በመንግስት በቅርስነት ተመዝግቦ የሚገኘው የብሪቲሽ መፅሐፍ ቅዱስ ማህበር ህንፃ በፒያሳ ኮሪደር ልማት ምክንያት ሊፈርስ መሆኑ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቀድመው ከተሰሩ ህንፃዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በተለምዶ ፒያሳ አምፒር ሲኒማ አካባቢ የሚገኘው የብሪቲሽ መፅሐፍ ቅዱስ ማህበር (British Bible Society) ወይም በአሁን ግዜ 'ሸዋ ሆቴል' በመባል የሚታወቀው ህንፃ ነው።
ህንፃው በ1920ቹ ሙሉ በሙሉ በእንግሊዞች የተገነባ ሲሆን በፊት ለእምነት ተቋምነት እና ለመፅሐፍ ቅዱስ መሸጫ፣ አሁን ደግሞ ንግድ ስራ ላይ ውሎ ይገኛል።
መሠረት ሚድያ እንዳረጋገጠው ህንፃው አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በታሪካዊ ቅርስነት ተመዝግቦ ይገኛል፣ ይህን የሚያሳይ ሰነድም እጃችን ገብቷል።
ይሁንና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አሁን ላይ ህንፃውን ተከራይተው ለሚገኙ ድርጅቶች የኪራይ ውል ማቋረጥ ደብዳቤ ጥር 20/2018 ዓ.ም መስጠቱን ሚድያችን የደረሰው ማስረጃ ያሳያል፣ ምክንያቱ ደግሞ በኮሪደር ልማት ምክንያት ይፈርሳል የሚል ነው።
ይሁንና በአራዳ ክፍለ ከተማ የባህል እና ኪነጥበብ ፅህፈት ቤት ህንፃው ቅርስ መሆኑን በመጠቆም ለቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ደብዳቤ ፅፎ ነበር፣ ታሪካዊ ቅርስ ቤቱ አስፈላጊው ክትትል እና ጥበቃ እንዲደረግለትም አሳስቦ ነበር።
ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው እና በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶችን የመመዝገብ፣ የመጠበቅ፣ የማልማት እና ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ የማድረግ ሀላፊነት ያለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ኪነጥበብ ቢሮም ድምፁን አሰምቷል።
ቢሮው የካቲት 20/2018 ዓ.ም ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በፃፈው ደብዳቤ ከቢሮው እውቅና ውጪ ቅርሶቹን ከሶስተኛ ወገን ጋር ለማፍረስ የተሄደበት ሂደት 'አግባብ አይደለም' ብሏል።
"ብሪቲሽ መፅሐፍ ቅዱስ ማህበር በመባል የሚታወቁት ቤቶች በቢሯችን በቅርስነት የተመዘገቡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ቅርስ ቤቶቹ በኮሪደር ልማት ለምተው እና ታድሰው የአካባቢው መልካም ገፅታ በሆኑበት ሰዓት ከህግ ውጪ ለተከራዮቹ ማሳወቁን የአራዳ ክፍለ ከተማ ባህል እና ኪነጥበብ ፅ/ቤት አሳውቆናል" የሚለው ሚድያችን የተመለከተው ይህ ደብዳቤ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ኪነጥበብ ቢሮ አስከትሎም ስምምነት ሳይደረስ ህንፃው እንዳይፈርስ ማሳሰቢያ ለፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ልኳል።
"ህንፃውን ለማፍረስ ዝግጅት ጨርሰዋል፣ ከዛሬ ነገ ይህን ታሪካዊ ህንፃ በግብረ-ሀይል መጥተው ያፈርሱታል ብለን ስጋት ላይ ነን። ህዝብ እንዲያውቀው አርጉልን" ብለው ለመሠረት ሚድያ ቃላቸውን የሰጡት አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉብየቅርስ ጉዳዮች ተቆርቋሪ አዛውንት ናቸው።
'ቱዶር- Tudor' በተባለ በጣውላ መቃን በሚሰራ የሥነ-ህንፃ ንድፍ ያጌጠው ህንፃው አፄ ሐይለሥላሴ በወቅቱ ከእንግሊዞች ጋር ጥሩ ግንኙነት ስለነበራቸው በሰጧቸው ቁልፍ መሬት ላይ መሆኑን ያገላበጥናቸው ታሪካዊ ሰነዶች ያሳያሉ።
በሩን ልክ የዛሬ መቶ ዓመት ማለትም እ.አ.አ በ1926 የከፈተው ተቋሙ መፅሐፍ ቅዱስ ማስተማር፣ ማተም እና ማሰራጨት ዋነኛ ተግባሩ ነበር።
-መሠረት ሚድያ-






