የዘንድሮው የግራንድ አፍሪካ ራን ላይ የሚሳተፉ አስር የበጎ አድራጎት አጋር ድርጅቶች ይፋ ሆኑ
(መሠረት ሚድያ)- ጥቅምት 1/2018 ዓ.ም በአሜሪካ ቪርጂኒያ ግዛት አሌክሳንድሪያ ከተማ በሚካሄደው እና በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚሳተፉበት ግራንድ አፍሪካ ራን ላይ የሚሳተፉ በበጎ አድራጎት ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በዛሬው እለት ለህዝብ ተዋውቀዋል።
ለሰባተኛ ግዜ በሚካሄደው በዚህ የሩጫ ውድድር ላይ 'ከሩጫም በላይ’ በሚል መርሃግብር ተመራጮቹ አስር የበጎ አድራጎት አጋር ድርጅቶች ይፋ የተደረጉ ሲሆን መሠረት ሚድያ አንዱ ተመራጭ ከሆነው 'Girls Gotta Run Foundation (GGRF)' ከተባለው ድርጅት ጋር አብሮ በበጎ ፈቃደኝነት ይሰራል።
ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደ የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የግራንድ አፍሪካ ራን አዘጋጆች ያስተዋወቋቸው አስር ድርጅቶች ግራንድ አፍሪካ ራንን እንደመድረክ በመጠቀም ተሳታፊዎች በአቅራቢያቸዉ ያለ ወዳጅ ዘመድ ጓደኛ ቤተሰብ በኩል ለመረጡት በጎ አድራጎት ድርጅት ገቢ የሚያሰባስቡበት መድረክ ነዉ።
ይህ አሰራር በምዕራቡ ዓለም በስፋት እና ለረጅም ጊዜ የተለመደ ሲሆን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሩጫ ዝግጅቶችን በመጠቀም ገቢ ያሰባስባሉ።
እነዚህ አጋሮች ኦቲዝም፣ የአካል ጉዳት፣ ካንሰር፣ የልብ በሽታ፣ ትምህርት፣ ድህነት ማስወገድ እና የሴቶች ልጆችን መደገፍ ዙሪያ ይሰራሉ።
እነዚህ የበጎ አድራጎት አጋሮች Heart Attack Ethiopia (HAE), The Belisha Foundation (TBF), Wegene Ethiopian Foundation (WEF), Girls Gotta Run Foundation (GGRF), Alpha Breast Cancer Support Service (ABCSS), African Women’s Cancer Awareness Association (AWCAA), Ethiopian Eritrean Special Needs Community (EESNC), Raeye Children Aid (RCA), Your Ethiopian Professionals Network (YEP), and SPOT ናቸው።
የእያንዳንዱ አጋር ተወካይ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ህብረተሰቡ በዝግጅቱ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዉ ለመረጡት የበጎ አድራጎት እገዛ በማድረግ ለተሳትፏቸዉ የበለጠ ትርጉም እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ተሳታፊዎች ከጓደኞቻቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ከጎረቤቶቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በኢሜይል፣ በአጭር ጽሑፍ መልእክት፣ በስልክ ጥሪ፣ በአካል እና በማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን በመጠቀም ለመረጡት የበጎ አድራጎት ገቢ ማሰባሰብ ይችላሉ።
ተሳታፊዎች የ5ቱን ኪሎ ሜትር ርቀት በ1ሜትር፣ 10 ሜትር ወይም በ1 ኪሎ ሜትር በመከፋፈል ለመደቡት ርቀት ወዳጅ ዘመድ ጓደኛቸው የመረጡትን በጎ አድራጎት እንዲደግፉ በማድረግ ገቢ ሲያሰባስቡ ገቢዉ በቀጥታ ወደ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ገቢ ይሆናል፤ ተሳታፊዉም የአሰባሰበዉን ገቢ መጠን በገቢ ማሰባሰቢያዉ ዌብሳይት ላይ ስንት እና እነማን እንደደገፉት መከታተል ይችላል።
በዚህ መንገድ ዝግጅቱ የማህበረሰብ ግንኙነትን ያጠናክራል እና እያንዳንዱን እርምጃ ለበጎ አድራጎት እንዲዉል መንገዱን ያመቻቻል ተብሎ ይታመናል ሲሉ አዘጋጆቹ ገልፀዋል።
“መሠረት ሚድያ *




