በትግራይ ክልል ያለው የሚዲያ ምህዳር እየፈራረሰ መሆኑን የሚገልፅ ሪፖርት ወጣ
(መሠረት ሚድያ)- ትናንት በመላው ዓለም የተከበረውን የፕሬስ ነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ ‘VOX Tigray’ የተሰኘው የፕሬስ ነፃነት ተሟጋች ድርጅት በትግራይ ክልል ያለውን የሚዲያ ሁኔታ የሚዳስስ አሳሳቢ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ድርጅቱ ሥራውን በይፋ የጀመረው ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ሲሆን በክልሉ የሚገኘው የሚዲያ ምህዳር በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉንና የፕሬስ ነፃነት አደጋ ላይ መውደቁን በሚያሳይ ዝርዝር ጥናት አውጥቷል።
ይህ ሪፖርት የተዘጋጀው በግል ሚዲያ ውስጥ ከሚሰሩ ጋዜጠኞች፣ ከሚዲያ ስራ አስኪያጆች እና ቀደም ሲል በመንግስት መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ይሠሩ ከነበሩ ባለሙያዎች ጋር በተደረገ ጥንቃቄ የተሞላበት የቀጥታ ቃለ-መጠይቅ መሆኑ ተገልጿል።
በሪፖርቱ ግኝት መሠረት በትግራይ ክልል የሚገኘው የሚዲያ ድባብ በአካላዊ ጥቃት፣ ያለአግባብ እስራት፣ ስልታዊ በሆነ የስነ-ልቦና ጫና እና በባለሙያዎች የጅምላ ስራ መልቀቅ የታጀበ ሆኗል።
የግል ሚዲያ ባለሙያዎች በመስክ ስራ ወቅት የተኩስ ጥቃትን ጨምሮ፣ መደበኛ የሆነ የፖሊስ ትንኮሳና በአስፈሪ ስልኮች የታጀበ የስም ማጥፋት ዘመቻ እየደረሰባቸው ይገኛል።
ለዚህም እንደ ማሳያ በቅርቡ በመጋቢት ወር የታሰሩትን የሮማን ኦንላይን ጋዜጠኛ ሸዊት ገብረእግዚአብሔርን እና የትግራይ ቴሌቪዥን ባለሙያ የነበረውን ዮሐንስ በርሀን መጥቀስ እንደሚቻል ሪፖርቱ አመላክቷል።
ምንም እንኳን ሁለቱም ጋዜጠኞች በዋስ ቢፈቱም፣ እስራቱ ባለስልጣናት ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን ወንጀል ለማድረግ እየተጠቀሙበት መሆኑን ያሳያል።
ከግል ሚዲያዎች በተጨማሪ በመንግስት እና በድርጅት ስር የሚገኙት እንደ ትግራይ ቴሌቪዥን እና ድምጺ ወያነ ያሉ ተቋማትም ከባድ ውስጣዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
ከ2018 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ ቢያንስ 23 ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ስራቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል ወይም ደግሞ ያሉበት ሳይታወቅ ተሰውረዋል።
ለዚህ የጅምላ ስራ መልቀቅ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ከባድ የአርትኦት ጣልቃ ገብነት፣ ለተወሰኑ ቡድኖች ፍላጎት እንዲሰሩ የሚደረግ ጫና እና የደመወዝ መዘግየት የፈጠረው የኢኮኖሚ ችግር መሆኑ በዝርዝር ተቀምጧል።
"ይህ የጠነከረ ጫና በክልሉ የሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች በብዛት እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ሰባት የግል ሚዲያ ድርጅቶች እና ስምንት ታዋቂ ጋዜጠኞች ክልሉን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል" ያለው ሪፖርቱ በተለይም ከየካቲት ጀምሮ ባሉት 40 ቀናት ውስጥ በደረሰባቸው ከፍተኛ ክትትልና ጥቃት የተነሳ አብዛኛው ባለሙያ የተሰደደበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል።
‘VOX Tigray’ ይህንን ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው በዚህ መግለጫ፣ የክልሉ ባለስልጣናት በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርጉትን ክትትልና እስራት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ የፌዴራል መንግስት ደግሞ የሚዲያ ፈቃዶችን ከመሰረዝ እንዲታቀብ እና የክልሉን በጀት እንዲለቅ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ተቋማት ለተጎዱ ጋዜጠኞች የህግና የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያደርጉ ድርጅቱ አሳስቧል።
| መሠረት ሚድያ |


