አዲስ አበባ የሚገኘው የአዘርባጃን ኤምባሲ የኢትዮጵያውያን ሠዓልያንን ስራዎች ለውድድር እና አውደ ርዕይ በሚል ወስዶ መከልከሉ ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ የሚገኘው የአዘርባጃን ኤምባሲ ከአለላ መልቲሚድያ እና ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የስዕል ውድድር እና ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀት ማስታወቂያ ያወጡት የዛሬ አመት ተኩል ገደማ ነበር።
የውድድሩ አላማ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ግንዛቤ መፍጠር የነበረ ሲሆን ለዚህ ውድድር በግጥም፣ ስነ ፅሁፍ እና አጭር ፊልም በተጨማሪ 17 ኢትዮጵያውያን ሰዓልያን ተሳትፈው ነበር።
በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አራት ሰዓልያን የገንዘብ ሽልማትና ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ ወደ አዘርባጃን እንደሚሄዱ በይፋ ተነግሮ ነበር።
ይሁንና አሸናፊቹ ኤምባሲው ባዘጋጀው ኘሮግራም ላይ ይፋ ከተደረጉ በኋላ አሸናፊ ያልሆኑት ስራዎቻቸው ሊመለስላቸው ሲገባ እስካሁን ደጋግመው ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
"የሽልማቱ ዕለት አሸናፊ ባለመሆኔ ስዕሌን መቼ መውሰድ እንዳለብኝ ስጠይቅ ኘሮግራሙ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሚመለስልኝ ተነጋግረን ተለያየን። ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ ስዕሌን ለመውሰድ ብጠይቅም ሊመልሱልኝ አልቻሉም" የሚለው ምህረቱ ዋሴ የተባለ ተወዳዳሪ አርቲስት ነው።
አክሎም "የተወዳደርኩበት የኔልሰን ማንዴላን ምስል በአዝራር በመስራት ነበር። የአዘርባጃን አምባሳደር ለቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ዋና ፀሃፊ ሙሳ ፋኪ መሃማት በስጦታ ሲያበረክቱ በሚዲያ ተመለከትሁ፣ ያለ እኔ ፈቃድና እውቅና ለውድድር ያስገባሁትን ስዕል መመለስ ሲገባቸው ለምን ለሶስተኛ ወገን አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ በማለት ከኤምባሲው ጋር በአካል፣ በኢሜል እንዲሁም በደብዳቤ ብጠይቅም መፍትሄ አላገኘሁም" በማለት አስረድቷል።
ሌሎች ተወዳዳሪዎችም ለሚድያችን እንደተናገሩት ለውድድር የቀረቡትን ሁሉንም ስዕሎች አወዳዳሪዎቹ እንደማይመልሱና ለሚፈልጉት አላማ ማዋል እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል።
"ጭራሽ አሸናፊ የነበሩ አራት ሰዓልያን የተገባላቸው የገንዘብ ሽልማት አልተሰጣቸውም፣ ወደ አዘርባጃንም አልሄዱም። አሸናፊ ያልሆኑ ስዕሎችን መመለስ ሲገባቸው ወርሰዋል" የሚሉት ሌላኛው ምንጫችን ናቸው።
ለውድድር የቀረቡ ስዕሎችን የሰራነው ሙሉ በሙሉ በራሳችን ወጭ ነው የሚሉት ተወዳዳሪዎቹ "የራሳችንን የፈጠራ ስራዎች ያለምንም እውቅና ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ የመስጠት መብት የላቸውም። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን የተፈፀመብንን ማጭበርበርና በደል ፍትህ እንድናገኝ ይወቁልን" ብለዋል።
በዚህ ዙርያ የአዘርባጃን ኤምባሲን ለማነጋገር ሙከራ አርገው እንደነበር ጥያቄ የቀረበላቸው ሰዓሊያኑ ከኤምባሲው ጋር በነመነጋገር ችግሩ ለመፍታት ከ 9 ወር በላይ እንደሆናቸው ገልፀው ውድድሩ የተካሄደው ከአንድ አመት በፊት ቢሆንም እስካሁን ምንም መፍትሄ አላገኘንም ብለዋል።
መሠረት ሚድያ አምባሳደሩን እና ኤምባሲውን ለማግኘው ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ጥያቄያችንን ወደ አለላ መልቲሚዲያ መርተውታል።
