#አስተያየት ከትራንስፖርት እንግልት እስከ መንግስት አገልግሎት ምሬት: የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ያልመለሳቸው ጥያቄዎች
(መሠረት ሚድያ)- ዋነኛ የአዲስ አበባ መንገዶች ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበራቸው ገፅታ ተቀሯል። አሁን ማራኪና ወብ ሆነው ይታያሉ። የከተማዋ ጎዳናዎች ሰፋፊ የእግረኛ እና የመኪና መንገዶች ተንጥፎባቸዋል፣ የሳይክል መስመሮች ተለይተዋል። በፓርኮች ተሞልተዋል፣ በቅንጡ መብራቶች ተሽቆጥቁጠዋል፣ ለደቂቃዎች በማይቋረጡ ስክሪኖች አሸብርቀዋል።
በሌላኛው የከተማው ክፍሎች ደግሞ ከዚህ “ማራኪ” መሰረተ ልማት የሚቃረን ትዕይንት በግልፅ ይታያል። ለዐይን የሚታክቱ ረዣዥም የትራንስፖርት ሰልፎች፣ በመንግሥታዊ አገልግሎት የተማረሩ፣ በውሃና መብራት መቆረጥ የተማረሩ፣ በግዳጅ መዋጮ የተሰላቹ እና “የኮሪደር ልማት” የቀድሞ ህይወታቸውን ፈቅ ያላደረገው ዜጎች ይስተዋላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ሌሎች ሹመኞቻቸው ደጋግመው “አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ” እንደሆነች እና በከተማዋ ያለው ልማት “ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ” የሚሆን እንደሆነ ያነሳሉ።
የመንግስት መገናኛ ብዙኃን በየቀኑ ከሚዘምሩለት እና ሹማምንት በየጊዜው ከሚያወድሱት የአዲስ አበባ ኮሪደር ያልመለሳቸውን 3 ጥያቄዎች እንመልከት። አስቀድመን ግን የምቹ ከተማነትን ትርጉም በዓለም አቀፍ መነፅር እንቃኘው።
የከተማ ምቹነት ምንድን ነው?
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ከተማ ነክ ጉዳዮች ላይ የሚሰራው ዩኤን ሀቢታት (UN Habitat) ዘላቂ (stainable) የሚባል ከተማ አደጋን መቋቋም የሚችል፣ ሁሉንም የሚያስተናግድ ወይም አካታች የሆነ እንደሆነ ይጠቅሳል።
ሰዎች በአቅማቸው ቤት የሚያገኙበት፣ አረንጓዴ ስፍራ ያለው፣ የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ በቂ ትራንስፖርት፣ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ያለው፣ እና ሌሎች መስፈርቶችን ሊያሟላ ይገባል ይላል። ይህ ትርጉም ወደ ፍፁምነት የተጠጋ ይመስላል።
በዚህም ሳቢያ በዓለም ላይ ለዚህ ትርጓሜ ቅርብ የሆኑ ብዙ ከተሞች ቢኖሩም መቶ በመቶ ያሟሉ ናቸው ማለት ግን ከባድ ነው።
በተገባደደው የፈረንጆች ዓመት 98 በመቶ በማምጣት የዴንማርኳ ኮፐንሃገን አንደኛ ነበረች። ቪዬናና ዙሪክ ደግሞ ተከትለዋል። ምቹ የተባሉ ከተሞች የትራንስፖርት ችግር ችግራቸው ዓይደለም። መንግስታዊ አገልግሎቶች እጅግ ቀልጣፋ ሆነው ይታያሉ። መሰረታዊ አቅርቦቶች ሳይሰተጓጎሉ ይቀርባሉ።
ይህንን መነሻ አድርገን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ለአፍሪካ ምሳሌ”፤ ከንቲባ አደነች አቤቤ “ለኗሪዎቿ ምች” ነው ያሉትን የአዲስ አበባ ከተማ ልማት እንፈትሸው።
ትራንስፖርት እና የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት
