መንግስት ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎች ባዘጋጁት የዩትዩብ ውይይት ላይ ጠ/ሚር አብይ አህመድ እንዲገኙ ጥሪ አደረጉ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ በዋሽንግተን ዲሲ እና በለንደን እንዲሁም ሌሎች ከተሞች የተቃውሞ ትዕይንተ ህዝብ እያዘጋጁ ያሉ ዜጎች በዛሬው ዕለት አንድ ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስገብተዋል።
የትዕይንተ-ህዝቦችና ሰላማዊ ሰልፎች አዘጋጅ ግብረ-ሃይል በሚል የሚጠራው ስብስብ በበርካታ ድርጅቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች የተቋቋመ እንደሆነ የሚነገርለት ሲሆን የመንግስትን 'ጦረኛ' አካሄድ በመተቸት የበይነ-መረብ የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝብ እያዘጋጀ ይገኛል።
ይህ የበይነ-መረብ የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝብ የሚካሄደው ቅዳሜ መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ከአመሻሹ 12 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን፣ መሪ ቃሉም— “ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን! ግፋዊ አገዛዝ ያብቃ! ከምርጫ በፊት ሽግግር ይኑር!!” የሚል እንደሆነ መሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ያሳያል።
በዚህ የተቃውሞ ትዕይንተ-ህዝብ ላይ በወቅቱ የአገራችን ፖለቲካ ወይም የሲቪክ እንቅስቃሴ የጎላ የተጽዕኖ ፈጣሪነት ሚናና ማህበራዊ መሰረት አላቸው ተብሎ የታመነባቸው 20 ታዋቂ ሰዎች ተገኝተው በብዙ ሚሊዮኖች ለሚቆጠር ታዳሚ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።
"ይህ መድረክ በዋናነት የተዘጋጀው በእርስዎ እየተመራ ያለው የብልጽግና መንግስት በሚያራምደው የጦረኝነት ፖሊሲ ምክኒያት የአገሪቱና የህዝቧ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ለመቃዎም ነው። ነገር ግን በእርስዎ የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በአገሪቱ ፖለቲካ የራሴ የሚለው ማህበራዊ መሰረት ያለውና የአገሪቱን የወደፊት ህልውና በመወሰን እረገድም የራሱ ሚና እንዳለው በመገንዘብ እንደ አንድ የፖለቲካ ኃይል ቢጋበዝና በመድረኩ ላይ ቢገኝ ተገቢ ነው ብሎ ግብረ-ሃይላችን አምኗል" በማለጥ የጥሪ ደብዳቤው ይገልፃል።
አክሎም "ግብረ-ሃይላችን ባልተለመደ ሁኔታ በራሱ የተቃውሞ መድረክ ላይ የአገዛዙ ቁንጮ መሪ የሆኑትን ሰው ለመጋበዝ የወሰነውም እርስዎ ከጦርነት ውጭ ሌላ የመፍትሄ አማራጭ የማይታየዎትና ለእንዲህ ዓይነቱ ሰላማዊ የህዝብ መድረክም አክብሮት እንደሌለዎት ሳይገነዘብ ቀርቶ ሳይሆን የአገራችንን ህልውና እየተፈታተነ የሚገኘው የወቅቱ የፖለቲካ ቀውስ በሀቀኛ ድርድርና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በኛ በኩል ያለንን ልባዊ ፍላጎት ለኢትዮዽያ ህዝብና ለዓለም-አቀፉ ህብረተሰብ ለማሳዬት በማሰብ ነው" በማለት ያስነብባል።
በዚህም መሰረት ጠ/ሚሩ ፍላጎት ካላቸው ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት በበይነ-መረብ መድረኩ ላይ ተገኝተው እየቀረበባቸው ባለው የተቃውሞ ሀሳብ ላይ ያላቸውን አቋም ተጋብዘዋል።
-መሠረት ሚድያ-


