የኢትዮጵያ አለም አቀፍ አበዳሪዎች ገንዘባቸውን ለማስመለስ ህጋዊ አማራጭ ሊወስዱ እንደሚችሉ ተናገሩ
(መሠረት ሚድያ)- ኢትዮጵያ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር እያረገችው ያለው የብድር ሽግሽግ ብዙ ርቀት መጓዝ ባለመቻሉ አበዳሪዎች ጉዳዩን ወደ ህግ ሊወስዱት እያሰቡ እንደሆነ ተሰምቷል።
ሬውተርስ ማምሻውን የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው በሀገሪቱ እና በአበዳሪዎች መሀል ሲካሄድ የቆየው የብድር ሽግሽግ ንግግር ሳይሳካ ቀርቷል፣ ይህም ሀገሪቱን ላለፉት ሁለት አመታት የፋይናንስ ስናግ ውስጥ ከትተው በሚገኙ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻሉ ነው።
ኢትዮጵያ የዛሬ አንድ አመት ተኩል ገደማ የአለም አቀፍ ቦንድ ክፍያን ሳትፈፅም መቅረቷ ይታወሳል፣ በወቅቱ ክፍያውን ከመፈፀም ይልቅ ብድሩን በG20 ሀገራት ማዕቀፍ ውስጥ ለሽግሽግ ማዘጋጀት ተመራጭ ሆኖ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት ንግግሩ አሁን ባይሳካም በርካታ እመርታዎች መኖራቸውን ያስታወቀ ሲሆን ንግግሩ ወደፊት እንደሚቀጥል ተስፋ ማረጉ ተሰምቷል።
ስምምነት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መሀል አበዳሪዎች የ15 ፐርሰንት የእዳ ስረዛ ማድረግ እንዲሁም ወደፊት የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ (export) መሻሻል ካሳየ አሁን ያጡትን ገንዘብ ወደፊት ማግኘት የሚያስችላቸው ይገኝበታል።
የኢትዮጵያ የብድር አስመላሽ ኮሚቴ ውስጥ ሞርጋን ስታንሊ ኢንቨስትመንት ማኔጅመንት፣ ፍራንክሊን ቴምፕልቶን እና ቪ አር ሄጅ ፈንድ እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፣ በውይይቱ አለመሳካትም መበሳጨታቸውን ይፋ አርገዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለባት አጠቃላይ የውጭ ብድር 31 ቢልዮን ዶላር የተሻገረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የቻይና ብድር አንድ አራተኛው እንደሚሆን ሬውተርስ ዘግቧል።
"ኢትዮጵያ በሽግሽጉ ዙርያ የተከለሰ አዲስ ሰነድ ይዛ ከቀረበች በሩ ለንግግር ክፍት ነው፣ አሁን ላይ ግን ኮሚቴው ንግግሩ ከዚህ በላይ መጓዝ እንደማይቻል ይገልፃል" ያለው የአበዳሪው አካል ህጋዊ አማራጭን ከመከተል ጀምሮ ማንኛውንም መንገድ ሊከተል ይችላል ብሏል።
ኢትዮጵያ እና አበዳሪዎች አሁን ስምምነት ላይ መድረስ ያልቻሉት በአንድ ቢልዮን ብር ቦንድ ዙርያ መሆኑ ታውቋል። የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) አበዳሪዎቹ እና የኢትዮጵያ መንግስት ንግግር ማድረግ እንዲቀጥሉ አበረታቷል።
-መሠረት ሚድያ-



