በፍርድ ቤት የዋስትና መብት የተፈቀደለት ዶ/ር ሀብታሙ ዓለሙን የድሬዳዋ ፖሊስ "በሌላ ወንጀል እንፈልገዋለን" በማለት ሊለቀው ፍቃደኛ አለመሆኑ ተገለጸ
(መሠረት ሚዲያ)- በድሬዳዋ ከተማ በቁጥጥር ስር ውሎ በእስር ላይ የሚገኘው ቀደም ሲል በምርጫ ተወዳዳሪ የነበረው ዶ/ር ሀብታሙ ዓለሙ ሰኞ ዕለት የድሬዳዋ መጀመሪያ ደረጃ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የ40,000 ብር ዋስትና ፈቅዶለት ከእስር እንዲፈታየወሰነ ቢሆንም የድሬዳዋ ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሳያስፈጽም ቀርቷል።
ሰኞ ተቀጥሮ የነበረው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለትናንት ማክሰኞ በሰጠው ቀጠሮ መሠረት ዶክተር ሀብታሙ ለ5ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በሚከተሉት ሁለት ዋና ዋና ቅድመ ሁኔታዎች ከእስር በዋስትና እንዲለቀቁ ወስኗል፦
1. ከድሬዳዋ ከተማም ሆነ ከኢትዮጵያ ወጥተው እንዳይሄድ
2. የተመሰረተበት ክስ በሕግ ሂደት እስኪዘጋ ድረስ ምንም ዓይነት የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እንዳያደርግ የተከለከለ መሆኑን በመጥቀስ ነበር።
ይሁን እንጂ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅላላ ወንጀል ምርመራ ክፍል የፍርድ ቤቱን የዋስትና ውሳኔ በመጣስ ዶክተር ሀብታሙን ከፖሊስ ጣቢያ ሳይለቀው መቅረቱን ምንጮች ለመሠረት ሚድያ ጠቁመዋል።
ፖሊስ ለዚህ በሰጠው ምላሽ ዶክተር ሀብታሙን "በሌላ ወንጀል እንፈልገዋለን" ማለቱ የተገለጸ ሲሆን በተለይም ቀደም ሲል በጤና ባለሙያነት ያገለግል በነበረበት ወቅት በነበረው እንቅስቃሴና ተሳትፎ እንደሚፈልገው መናገራቸው ታውቋል።
ዶክተር ሀብታሙ ዓለሙ በድሬዳዋ-1 የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግል ዕጩነት የቀረበ ቢሆንም በየደረጃው ባሉ የደህንነትና የፍትህ አካላት ተፈጽመዋል ባሏቸው የሕግ ጥሰቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገቢውን ምላሽ አልሰጠኝም በማለት ከምርጫ ውድድሩ ራሳቸውን ማግለሉ ይታወሳል።
ከዚያም ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ጠዋት ወደ ሥራ ቦታው በጉዞ ላይ እያለ በቁጥጥር ስር የዋለው ዶክተር ሀብታሙ መኖሪያ ቤቱ በድንገት ተበርብሮ ላፕቶፕ፣ ኮምፒውተሮችና የቪዲዮ/ኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች በፖሊስ መወሰዳቸው አይዘነጋም።
መሠረት ሚዲያ ቀደም ሲል ባወጣው ዘገባ ዶክተር ሀብታሙ ከተያዘ በኋላ ላለፉት ሳምንታት በ1 ሜትር በ80 ሴንቲሜትር በሆነ እጅግ ጠባብና ሰብአዊነት በጎደለው ክፍል ውስጥ ብቻውን ታስሮ እንደሚገኝ እና ይህም ለአእምሯዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ለማድረስ ታስቦ የተደረገ እንደሆነ መዘገቡ ይታወሳል።
አሁን ላይ ፍርድ ቤት በነፃነት እንዲንቀሳቀስ የዋስትና መብቱን አክብሮ እንዲፈታ ቢወስንም የድሬዳዋ ፖሊስ በሌላ አዲስ ምክንያት ውሳኔውን ሳያስፈጽም ማስቀረቱ በሕግ የበላይነትና በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ከፍተኛ ስጋትና ጥያቄ ማስነሳቱን የአካባቢው ታዛቢዎችና ደጋፊዎቻቸው ገልጸዋል።
| መሠረት ሚድያ |



