ግብፅ በህዳሴ ግድብ ዙርያ እያነሳችው ያለው ጥያቄ በፖለቲካዊ ሳይሆን በቴክኒክ ደረጃ ምላሽ እንዲያገኝ አሜሪካ አሳሰበች
(መሠረት ሚድያ)- የግብፅ መሪዎች በቅርቡ በተጠናቀቀው የህዳሴ ግድብ ዙርያ አዲስ ውዝግብ እያስነሱ ይገኛሉ፣ እሱም ግድቡ በሱዳን ከፍተኛ ጎርፍ አስከትሏል ይህም ግድቡን በጋራ ለመቆጣጠር አይነተኛ ማሳያ ነው የሚል ነው።
በትናንትናው ዕለት የውሀ ሀብትና እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለዚህ የግብፅ አቋም ረዘም ያለ ምላሽ የሰጠ ሲሆን ግብፅ አሁንም በቅኝ ግዛት እሳቤ ውስጥ በመሆን ለአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ጥቅማ ጥቅሞችን በመስጠት ውዝግብ ማስነሳት መቀጠሏን አንስቷል።
አሁን ደግሞ ግብፅ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርግ እየጠየቀች ባለችበት ወቅት ያልተጠበቀ ምላሽ ከአሜሪካ እንዳገኘች ታውቋል።
በቅርቡ በፕሬዝደንት ትረምፕ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ተደርገው የተሾሙት ማሳድ ቦውሎስ ሀገራቸው ኢትዮጵያ እና ግብፅ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ገልፀው የህዳሴ ግድብ ውዝግብ ፖለቲካዊ ሳይሆን ቴክኒካዊ ምላሽ እንዲያገኝ አሳስበዋል።
"ሁላችንም ጉዳዩ እንዲፈታ እና ለሁሉም ተቀባይ እንዲሆን እንፈልጋለን፣ በተለይ ደግሞ በቴክኒክ በኩል ምክንያቱም ጉዳዩ የቴክኒክ ስለሆነ ቴክኒካዊ ምላሽ ያስፈልጋል" ብለው አል አረቢያ ለተባለው ሚድያ ቦውሎስ ተናግረዋል።
ቦውሎስ ጉዳዩ የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ "የህይወት እና የመኖር ጉዳይ ነው" በማለትም ግብፅ ከዚህ በፊት ለብቻዋ የናይል ውሀ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ስትል ስትገልፅ የነበረውን በአዲስ መልኩ ሶስቱንም ሀገራት አካተው ገልፀውታል።
"አሁን ግድቡ ስለተጠናቀቀ እውን የሆነ ጉዳይ ነው፣ በዚህ መሬት ላይ ባለ እውነታ ዙርያ መፍትሄ ያስፈልጋል" በማለት አሜሪካዊው ዲፕሎማት ተናግረዋል።
በቅርብ ቀናት የግብፁ ፕሬዝደንት አዱል ፈታህ አልሲሲ ሀገራቸው የህዳሴ ግድብን በተመለከተ 'እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም' የሚል አነጋጋሪ መልዕክት በቢራቸው በኩል አሰራጭተው ነበር።
-መሠረት ሚድያ-



