የባህር ዳር ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች የታሰረው ባልደረባቸው ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ (ዶ/ር ደቦል) ፍትህ እንዲያገኝ በህብረት ጠየቁ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ የጤና ባለሙያዎች በመላው ኢትዮጵያ ሲያሰሙት የነበረውን ድምፅ እና ሲያቀርቡት የነበረውን የመብት እና የጥቅም ጥያቄ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በማስተጋባት የሚታወቀው 'ዶ/ር ደቦል' ለእስር መዳረጉ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የባህር ዳር ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች የታሰረው ባልደረባቸው ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ (ዶ/ር ደቦል) ፍትህ እንዲያገኝ በህብረት ትናንት ጠይቀዋል።
ባለሞያዎቹ የተለያዩ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን ከነዚህም መካከል ፍትህ ለዶ/ር ዳንኤል፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ ጤና ባለሞያዎች፣ ጥያቄዎችን የህልውና ነው፣ ድጋሜ አድማውን ለማድረግ 2 ወር ይቀረናል፣ ጥያቄዎቻችን ይፈቱልን፣ ዶ/ር ዳንኤል ጀግናችን ነው፣ የንቅናቄው ባለቤት እራሱ የጤና ባለሞያው ነው የሚሉ ይገኙበታል።
ትናንት በህብረት ድምፅ ያሰሙት የዶ/ር ዳንኤል ባልደረቦች በንቅናቄው እና በእሱ መታሰር ዙርያ ያላቸውን አቋም እና የሚያደርጉትን ትግልና ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
ለዶ/ር ዳንኤል የሚደረገው የድጋፍ ድምፅ በሌሎች ሆስፒታሎች እና ዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል።
በቅርቡ የንቅናቄው ቦርድ አባላት እንዳስታወቁት ለጥያቄዎቻቸው መልስ የማይሰጥ ከሆነ ከሁለት ወር በሗላ በድጋሜ የስራ ማቆም አድማ እንደሚደረግ ለመንግስት አስጠንቅቀዋል።
"ጥያቄዎቻችን ሳይድበሰበሱ ይመለሱ የሚል መልእክታችንን በሰላማዊ መንገድ አቅርበናል። ይህ መልካም ተሞክሮ ሌሎች ተቋማትም ማዳበር አለባቸው። አንዳችን ስንታሰር ሁላችንም እንደታሰርን ያህል ሊሰማን ይገባል" ያሉት አንድ የጤና ባለሙያ ናቸው።
"ባልደረቦቻችን ዋጋ እየከፈሉ ያሉት የእኛን የመብት እና የመኖር ጥያቄ ስለተናገሩ እንጂ ወንጀለኛ ሆነው አይደለም። ፍርሀትን ያስወገደ ትዉልድ መብቱን ያስከብራል" በማለት ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያው 'Debol Surgery Bedside' የተባለ መፅሀፍ የፃፈ እንዲሁም 'MAC Ethiopia' የተባለ የህክምና ባለሙያዎች ከሙያቸው ውጪ ሌሎች ተሰጥዎቻቸውን ፈልገው እንዲያገኙ የሚያግዝ ድርጅትን ከመሰረቱ አንዱ ነው።
ዶ/ር ዳንኤል ባህር ዳር በሚገኘው ጥበበ ግዮን ሆስፒታል የፅንስና የማህፀን ህክምና (Obstetrics and Gynecology) የመጨረሻ አመት ረዚደንት ሀኪም ሲሆን ከስድስት ወር በሗላ ምርቃት እንዳለው ታውቋል።
መረጃን ከመሠረት!



