"ጥያቄዎቹን ለማፈን የሚወሰዱ የሀይል እርምጃዎች ጥያቄው በልቶ የማደር ከመሆኑ አንፃር ዘለቄታዊ መፍትሄን አያመጡም፣ መንግስትንም ከህዝቡ ጋር ይበልጥ ያቃቅራል"
በቲኦዶር ተስፋዬ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- የሰሞኑ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ በከፍተኛ ደረጃ እየተስተጋባ ይገኛል። ይህ ጥያቄ ወዴት ያመራል? መንግስትስ ለጥያቄዎቹ ምን ምላሽ ሰጥቶ ጉዳዩን ያረግበዋል? የሚለው የሚጠበቅ ጉዳይ ሆኗል።
በአሁን ሰአት አንድ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የጤና ባለሙያ ወይም ዶክተር ሰባት አመት በዩኒቨርስቲ ውስጥ ተምሮ እና ከባዱን ትምህርት አጠናቆ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት በወር የሚከፈለው በልቶ ማደርን እንደ ፀጋ የሚያሳይ ደሞዝ ሆኗል።
አንድ ሰራተኛ ከስምንት ሰአት በላይ እንዲሰራ ሲደረግ በሰአት ታስቦ ክፍያ እንዲከፈለው ህግ ያስገድዳል፣ አሁን ላይ ግን በተለይም ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች፣ መምህራን እና ሌሎችም የመንግስት ሰራተኞች ይህ ክፍያ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ እና በአንዳንድ አካባቢዎች ከመጠን ያለፈ የክፍያ መዘግየት እንደሚያጋጥም በተደጋጋሚ የሚሰሙ የሰራተኞች አቤቱታዎች ያስረዳሉ፡፡
ይህ ደግሞ የሰራተኛውን የኑሮ እንቅስቃሴ በእጅጉ ፈታኝ አድርጎታል። ቀድሞ በነበረው የኑሮ ውድነቱ ላይ ተጨምሮ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሀብታም የነበረውን ድሀ እያደረገ ሲሆን ፈታኙን የድህነት ኑሮ የሚኖረውን የመንግስት ሰራተኛውን ደግሞ ህይወቱን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎበታል፡፡
ለዚህ ደግሞ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ ተፈጥሮ የነበረው መካከለኛ ገቢ ወይም ሀብት ያለው ሰው ጠፍቱዋል በሚል ያስነበቡት ሀተታ ለዚህ ትንታኔ እማኝ ማድረግ ይቻላል፡፡
ይህ የህክምና ባለሙያዎች የጀመሩት የመብት፣ የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄን በምን መልኩ መንግስት እያየው ነው ስንል የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትእ ዶ/ር ፍፁም አሰፋ ሆነው 'እውነት ሀሰት' በሚል ተዘጋጅቶ ከህብረተሰቡ ተነሱ በተባሉ ጥያቄዎች ከላይ የተጠቀሱት አመራሮች ሲመልሱ በየዘርፉ የሚነሱ የደሞዝ ጥያቄዎችን እንደሚያውቁ፣ እነዚህንም ጥያቄዎች ለመፍታት በሂደት፣ በንግግር እና በጥናት ላይ መሆናቸውን ከመጥቀስ ባሻገር ለጉዳዩ እዚህ ግባ የሚባል ምላሽ አለመስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ወደ ስልጣን ከመጡ ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ የህክምና ባለሙያዎችን ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት ተመሳሳይ የደሞዝ ጥያቄ ከህክምና ባለሙያዎች ቀርቦላቸው ነበር። እርሳቸውም ለጉዳዩ አርኪ የሆነ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ዘወርዋራ እና ለጊዜው ቀልብ ሳቢ የሆነ ለህክምና ባለሙያዎች ደግሞ ስር ሰደድ የሆነ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ትናንት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም ወቅታዊ ለሆነው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ዘወርዋራ የሆነ ንግግር ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመሩት መንግስት እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባሉ አለም አቀፍ ተቋማት ያስተቸ፣ በሀያላን መንግስታት ትዝብት ውስጥ የከተተ፣ መነሻውን አዲስ አበባ ያደረገ ቀጥሎም ወደ ክልሎች የቀጠለ የብዙዎችን የድህነት ጥግ ያሳየ፣ ከሀብት ማማ ቁለቁል ወደ ድህነት ያንደረደረ የኮሪደር ልማት በሚል ሰፊ እንቅስቃሴ እያረጉ ነው፡፡
በእርሳቸውም ሆነ በመንግስታቸው አመራሮች ይህ የኮሪደር ግንባታ ስላፈናቀለው ማህበረሰብ ሲጠየቁ ምላሻቸው "እዩት አያምርም ወይ? በፊት ይህ ቦታ ምን ነበረ?" ከማለት ባሻገር በአካባቢዎቹ ህይወታቸው ለተመሰረተ እና ከዚህ ኑሮዋቸው ለተፈናቀሉት ሰዎች ምን ተደረገ ለሚለው ግን ምላሽ የላቸውም፡፡
