የሰብዐዊ መብት ተሟጋቹ በመንግስት አካላት በደረሰባቸው ጫና ከሥራ ኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ
(መሠረት ሚድያ)- ከተመሰረተ አራት አመት ተኩል ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን (Ethiopian Human Rights Defenders Center) በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ባጋጠማቸው አስገዳጅ ሁኔታዎች ከሐምሌ 25/2017 ዓ.ም ጀምሮ ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አሳውቀዋል።
"ከአንድ አመት ወዲህ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በሚገኙ ሚዲያዎች ላይ እየቀረብኩ አገሪቱ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የምሰጠቸው መገልጫዎችና ማብራሪያዎች፣ በማህበረ ድህረ ገጾች ላይ ዜጎችን ስለ መብታቸው እንዲያውቁና በአገሪቱ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ በማስመልከት የማካፍላቸው ሃሳቦችና የምሰነዝራቸው የሰሉ ትችቶች በአገዛዝ ሥርአቱ ዘንድ በጥሩ ሁኔታ እየታዩ ባለመምጣታቸው የተነሳ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ አይነት ጫናዎችን ሳስተናግድ ቆይቻለሁ" በማለት አቶ ያሬድ አስታውቀዋል።
አክለውም የተለያዩ ዛቻዎች፣ ማስፈራሪያዎችና ትንኮሳዎችን በጸጥታ አካላት በኩል ሲፈጸሙ እንዲሁም በተንቀሳቃሽ ስልኮቼ ያልተለመዱ ጥሪዎችን ሳስተናግድ ያለውን ግልፅ ስጋት ችላ በማለት በሥራዬ ላይ አተኩሬ ቆይቻለሁ ብለዋል።
"ሆኖም በዚህ ሁኔታ ውስጥ በነጻነት ለመወጣትም ሆነ የተቀበልኩትን የሥራ ሃላፊነት በብቃት ለማከናወን የማልችልበት ደረጃ ላይ መድረሴን ስላረጋገጥኩ በተጓዳኝም በሥራ ጫና ብዛት ችላ ያልኳቸው የግል የጤና ጉዳዮችም ስለነበሩ እነዚህን ምክንያቶች በመጥቀስ ከወራቶች በፊት ለድርጅቱ ቦርድ የመልቀቂያ ጥያቄዬ አቅርቤ በምትኬ ሰው እንዲፈልጉ አሳውቄያለሁ" ብለዋል።
በተወሰነ ደረጃ መሻሻሎች ታይተውበት የነበረው የአገራችን የሲቪክ ምህዳር ዳግም እየተዘጋና ከፍተኛ አደጋዎችም ከፊቱ የተደቀኑ መሆኑን የሚገልፁት አቶ ያሬድ ሚዲያዎች ለጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
አቶ ያሬድ ተቋሙ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቋቋምና በሌሎች አፍሪካ አገሮች ከሚገኙ አቻ ድርጅቶች ጎን ቆሞ ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች መብት መከበርና አቅማቸውንም ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
ድርጅቱ ከተመሰረተ አጭር እድሜ ያለው ቢሆንም ሲያከናውን የቆያቸው ሥራዎች እና አገሪቱ ውስጥ ለሚፈጽሙ የመብት ጥሰቶች፤ በተለይም በጋዜጠኞች፣ በሲቪል ማህበረሰብ አባላት እና በመብት ተሟጋቾ ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በማጋለጥና መብታቸው እንዲከበር በአደባባይ በመሟገት ይታወቃል።
መረጃን ከመሠረት!