እርግጥ ነው አዲስ አበባ ሰፋፊ የአስፋልት፣ የእግረኛ እና የሳይክል መንገዶች ተገንብተዋል። በምሸት የቀን ያህል ሰሜት የሚፈጥሩ መብራቶች በዋና ዋና ጎዳናዎች ይስተዋላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአንድ ወቅት ስለ ኮሪደር ልማት ሲናገሩ በተለይ ሰፊ ቁጥር ያለውን እግረኛ በዚያውም አብዛኛውን የከተማ ነዋሪ ይህ የኮሪደር ልማት እንደሚጠቅም እና ያንን ተሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
ሆኖም ከእነዚህ ወብ መንገዶች ጀርባ ታክሲ ወይም አውቶብስ የሚጠብቁ ሰዎች የሰሩት ረዥም ሰልፎችን መመለከት እጅግ የተለመደ ነው። ጥያቄው የሚመጣው እዚህ ጋር ነው። የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የከተማዋ የትራንሰፖርት ችግር ላይ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አለማሳየቱ ከማንም አልተደበቀም። ይህም አዲስ አበባ “ለነዋሪዎቿ ምቹ” ሆናለች የሚለውን ተደጋጋሚ ቃል ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው።
ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ የሚያሰኛቸውን መስፈርት የኢኮኖሚስት ጋዜጣ አካል የሆነው “ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተሌጀንስ ዩኒት” (EIU) በተባለ በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቡድን የሚዘጋጀው መለኪያ (index) ትራንስፖርት የከተማ ልማት ዋናው አስኳል እንደሆነ ያትታል።
መለኪያው የህዝብ ትራንስፖርት ትስስር (Connectivity)፣ የምልልስ ብዛት፣ ዘመናዊነት፣ ተደራሽነት እና ዋጋ ከተማን ከተማ እንደሚያሰኝ ያነሳል። ከዚህ ተቃራኒ በአዲስ አበባ በመገናኛ፣ በስቴዲየም፣ በፒያሳ፣ ሜክሲኮ፣ አውቶብስ ተራ፣ ቃሊቲ፣ ጦር ኃይሎች፣ ሽሮ ሜዳ እና በተለያዮ የከተማዋ ክፍሎች በተለይ በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት ትራንስፖርት የሚጠበቅ “እንደ አሸዋ” የበዛ ሰው መመልከት ምንም የማያስገርም ሆኗል።
ነዋሪዎች ሰልፎች ላይ ረዥም ደቂቃዎች፣ አልፎ አልፎም ሰዓታትን ባስ ወይም ታክሲ መጠበቅ ግድ ይለቸዋል። በተጨናቁ አውቶብሶች የሚሳፈሩ እና ረዥም ደቂቃዎች የሚጓዙ ነዋሪዎች ምን አልባትም ከቤታቸው ለመድረስ ተጨማሪ ትራንስፖርት መጠቀም ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
ሁለት ሰዓት ስራ መድረስ ያለበት አንድ ሰራተኛ ከቤቱ ንጋት 11 መነሳት ሊኖርበት ይችላል። ይህ ውብ የሆኑት እና በመብራት ያሸበረቁት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የማይሸፍኑት ሀቅ ነው። ዩኤን ሀቢታትም የተሰላጠ ትራንስፖርት ከተሞችን “ምቹ” እንደሚያሰኙ ይገልፃል።
ከውብና ማራኪ የአዲስ አበባ መንገዶች መካከል ወይም ሥር በሌሎች አገራት እንደሚታየው 10 ሺዎችን የሚያጓጉዙ ባቡሮች አሊያም ሌላ ከተማዋን የሚያስተሳስሩ ፈጣን የትራንስፖረት አማራጮች ተካተው ቢሆን ለከተማዋ ውብት ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎቿ እፎይታም በሰጡ ነበር።
እውነታው ግን ከዚህ የሚቃረን ነው፣ የመንግስት ሹመኞች የከተማዋ ትራንስፖርት እንዴት ሊፈታ እንደሚችል ሲያወሩ እብዛም አይደመጡም። እንዲያውም ቀድሞ የተሰራውን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ለማስፋፋት እና ለማሻሻል ከማሰብ ይልቅ ሲያጣጥሉ ይስተዋላል።
በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ከጦር ኃይሎች አያት እና ከቃሊቲ አውቶብስ ተራ የተዘረጉትን የባቡር መሰረተ ልማቶች “ደንቀራ” ሲሉ ተችተውታል። እሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ አንድ ፉርጎ በቀረው ባቡር ፍጹም በማይመች ሁኔታ ሺዎች ሲጓጓዙበት ለተመለከተ፣ የከተማዋ ነዋሪ በትራንስፖርት ችግር ምን ያህል እንደሚፈተን እና የኮሪደሩ ልማት የለወጠለት ነገር እንደሌለ ይረዳል።
ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ለነዋሪዎቹ ምቹነትን አለማረጋገጡ የሚታይ እውነት ነው። የመንግስታዊ አገልግሎት ቅልጥፍና በ “ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተሌጀንስ ዩኒት” እና ዩኤን ሀቢታት መለኪያ የከተማ ምቹነት ከመንገድ ዝርጋታ እና ህንፃ ግንባታ ያለፈ ነው።
ከተማ ውስጥ የሚሰጠው አገልግሎት ምን ያህል ቀልጣፋ እና ከሙሰና የፃዳ ነው የሚለው ጉዳይ ወሳኝ ነው። የዓለም ባንክን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ተቋማት መስፈርት መሰረት ከተሞች ለዜጎቻቸው የሚሰጡት የተቀላጣፈ እና በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት የከተማዋን ምቹነት ይወስናል።
የዓለም ባንክ የከተሞች ልማት ፕሮግራም በአውሮፓውያኑ 2009 ባወጣው አንድ ሰንድ ላይ “ውጤታማ አካባቢያዊ መንግስት (local government) እና የተቀላጠፈ የህዝብ አገልግሎት ተደራሽነት በከተሞች ያለውን የዜጎች ኑሮ ለማሻሻል መሰረታዊ ነው” ሲል ይገልጻል።
በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዛሬም ከሚመማረሩባቸው ጉዳዮች አንዱ መንግስታዊ አግልግሎት ነው። ለዚህ ጽሁፍ ያነጋገርኩት አንድ ነዋሪ “አሁን ካለው ሲስተም፣ የድሮ በእስኪሪብቶ የሚሰራው ይሻለናል’’ ብሏል። ለምን የሚል ጥያቄ ሳስከትል “ለትንሽ ጉዳይ ሲስተም የለም፣ መብራት የለም፣ ፕሪንትር አይሰራም እያሉ ያመላልሱናል። ድሮ ቢሆን ግን አስፈላጊውን ነገር ካሟላህ አንድ ፎርም ላይ ትሞላለህ፣ ትፈርማለህ መታወቂያ ይሰጥኻል” ሲል ያነሳል።
ሌላኛዋ ነዋሪ ደግሞ መታወቂያ ለመውሰድ ለሊት 10 ሰዓት ወረፋ መያዝ ግድ እንደሆነባት አንስታልኛለች። “ለሊት 10 ሰዓት ስደርስ ከኔ በፊት 7 ሰዎች ነበሩ። አለቃዬን አስፈቅጄ ነበር የመጣሁት አንዲት መታወቂያ ለመወሰድ ፕሪንተሩ አይሰራም በሚል ቀን ሙሉ ነው የዋለኩት። ያስፈቀዱት ለግምሽ ቀን ቢሆነም ቀን ሙሉ በመቆየቴ አለቃዬ አላመነችኝም” ብላለች።
ይህ እውነት በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሚጋፈጡት ነው።
“ትንሽ” ለሚመስሉ ጉዳዮች ቀናትን መጠበቅ የተለመደ ነው። መታወቂያ ወይም የጋብቻ ማስረጃ ለማግኘት ከሚወሰደው ሰነድ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሚመስሉ መረጃዎች እንደሚጠየቁ የጠቀሱልኝ ነዋሪዎች ይህ ጉዳይ ማስፈጸምን ከባድ እንዳደረገው ይናገራሉ።
“አሁን መታወቂያ ከቀበሌ ማግኘት የሽልማት ያህል ሚያስደሰት ነው” ስትል ነዋሪዋ ገልጻልኛለች። መሰል ችግር በሌሎችም የከተማዋ ቢሮዎች የሚታይ ነው። ይህ የተጓተተ መንግስታዊ አገልግሎት አንዱ የከተማው ገጽታ ነው።
ታዲያ ይህ ገጽታ በምን መልኩ ነው “የአፍሪካ ምሳሌ” የሚሆነው? እንዴትስ ነው “አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ ሆናለች” በሚል በሙሉ ልብነት የሚያስወራው?
