ለድሬዳዋ ሕዝብ ድምፅ በመሆን የሚታወቀው ወጣት በቃሉ ምሥጋናው ከእስር ተፈታ
(መሠረት ሚዲያ) - በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ውስጥ ያለውን ስር የሰደደ ሙስና እና ብልሹ አሠራር በማጋለጥ የሚታወቀው ወጣት በቃሉ ምሥጋናው ከእስር መፈታቱ ታወቀ።
ወጣት በቃሉ በተደጋጋሚ እየታሰረ የሚፈታ የነበረ ሲሆን ከወራት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ ከተወሰደ በኋላ ለ3 ወራት ከ20 ቀናት በእስር ላይ ቆይቶ ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም መፈታቱን መሠረት ሚዲያ አረጋግጧል።
ወጣቱ በእስር በቆየበት ጊዜ ለሁለት ወራት ያህል በአንድ ክፍል ውስጥ በካቴና ታስሮ መቆየቱን የገለጹት የመንግሥት የመረጃ ምንጫችን በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ የጀርባ ሕመም ተዳርጎ በአሁኑ ወቅት ሕክምና በመከታተል ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ምሥጋናው ከእስር ቢፈታም ስልኩ በፖሊስ ተይዞ ያልተመለሰለት በመሆኑ እርሱን በቀጥታ ማግኘት ባንችልም ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ግለሰቦች እንደገለጹት የእስሩ መነሻ ከአራት ዓመታት በፊት የተፈጸመ የሙስና ማጋለጥ ነው።
በወቅቱ መሐል ድሬዳዋ ከተማ የሚገኘውንና 17,000 ካሬ ሜትር የሚሸፍነውን የድሬዳዋ ምድር ባቡር እግር ኳስ ሜዳ (ስታዲየም) ሽያጭ ከንቲባ ከድር ጁሀር ለቅርብ ዘመዳቸው በልማት ስም ያለ ጨረታ መሸጣቸውን ተከትሎ ይህንን ወንጀል በማጋለጡ ከፍተኛ ጫና አሳድሮባቸዋል። ይህን ማጋለጡን ተከትሎ የመሬቱ ካርታ ተሰርዞ ለመንግሥት ተመላሽ በመሆኑ በወጣቱ ላይ ቂም ተይዞበትና ጥርስ ተነክሶበት እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል።
"በእስር ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ፍርድ ቤት ይቀርብ የነበረው እንደ ሚያዝያ 23 እና 27 ዓይነት የሥራ ቀናት ባልሆኑ (በዓላት) ቀናት ለብቻው እየተጠራ ነበር። ከፍርድ ቤት ዳኛ ጋር ለብቻው እየተጠራ ቢቀርብም በተጠረጠረበት ወንጀል ሁሉ ነፃ ተብሏል። ፍርድ ቤቱም ከዚህ በላይ ቀጠሮ እንደማይሰጥ በማመኑ ምንም ዓይነት ይፋዊ ክስ ሳይመሰረትበት በ10,000 ብር ዋስ እንዲፈታ ተደርጓል" ሲሉ ምንጫችን ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ምድር ባቡር ሜዳ ሕገወጥ ምሪት በተጋለጠበት ወቅት በተነሳው ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት የምድር ባቡር ንብረት እና አጠቃላይ የባቡር ቤቶች ያሉባቸው የከዚራ መሬቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥተኛ ትዕዛዝ እንዲታገዱ መደረጉ በወጣቱ ላይ የነበረውን ቂም ይበልጥ አጠናክሮታል።
በምድር ባቡር እግር ኳስ ሜዳ ሕገወጥ ሽያጭ የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሀር እና በወቅቱ የነበረው የመሬት ልማት ኃላፊ አቶ ገበየው ጥላሁን በጉዳዩ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀርበው ቃል ሰጥተው እንደነበር ያነጋገራናቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት በ2013 ዓ.ም ሰኔ ላይ ወጣት በቃሉ ምሥጋናው ከአዲስ አበባ ተይዞ ወደ ድሬዳዋ በመወሰድ ለእስር ተዳርጎ ነበር።
" እንደ 'ሐሰተኛ መረጃ አጋርተሃል፣ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ እንዳይታመን ሠርተሃል’ በሚል ክስ አቅርበውበት የነበረ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ ውድቅ ተደርጓል። ነገር ግን በወቅቱ ከአራት ዓመት በፊት በእርቅ ተቋርጦ የነበረን የግል ክስ ፈልገው በማንሳት የ2 ዓመት እስራት እንዲፈረድበት አድርገው ነበር" ሲል ሌላኛው ጉዳዩን የሚያውቅ ምንጭ ለመሠረት ሚዲያ ገልጿል።
ወጣት በቃሉ ከቀደመው እስር ከተፈታ 1 ዓመት ሳይሞላው በድሬዳዋ ከተማ በሚፈጸሙ የሙስና ድርጊቶች ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ በተከፈተ ዘመቻ ላይ ጠርጥረነዋል በሚል እንዲሁም የ2018ቱን ምርጫ ሰበብ በማድረግ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ ወስደው እንደገና እንዳሰሩት የመሠረት ሚዲያ የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል።
ያነጋገርናቸው አንድ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ "በቃሉ ምሥጋናው ድሬዳዋ ውስጥ ስር የሰደደ የመንግሥት ሌብነት እንዳለ በማመን ከኢሕአዴግ ሥርዓት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በሌላ አጀንዳ ሳይጠለፍ ከፍተኛ የመንግሥት የሙስና ወንጀሎችን በማጋለጥ እና በተለያዩ በጎ ተግባራቱ በድሬዳዋ ዘንድ የሚታወቅ ቆራጥ ልጃችን ነው" በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
| መሠረት ሚዲያ |


