የፖለቲካ እስረኛው አቶ ዮሐንስ ቧያለው በፀና ታመው ሆስፒታል መግባታቸው ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በቂሊንጦ ማረሚያ ማዕከል በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ዮሐንስ ቧያሌው ለሁለተኛ ጊዜ በፀና ታመው ሆስፒታል መግባታቸውን ቤተሰቦቻቸው ለመሠረት ሚዲያ ተናግረዋል።
አቶ ዮሐንስ ሆስፒታል የገቡት ቀደም ሲል በአዋሽ አርባ ታስረው በነበረበት ወቅት ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በወቅቱ በቂ ሕክምና ማገኘት ስላልቻሉ ነው ሲሉም አክለዋል።
ሕመሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰባቸው እንደመጣ የገለፁት ቤተሰቦቻቸው ማረሚያ ቤቱ አቶ ዮሐንስን ለማሳከም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካልደረሰኝ በስተቀር ወደ ሕክምና አልወስድም ብሎ ቆይቷል ይላሉ።
በዚህ መኃል ጤናቸው ታውኮ ለሕይወታቸው አስጊ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የተናገሩት ቤተሰቦቻቸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሆስፒታል መግባታቸው አስታውቀዋል።
የገጠማቸው ሕመም ፋታ የሚሰጥ አይደለም ያሉት የቅርብ ቤተሰቦቻቸው በእጃቸው እና በአንገታቸው መካከል የሚያገናኝ ነርቭ መጎዳቱን እና በቂ ሕክምና ካላገኙ እጃቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ የሕክምና ዶክተሮች አሳስበዋል ይላሉ።
አቶ ዮሐንስ ቧያሌው በአማራ ክልል የሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ በሽብር ተጠርጥረው ለሁለት ዓመታት ያህል በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
-መሠረት ሚድያ-