ይልቁንም መንግስታቸው የመንግስት ሰራተኛውን ከማማረር በተጨማሪ አሁን ላይ የተሻለ ኑሮ እየኖረ የሚገኘውን ነጋዴውን ማህበረሰብ ከግብር በተጨማሪ በትንሽ በትልቁ ብር እየጠየቀ እና እንዲሰጠው እያስገደደው ነው፡፡ ይህም ነጋዴዎች አሁን ላይ ነግዶ ከመለወጥ ወደ ሰርቶ ኑሮን ተቋቁሞ መቆየት ወደሚለው ከተሸጋገሩ ሰነባበቱ። የቆሻሻ ቅጣት፣ ዘንባባ ገጨህ ተብሎ የሚጣል የትራፊክ ቅጣት ከወር ወር የሚጨምረው የመብራት እና የውሀ ታሪፍ ህዝቡን ለልመና ዳርጎታል፡፡
አሁን ላይ ከፍ እያለ የመጣውን የሀኪሞች ጥያቄ ለማፈን በተለያዩ ክልሎች አካባቢዎች ስብሰባ እና ግምገማ በማድረግ ሀኪሞችን በማሰር እንዳይጠይቁ የማስፈራራት ስራ እየተሰራ እንደሆነ እየተሰማ ነው፡፡
ተመሳሳይ ጥያቄ ያለባቸው መምህራንም ይህንን ጥያቄ እንዳይጠይቁ ስብሰባ እና ግምገማ በሚል በአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለሁለት ቀናት ሚያዚያ 30 ና ግንቦት 01 ዝግ ተደርገው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡
ነገር ግን ጥያቄውን በዚህ መንገድ ማፈን ይቻላል ወይ? ለሚለው ተጠየቅ ብዙ ምላሾች ይሰጣሉ።
በዚህ ፅሁፍ ያሉት አማራጮች ሲዳሰሱ ይህ የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ጠንከር ብሎ በዶክተሮች ተነሳ እንጂ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የመምህራን እና ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች አብይ አጀንዳ ነው፡፡ የሀገሪቱ የሰላም እና የፀጥታ ሰራተኞችም ይህን እምብዛም ሲያሰሙ ባይስተዋሉም ደሞዛቸው ግን ከስራቸው አንፃር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡
ለዚህም ይመስላል መንግስት የማያውቃቸው ከ100 በላይ ህገወጥ ኬላዎች እንዳሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገለፀው፣ እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በፀጥታ ሀይሎች የሚፈፀሙ ዝርፊያዎች የተበራከቱት፡፡ በመንግስት ሊደረጉ ወይም ሊሰጡ ከሚችሉ መፍትዎች አንዱ በ2016 ዓ/ም ከፍተኛ ብድር የተገኘበት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሙሉ በሙሉ ማቆም ሊሆን ይችላል፡፡
ይህ የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ጠንከር ብሎ በዶክተሮች ተነሳ እንጂ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የመምህራን እና ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች አብይ አጀንዳ ነው
ይህ ማሻሻያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሹማምንቶቻቸው ተገኘ ብለው ከሚነግሩን ለውጥ ይልቅ የታየው የዜጎች ድህነት፤ የነዳጅ ዋጋ የተጋነነ ከፍተኛ ጭማሪ፤ የብር የመግዛት አቅም መዳከም በጥቅሉ መንግስት የሚሰበስበው ገንዘብ በእጅጉ ሲጨምር ዜጎች ደግሞ የሌላቸውን እንዲያመጡ ከሚያስገድድ ታሪፍ ውጪ የታየ ለውጥ የለም፡፡
ነገር ግን ይህን ማሻሻያ ማቆም ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ከአለም አቀፍ አበዳሪዎች እና ከምዕራባውያን መንግስታት ሊያመጣ ይችላል። ነገር ግን መንግስት ለዚህ ጫና ሳይንበረከክ ያለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከለስ የውጪ ግኑኙነት ፖሊሲውን ከከለሰ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ይችላል፡፡
ሌላኛው ደግሞ እጅግ ቅንጡ የሆኑትን የብሄራዊ ቤተመንግስት ግንባታን፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙትን የኮሪደር ግንባታ የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን ግንባታወች ሙሉ በሙሉ በማቆም ለግንባታዎቹ የሚደረጉ በጀት እና ትኩረት ወደ ዜጎች ሰብአዊ ልማት እንዲዞሩ ማድረግ ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡ ከዚህ ውጪም ጥያቄዎቹን ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
ነገር ግን ጥያቄዎቹን ለማፈን የሚወሰዱ የሀይል እርምጃዎች እና ስልታዊ ዘዴዎች ጥያቄው በልቶ የመኖር ከመሆኑ አንፃር ዘለቄታዊ መፍትሄን አያመጡም፣ መንግስትንም ከህዝቡ ጋር ይበልጥ ያራርቃል።
መረጃን ከመሠረት!




ምርጥ። የውስጤን ከውስጣችሁ!