የውሃና ኤሌክሪክ አቅርቦት ችግር የዓለም ባንክ የከተሞች ልማት ፕሮግራም በአውሮፓውያኑ 2019 ባወጣው ሌላ ሪፖርት መግቢያ ላይ እንደ ውሃና መብራት ያሉ መሰረታዊ አቅርቦቶች ከተማን ለመኖር ምቹ የሚያስብሉ እና ኢኮኖሚን የሚያነቃቁ እጅግ ወሳኝ የከተማ ግብዓት ናቸው ይላል።
የአዲስ አበባ ጎዳናዎች መብራት ተሞልተው፣ ‘በሚወዛወዙ’ የውሃ ፍውንቴኖች አጊጠው ሲታዩ የከተማው ነዋሪ መብራት ለሰከንድም የማይጨልምበት ውሃ ፈጽሞ የማይቋረጥበት ሊመሰል ይችላል።
እውነታው ግን ሌላ ነው።
በሳምንት ሁለት ቀን ውሃ የሚያገኙ መንደሮች እንደ እድለኛ ይታያሉ። በሳምንት አንድ ቀን የሚደርሳቸው አያማረሩም። በ10 ወይም በ15 ቀን ለተወሰኑ ደቂቃዎች ውሃ የምትጎበኛው ነዋሪዎች ብዙም አይከፉም። የአዲስ አበባን የውሃ አቅርቦት ችግር በየጋራ መኖሪያ ቤቱ፣ በየሰፈሩ አንዳንዴም እንደ ትምህርት ቤት እና ጤና ተቋማት ያሉ ቦታዎች ላይ “ተግተልትለው” ሚታዩ ቢጫ ‘ጄሪካኖች’ እና ግዙፍ የውሃ ማጠራቀሚያዎች ይመሰክራሉ። ይህ እውነታ አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹ ነች ለማለት አያስደፈርም።
አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በየቀኑ የኤሌክትሪክ መቋረጥ የተለመደ ነው። ሌሎች ሥፍራዎች ላይ ለቀናት መብራት መጥፋት የነዋሪዎች የህይወት ክፍል ሆኗል። ይህ ሁኔታ የነዋሪዎችን ህይወት ብቻ ሳይሆን ትልቅ ሚባሉ የመንግስትና የግል ድርጅቶችን አገልግሎት ሲያስተጓጉል ማየት አዲስ ነገር አይደለም።
እናም ለነዋሪዎች ፈታኝ የሆነ የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦት ችግር የያዘች ከተማ ለነዋሪዎቿ ምቹ ናት ለማለት ገና ይመስላል።
ይህም ብቻ አይደለም፣ በየቀኑ እየተበራከተ የመጣው ዝርፊያ፣ ቅሚያ፣ ማጭበርበር እና ማተለል የከተማውን የወንጀል መጠን ከፍ እያደረገው ነው።
ከዚያም አልፎ ከተማ ውስጥ እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ እንደሆነ ቢገለጽም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከቴክኒክ እና ሙያ የሚመረቁ ተማሪዎች ሥራ ማጣት ሌላኛው የከተማው ፈተና ነው።
እነሱም ብቻ ሳይሆኑ በርከት ያሉ ሰዎች ሥራ አጥ መሆናቸው እና በከተማው ለልመና እጃቸውን የሚዘረጉ ሰዎች መብዛት አዲስ አበባ አሁን ለኑሮ ምቹናት የሚለውን ሀሳብ የሚቃረን ነው።
በሌላ ጎኑ ደግሞ አንስተኛ ቢዝነስ ለመጀመር የሚተጉ ሰዎች የሚያልፉበት እጅግ የተንዘዛና ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ሂደት ከተማዋ ቢዝነስ ለመጀመር አስቸጋሪ አድርጓቷል። ሥራ ላይ ያሉትም ቢሆኑ በተደጋጋሚ በሚጠየቁት መዋጮ፥ ከፍተኛ ግብር እና ሙስና የተማረሩ ይመስላል።
የአዲስ አበባ የቀድሞ ገጽ በውብ መንገዶች መሰረተ ልማቶች ተቀይሯል። የቀድሞ ችግሯቿ እና አዲስ የተፈጠሩት ፈተናዎን ደግሞ ሌላኛው ገጽታዋ ሆኖ አሁንም ቀጥለዋል።
ይህ ጽሁፍ በኢዮብ ንጋቱ የተዘጋጀ ነው።
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
-መሠረት ሚድያ-





