በሚድያችን ዘገባ የቀረበበት የሆሳዕና ከተማው አሰቃቂ ድርጊት ፈፃሚ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
(መሠረት ሚድያ)- ከሁለት ቀን ባቀረብነው አንድ ዘገባችን ወጣት ምርታለም ዳሮታ የተባለች ግለሰብ ሆሳዕና ከተማ ውስጥ በምትገኝ አሰሪዋ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የአካል መጉደል እና ድብደባ መፈፀሟን ጠቅሰን ነበር።
ይህን ዘገባ ተከትሎ የዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ አስተዳደር በዛሬው ዕለት እንዳስታወቀው የዳውሮ ዞን ፖሊስ ከሀዲያ ዞን ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በወጣቷ ላይ ጥቃት ጥቃት በማድረስ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር አውሏል።
የዳውሮ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ብርሃኑ ባይከዳኝ እንደገለፁት የምርመራ ቡድኑ የቤት ሠራተኛ በነበረችው በወጣት ምርታለም ላይ ጥቃት ያደረሱ ወ/ሮ ሜሮን መንገሻ እና ባለቤቷን በቁጥጥር ስር አውሏል ብለዋል።
ተበዳይ ወጣቷ በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ የሻይቲ ፉላሳ ቀበሌ ተወላጅ እና ነዋሪ የነበረች ሲሆን ከ2005 ዓ/ም ጀምሮ በሀድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ነዋሪነቷን ያደረገች መሆኑን የፖሊስ ሀላፊው ገልፀዋል።
እንዲሁም ወ/ሮ ሜሮን መንገሻ በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ የጎቦ ሻመና ቀበሌ ነዋሪ ስትሆን በሥራ አጋጣሚ በሀድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ 18 ማዞርያ በርበራ በሚባል አካባቢ ነዋሪ እንደሆነችና በ2005 ዓ.ም ምርታለም ዳሮታን በቤት ሠራተኝነት ወደ ሆሳዕና ከተማ እንደወሰደቻት አመላክተዋል።
"ቢሆንም ምርታለም ላለፉት 12 ዓመታት ወደ ቤተሰቦቿዋ ያልተመለሰች ሲሆን ወ/ሮ ሜሮን ከወሰደቻት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ጥቃቶችን፣ ድብደባዎች የስነ-ልቦና ጫናዎችን ታደርስባት እንደነበር የምርመራ ቡድኑ ማወቅ ችሏል" በማለት ገልፀዋል።
በድብደባው ምክንያት እጁዋ ሊቆረጥ መቻሉን የገለፁት የምርመራ ቡድኑ አሁን ላይ ነፍሰ ጡር እንደሆነችም ጠቁመዋል።
ምርመራ ቡድኑ በሆሳዕና ከተማ በመገኘት ጉዳዩን እያጣራ ያለ ሲሆን ተበዳይ ምርታለምን በሆሳና ንግስት ህሊና መሐመድ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል ላይ የህክምና እርዳታ እያገኘች እንደሆነ ተናግረዋል።
ወ/ሮ ሜሮን መንገሻ እና ባለቤቷዋ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመግለጽ አሁንም ሰፊ ምርመራዎች ተደርገው የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ይሰራልም ብለዋል።
"የግራ እጇ የለም፣ እግሯ በሚዘገንን ሁኔታ ቁስል በቁስል ነው። በአጠቃላይ እንዲህ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ በወ/ሮ ሜሮን ቤት የአካል ጉዳተኛ ሆና ተመልሳለች" በማለት ጉዳዩን የተከታተሉ እና ለሚድያችን በማህበራዊ ሚዲያ ያጋሩ የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል።
-መሠረት ሚድያ-




