የፖለቲካ እስረኞችን ከማይካድራ ጭፍጨፋ ፍርደኞች ጋር በይቅርታ አንድ ላይ ለመፍታት መታቀዱ ተቃውሞ አስነሳ
(መሠረት ሚድያ)- በአማራ ክልል ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር በተያያዘ በማረሚያ ቤቶች ተይዘው የሚገኙ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ከመንግስት የቀረበላቸውን የይቅርታ ሰነድ አንፈርምም በማለት ጠንካራ ተቃውሞ ማቅረባቸውን መሠረት ሚድያ መዘገቡ ይታወሳል።
መንግስት የፖለቲካ ታሳሪዎቹን ከስድስት ዓመታት በፊት በማይካድራ ከተፈፀመው ዘግናኝ የጅምላ ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ "በሰብአዊ ፍጡር ላይ የሚፈፀም ወንጀል" (crimes against humanity) ተከሰሱ እና ከተፈረደባቸው አካላት ጋር በአንድ ላይ አደባልቆ በይቅርታ ለመፍታት ማቀዱ ታሳሪዎቹን አስቆጥቷል።
የመሠረት ሚድያ የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት የፖለቲካ እስረኞቹ ይህንን ውሳኔ "እጅግ ዘግናኝ የሆነ ግድያና ጭፍጨፋ ፈጽመው ፍርድ ካገኙ ግለሰቦች ጋር እኩል በማሰለፍ በሕዝብ ዘንድ በተመሳሳይ እይታ እንዲታዩና የወንጀሉ ተካፋይ ተደርገው እንዲሳሉ ሆን ተብሎ የተሸረበ ሴራ ነው" ሲሉ አውግዘዉታል።
ታሳሪዎቹ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ይህንን የይቅርታ ሀሳብ አዘጋጅቶ ለመንግስት ማቅረቡን በመግለጽ የኮሚሽኑ እርምጃ እጅግ እንዳዘናቸውና ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ተናግረዋል።
መንግስት በሚመጣው አዲስ ዓመት ከ1,300 በላይ ሰዎችን በይቅርታ ለማስፈታት አቅዶ የይቅርታ ደብዳቤ እያስፈረመ ይገኛል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ በርካቶች የቀረበላቸውን አነጋጋሪ የይቅርታ ሰነድ ቢፈርሙም 30 የሚሆኑ ታዋቂ የፖለቲካ እስረኞች ግን "አልፈርምም" በማለት አቋም ይዘዋል።
የቀረበው የይቅርታ ሰነድ አወዛጋቢ ቃል የሚከተለውን ያካትታል፦ «በአማራ ክልል ፅንፈኛው ቡድን በሚያደርገው ትግል ላይ መሳተፌ ስህተት መሆኑን በማመን መንግስትንና ሕዝብን ይቅርታ እጠይቃለሁ። በክልሉ ለጠፋው ሕይወትና ለወደመው ንብረት ኃላፊነት እወስዳለሁ። ሁለተኛ በአንዲህ ያለ ፀረ-ሰላም ተግባር እንደማልሳተፍ ቃል እገባለሁ፤ ይህንን አድርጌ ብገኝ መንግስት ማንኛውንም እርምጃ እንዲወስድብኝ በፈቃዴ እፈርማለሁ!»
ይህንን የይቅርታ ሰነድ አንፈርምም ካሉት 30 ታሳሪዎች መካከል አቶ ዮሐንስ ኃያለው፣ ዶ/ር ወንድወሰን አስፋው፣ ዶ/ር ሲሳይ አወቀ፣ መስከረም አበራ፣ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እና ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው ይገኙበታል።
እነዚህን ፊርማ የከለከሉ እስረኞች መንግስት "ምን እናድርጋቸው?" በሚል ውይይት እያደረገበት እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በማረሚያ ቤት ከወትሮው የተለየ ጥብቅ ፍተሻና የከፋ አያያዝ እየተደረገባቸው ይገኛል።
የይቅርታ ሂደቱ መነሻ ከስድስት ወራት በፊት የኢሰመኮ ኮሚሽነር አቶ ብርሀኑ አዴሎ ማረሚያ ቤቱን በጎበኙበት ወቅት የገቡት ቃል እንደነበርና በመቀጠልም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ ፈቃድ ማግኘታቸውን በመግለጽ የታሳሪዎች ተወካይ ኮሚቴ እንዲመረጥ ተደርጎ ነበር።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት መንግስት የቀረበውን የይቅርታ ቅድመ-ሁኔታና አያያዝ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፃሚዎች ጋር በማደባለቁ በፖለቲካ እስረኞችና በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል።
| መሠረት ሚድያ |


