ሶስት ቻይናውያንን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በዛሬው እለት ከፋብሪካ ውስጥ ታግተው ተወሰዱ
(መሠረት ሚድያ)- የእገታ ወንጀል ከእለት ወደ እለት እየጨመረ እንደሚገኝ መረጃዎች ቢያሳዩም በመንግስት አካላት ደግሞ የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ እጅግ እየተሻሻለ እንደሚገኝ ይገለፃል። የእገታ ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ ከተንሰራፋባቸው ክልሎች አንዱ ኦሮሚያ ነው፣ ዛሬ ከክልሉ የደረሰን መረጃም ይህን ያጠናክራል።
ዛሬ ግንቦት 29 2017 ዓመተ ምህረት ከጠዋቱ 2 ሰአት ገደማ ከጫንጮ ከተማ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ደርባ ሲሚንቶ መሄጃ ሙሎ መገንጠያ ሳይደርስ የሚገኘው ሰዮ ሀይላንድ ፋብሪካ ውስጥ ያሉ በርካታ ሰራተኞች መታገታቸውን መሠረት ሚድያ አረጋግጧል።
ሶስት ቻይናውያንን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች መታገታቸውን የሰማን ሲሆን አጋቾቹም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ወይም መንግስት ኦነግ ሸኔ የሚላቸው እንደሆኑ የአካባቢው ምንጮች ጠቁመውናል።
ይህ ሁሉ ሲሆን የኦሮሚያ ልዩ ሀይል አልታዘዝንም በማለት ከሩቅ ሲያዩ ነበር ያሉት ምንጮቻችን ድርጊቱ በርካታ የአካባቢውን ሰው እንዳስደነገጠ እና እንዳሳዘነ ተናግረዋል። ደርባ አካባቢ ደርሶ የመጣ እና ድርጊቱን በአይኑ ያየ አንድ ግለሰብ በአጠቃላይ ቁጥራቸው እስከ 18 የሚደርሱ ሰዎች ታግተው ተወስደዋል ብሎ ለሚድያችን ተናግሯል።
በሌላ ተመሳሳይ ዜና በዛሬው እለት ከጠዋቱ 12 ሰአት ጀምሮ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ታጣቂዎች በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ እና በርበር ቀበሌ በከፈቱት ተኩስ ከ 12 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ የአካባቢው ምንጮች ነግረውናል። ንፁሀን ሲገደሉ ከፍተኛ የአካል እና የንብረት ውድመት መድረሱም በተጨማሪ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ሰው ወደፈለገበት ቦታ መንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለው ከሰሞኑ መናገራቸው ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር።
ኮሚሽነር ጀነራሉ ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ ከዕገታ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ የከተተውን ሁኔታ ለመቀየር ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከደህንነት ተቋማት እና ከክልሎች ጋር በመቀናጀት በስፋት ተሰርቷል ብለው ነበር።
በገጠር እና በከተማ አካባቢ ዜጎችን በማገት ከቤተሰቦቻቸው ስልክ መደወልን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ገንዘብ የሚጠይቁበት እና የሚወስዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው በተሰራው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ዕገታን ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።
ይህንን ሁኔታ ለማስቀረት በተሰሩ ኦፕሬሽኖች በዕገታ ተግባር ይሳተፉ የነበሩ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሆነም ጠቁመው ነበር።
መረጃን ከመሠረት!




