ከትግራይ ክልል በተሽከርካሪዎች እየወጡ የሚገኙ ዜጎች አፋር ላይ በተዘረጉ ኬላዎች የገንዘብ ቅሚያ እየተፈፀመባቸው መሆኑ ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ ትግራይ ክልል ውስጥ እና አዋሳኝ ስፍራዎች ላይ ተቀስቅሶ የነበረውን ግጭት እና የጦርነት ስጋት በመስጋት በርካታ ዜጎች ክልሉን በመልቀቅ እየወጡ መሆኑ ይታወቃል።
ተፈጥሮ የነበረው ግጭት አሁን ላይ የተረጋጋ ቢመስልም እንዲሁም ተቋርጦ የነበረ የአየር ትራንስፖርት ቢጀምርም በርካታ ሰዎች አሁን ድረስ በአውቶቡስ እና በግል ተሽከርካሪዎች በተለይ በአፋር ክልል በኩል ወደ መሀል ሀገር እየተጓዙ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህን ተከትሎ አፋር ውስጥ ቢያንስ ከስድስት በላይ ህጋዊ እና ህገወጥ የትራፊክ ፖሊስና የመንገድ ትራንስፖርት ኬላዎች ተዘርግተው እንደሚገኙ እና በተለያዩ ሰበቦች ገንዘብ ቅሚያ እየፈፀሙ መሆኑን ሚድያችን ሰምቷል።
እነዚህ ምንም አይነት ደረሰኝ የሌላቸው አካላት በተለያዩ ኬላዎች ላይ የአስቸኳይ ህክምና እርዳታ መስጫ (First Aid Kit)፣ የእሳት ማጥፊያ፣ አንፀባራቂ የትራፊክ ምልክቶች ወዘተ የላችሁም በማለት ከተሽከርካሪዎች እስከ 10 ሺህ ብር በግዴታ እየተቀበሉ መሆኑ ታውቋል።
"ሁሉንም አሟልተህ ስትገኝ የኮቴ ክፈል ትባላለህ፣ የለኝም ካልክ በዛ በረሃና ሙቀት ወደ ፖሊስ ጣብያ ተመለስና መኪናህን አቁመው ይላሉ" በማለት አንድ ሚድያችን ያነጋገራቸው ተጓዥ ያስረዳሉ።
ሌላ ሹፌር ደግሞ "ዛሬ በግሌ ከ6 ሺህ ብር በላይ በአፋር መንገድ ከፍያለሁ። ሌሎች የጭነት መኪኖችም መንገላታትና ድብደባ እየደረሰባቸው ነው። ይሄን የቀን ዝርፍያ አፋር ጨርሰህ ከአዋሽ 7 በኋላ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ምንም መንገላታት የለም" በማለት ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ለቤተሰብ ጥየቃ እና ለገና በዓል ወደ ትግራይ ተጉዘው የነበሩ በርካታ ወጣቶች በዚህ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ በአውቶቡስ ሲመለሱ ለእስር እንደተዳረጉ ባሳለፍነው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል።
ባሳለፍነው ሰኞ በሶስት አውቶቡስ ተሳፍረው ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ የመጡ በአብዛኛው ተማሪዎች የሆኑ 120 ወጣቶች ታስረው መወሰዳቸው የተረጋገጠ ሲሆን አሁን ላይ በአብዛኛው እድሜያቸው የገፉ ጥቂት አዛውንቶች መለቀቃቸው ታውቋል።
ይሁንና የትግራይ ሰርከስ አባላት የሆኑ ወጣቶችን ጨምሮ በርካቶች አሁን ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ የቤተሰብ አባላት አሳውቀውናል።
በሌላ ዜና፣ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ መዳረሱን ተከትሎ በመዲናዋ የተለያየ አካባቢ የጅምላ አፈሳ እየተካሔደ መሆኑን ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
በመጪው ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው ስብሰባ በርካቶች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን በተለይ ከባለፈው እሮብ ጀምሮ እንደ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች በወጣቶች መጨናነቃቸው ታውቋል።
"የፖሊስ ሐላፊዎችን ስንጠይቅም ምንም አይነት መፍትሔ ሊሰጡን አልቻሉም፣ ይባሰሰ ብሎ ስብሰባው እስኪጠናቀቅ ድረስ አይወጡም እያሉ ተጨነቅን" በማለት አንድ የታሳሪ ግለሰብ ወንድም ተናግረዋል።
-መሠረት ሚድያ-