በዚህ ዙርያ ከአለላ መልቲሚዲያ ለሚድያችን ምላሽ የሰጡት ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ አደራጀው አስፋው ናቸው።
አቶ አደራጀው 'ተጓዥ ኪነጥበባት' የተባለውን የኪነጥበብ ፕሮግራም ድርጅታቸው መቅረፁን ገልፀው በአዘርባጃን የተካሄደው 'ኮፕ29' ላይ የተወሰኑትን ለመውሰድ እቅድ ነበር ይላሉ፣ ለዚህም የአዘርባጃን ኤምባሲ እንደ አጋዥ ተሳታፊ ሆኖ እንደነበርም ያስረዳሉ።
"ኤምባሲው የሽልማት ፕሮግራሙን እና የተወሰኑ የማስታወቂያ ስራዎችን ወጪ ሸፍኗል። እርግጥ ነው አሸናፊው/አሸናፊዎች ወደ አዘርባጃን አልሄዱም፣ ቃል የተገባውም ብርም አልተሰጠም። ይህ የሆነው ስፖንሰሮች ቃል የገቡትን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ነው" ይላሉ።
አቶ አደራጀው የአዘርባጃን ኤምባሲ የፕሮግራሙ ተባባሪ እንጂ አዘጋጅ አለመሆኑ ይታወቅልን፣ ለውድድር የሚቀርቡ ስራዎች የአለላ መልቲሚድያ ንብረት እንደሚሆኑ ቀድመን አስታውቀናል፣ ስዕሎቹን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለተያያዘ ስራ እንደፈለግነው ልንጠቀምበት እንችላለን በዚህም መሰረት ለአፍሪካ ህብረት የቀድሞ ሊቀመንበር ካለ ሰዓሊው ፍቃድ ተሰጥቷል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ይሁንና ሚድያችን የስዕል ስራዎቹ እንደማይመለሱ በግልፅ ስምምነት ወይም ኮንትራት አለመቀመጡን፣ ለአፍሪካ ህብረት የቀድሞ ሀላፊ የተሰጠው ስዕል ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ለማይገናኝ ጉዳይ መሆኑን እንዲሁም አርቲስቶቹ ስዕሎቹን በተመለከተ የፈረሙት ዶክመንት ካለ አለላ መልቲሚዲያን ቢጠይቅም ይህ ዜና እስከወጣበት ሰዓት ምላሽ አላገኘም።
አለላ መልቲሚድያ 'ተጓዥ ኪነ ጥበባት' የተባለው የፌስቡክ ገፁ ላይ ከ370,000 ብር በላይ ሽልማት ማዘጋጀቱን በመጀመርያ እንዳስተዋወቀ የተመለከትን ሲሆን ኋላ ላይ በሽልማቱ ዙርያ ጥያቄ ሲነሳ ይህን ከገፁ ላይ ኤዲት አርጎ ማውጣቱን ተመልክተናል።
ከዚህም በተጨማሪ ለውድድር የሚቀርቡ የስዕል ስራዎችን ለባለቤቶቹ የመመለስ ግዴታ እንደሌለበት የሚያሳይ ምስል አለላ መልቲሚዲያ ቢልክን ተወዳዳሪዎች በጭራሽ እንደማያውቁት ተናግረዋል።
"በጭራሽ አልተነገረንም፣ አሁን አቀናብረው ያዘጋጁት ነው። እንኳንና ይህንን ሁሉ የውድድር መስፈርት ቀርቶ ስራዎቻችንን የመረካከቢያ ፎርም እንኳን አላዘጋጁም ነበር። ለምሳሌ አብዛኛው ተወዳዳሪ ያየው የቪድዮ ማስታወቂያውንና ፖስተሩን ነው። እዛ ላይ ደግሞ እንደዚህ አይነት ሀሳብ ከነጭራሹም የለም" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
አንድ ተወዳዳሪ ደግሞ "ምንም አይነት የውድድሩ ግዴታ ተብሎ ተፅፎ ያነበብነው፣ የተነበበልንም ሆነ የፈረምነው የውል ግዴታ የለም። ሲጀመር እንደዚያ አይነት ውልና ግዴታ ቢኖር በጭራሽ በውድድሩ ላይ አልሳተፍም ነበር" ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰአሊያን እና ቀራጺያን ማህበር ፕሬዝደንት አክሊሉ መንግስቱ በዚህ ዙርያ ለኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት ደብዳቤ የፃፉ ሲሆን ሠአሊ ምህረቱ ዋሴ የተሳተፈበት ስዕል ለባለቤቱ መመለስ ሲገባው ከእውቅናው ውጪ ለቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ተሰጥቷል ብሏል።
"መብቱ ሳይጠበቅ የተከናወነ ድርጊት በመሆኑ ፅህፈት ቤታችሁ የሠአሊውን መብት እንዲያስጠብቅ እንጠይቃለን" ብሏል።
ሠዓሊ ምህረቱ ዋሴ በበኩሉ "ይህንን ጉዳይ ኤምባሲው እና አለላ መልቲሚድያ አሁንም መፍትሄ የማይሰጡን ከሆነ ወደቀጣዩ ሂደት ለመሸጋገር እንገደዳለን" በማለት ለሚድያችን ተናግሯል።
-መሠረት ሚድያ-






