ከምርጫ በፊት መንግሥት የፖለቲካ እሥረኞችን እንዲፈታ እና በርከት ያሉ የውጭ ታዛቢዎች ሂደቱን እንዲከታተሉ እንዲያደርግ ተጠየቀ
(መሠረት ሚድያ)- መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ እናት ፓርቲና ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀጣዩን አገር አቀፍ ምርጫ የሞት ሽረት አድርጎ በመያዝና አገሪቱ ከገባችበት ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅል መውጫ አማራጩ አርጎ እንዲወስድ አሳስበዋል።
ፓርቲዎቹ ከምርጫው በፊትም መንግሥት የፖለቲካ እሥረኞችን እንዲፈታ እና በርከት ያሉ የውጭ ታዛቢዎች ሂደቱን ከመነሻው እንዲከታተሉ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
"ሰባተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማከናወን የአንድ ዓመት ጊዜ ብቻ የቀራት አገራችን በመንግሥት በኩል እንዲሁም በአዋጅ ሥልጣን በተሰጠው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስለምርጫውም ኾነ እየተደረጉ ስላሉ ዝግጅቶች እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም" ያሉት ፓርቲዎቹ ኢትዮጵያ አኹን ካለችበት የጦርነት አዙሪት ለመውጣትና የሕዝብ ጭቆና፣ አፈና፣ ሰቆቃና እልቂትን ማስቆም የሚቻለው ከማጭበርበር የጸዳ፣ ነጻ፣ ፍትሓዊና ተአማኒ ምርጫ በማካሄድ ብቻ መኾኑን እኛ በሰላማዊ መንገድ የምንታገል የትብብር ፓርቲዎች በጽኑ እናምናለን ብለዋል።
"ምርጫው የቀረው አንድ ዓመት ብቻ ከመኾኑ አንጻር ገዢው ፓርቲ ሰይፉን ወደ ሰገባው በመመለስ አገራችን ውስጥ የተፈጠሩ ቀውሶችን በአስቸኳይ እውነተኛና ኹሉን አካታች የሆነ ድርድር አድርጎ በመፍታት ሰላማዊ የውድድር ሜዳ ከወዲሁ እንዲፈጥር በጥብቅ እናሳስባለን" በማለት አቋማቸውን አንፀባርቀዋል።
አክለውም "መንግሥት ለምርጫው ስኬታማነት ጠቃሚ የኾኑ ሚዲያውን ፍትሓዊ በማድረግ፣ ሲቪክ ተቋማት በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ በማስቻል፣ የአፈና ቀንበሩን በማንሳት፣ ለዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛና ነጻ መደላድል በመፍጠርና የፀጥታ ተቋማትን ከብልጽግና አገልጋይነት በመነጠል፤ ታዛቢዎች ሂደቱን ከወዲሁ መከታተል የሚጀምሩበትን ኹኔታ በማመቻቸት ሚናውን እንዲወጣ እናሳስባለን። ለሰላማዊ ትግል ውጤታማነት ያግዝ ዘንድ መንግሥት የፖለቲካ እሥረኞችን እንዲፈታ እንጠይቃለን። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀጣዩን አገር አቀፍ ምርጫ የሞት ሽረት አድርጎ በመያዝና አገር ከገባችበት ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅል መውጫ አማራጩ እንደኾነ አምኖ መንግሥት ወደ መሥመር እንዲገባ ጫና በማሳደር እንደ ሕዝብ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላለፋለን" ብለዋል።
ፓርቲዎች በተናጠል የሚያደርጉት ትግል የሕዝቡን ሥቃይ ከማራዘም የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው በመረዳት በጋራ እንዲታገሉ ለሌሎች ፓርቲዎችም ጥሪ አቅርበዋል።
ሚድያችን ከሰሞኑ ከመንግስት የመረጃ ምንጮች እየደረሱት ያሉ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የተወሰኑ የፖለቲካ እስረኞች በቅርብ ይፈታሉ።
እነዚህ ምንጮች የሚፈቱት ታሳሪዎችን በስም ባይጠቅሱም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ካሉ ክስተቶች ጋር ተያይዘው በተለያዩ ግዜ ለእስር የተዳረጉ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ግን ጠቁመዋል።
መረጃን ከመሠረት!



