሲያረግ ቆይቶ ነበር።
መረጃን ከመሠረት!



