ሱፐር ደብል ቲ በተባለ የግል ድርጅት ባለሀብት ትእዛዝ ታስረው የሚገኙ ከስልሳ በላይ ዜጎች የ 'አድኑን' ተማፅኖ ደብዳቤ ለጠ/ሚር አብይ የአህመድ ፃፉ
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን 'ሱፐር ደብል ቲ ጄኔራል ትሬዲንግ' በተባለ የግል ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሰራተኞች ላይ ስለሚፈፀም የመብት ጥሰት፣ ወንጀል እና እስር በተመለከተ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ተከታታይ መረጃዎችን ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።
ሮዳስ ቀለም እና ሱፑር ፋይበር በሚል ምርቶቹ የሚታወቀው ሱፐር ደብል ቲ ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር በሸገር ከተማ፣ አለም ገና ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ላይ ድብደባ፣ እስር፣ ማዋከብ፣ ደሞዝ መከልከል እና መቁረጥ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የሰብዓዊ ጥሰቶች እንደገፀመባቸው ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሰራተኞች ለሚድያችን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
አሁን ለሚድያችን የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው በሶስት ቦታዎች ተከፋፍለው ታስረው የሚገኙ የቀድሞ የተቋሙ ሰራተኞች የ 'አድኑን' ተማፅኖ ደብዳቤ ለጠ/ሚር አብይ አህመድ ፅፈዋል።
'እምነት በማጉደል እና በሀሰተኛ ሰነድ' በሚል ተመሳሳይ ክስ በየእስር ቤቱ ተይዘው የሚገኙት ዜጎች በዚህ ደብዳቤያቸው ላይ ከድርጅቱ በማንኛውም ምክንያት ከስራ ገበታው ተባሮም ይሁን በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁ ሰራተኞች 'የድርጅቱን ሚስጥር እና ገመና ያወጣሉ' በሚል በውጪ በኩል በፖሊስ አሳዶ እያሳሰረ ይገኛል ይላሉ።
አብዛኞቹ ታሳሪዎች የሂሳብ ክፍል ሰራተኞች እና ሽያጭ ላይ የነበሩ ሲሆኑ ይህም ድርጅቱ ውስጥ ያለውን የግብር እና ታክስ ማጭበርበር ለመሸፈን መሆኑን ተናግረዋል።
"በድርጅቱ ውስጥ ከመንግስት የተደበቁ ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጃ ማሽኖች አሉ፣ ይህን የሚያዘጋጁት ሁለት ግለሰቦች ናቸው። የሰራተኞች ደሞዝ መንግስት የሚያውቀው እና የማያውቀው ተብሎ ይፈላል፣ በባንክ ሳይሆም በእጅ ይከፈላል" ይላሉ።
መንግስት የሚያውቀው የሚባለው የጡረታን ጨምሮ የመንግስት ግብር የሚከፈልበት ሲሆን በዚህ ክፍያ ከ2 ሺህ እስከ ሰባት ሺህ ብር የሚከፈላቸው እንዳለ ታውቋል፣ ከዚህ ላይ በሰራተኛ ቅጣት እስከ 25% የሚሆነው ተቆርጦ በድርጅቱ እንደሚወሰድ መረጃዎች ያሳያሉ።
በፖስታ የሚባለው የድርጅቱ ደሞዝ ደግሞ ምንም አይነት የመንግስት ገቢ ሳይከፈልበት በዚህም በቅጣት በትንሹ ከ25% ጀምሮ እስከ ስድስት ወራት ያለ ምንም ማስረጃ እና ደረሰኝ ሰራተኞች የሚቀጡበት ሁኔታ እንዳለ ታውቋል።
ሱፐር ደብል ቲ አንድም ሰራተኛ በራሱ ስም እንደማይቀጥር፣ ይህም ከግብር ለማምለጥ የሚጠቀምበት ስልት መሆኑን አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የመንግስት ምንጫችን ጠቁመዋል።
ለጠ/ሚሩ የተፃፈው ደብዳቤ ላይ "ድርጅቱ ከውጭ ሀገር የሚያመጣቸውን እቃዎች ወይም ኬሚካሎች የመጣበትን ስቲከር ልጦ በመቀየር የዱባዩን ወደ ጣልያን ወዘተ በማድረግ የመጣውን ዱለንቲ ለምሳሌ ከ163 ኪ/ግ ወደ 200 ኪ/ግ አድርጎ በማብዛት እየሸጠ ይገኛል። ይህንንም ዶክመንት ያለው እና የሌለው ተብሎ ይመዘገባል፣ ለዚህም ማስረጃ አለን" ይላል።
በሌላ በኩል የድርጅቱ የሽያጭ ሰራተኞች ያለ ደረሰኝ መግዛት እና መሸጥ የቀን ተቀን ስራቸው መሆኑን ምንጮች ጠቁመው የድርጅቱ ማኛውም ገቢ ወደ ድርጅቱ እንደማይገባ ይህም የግብር ስወራ ወንጀል እንዳይታወቅ እነሱ ታስረው እየተሰቃዩ መሆኑ ታውቃል።
"የድርጅቱ ማንኛውም ገቢ በድርጅቱ የሂሳብ ቁጥር ባለመሆኑ እና ለማጭበርበር እንዲመች 'ባንከር ዲፓርትመንት' የሚባል አቋቁሞ በሶስተኛ ወገን ወይም በግለሰብ ሂሳብ ቁጥር ላይ መጠቀሙ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው፣ ይህ ማለት የድርጅቱ ገቢ እንዳይታወቅ ገንዘብ ማሸሽ ወይም መደበቅ ማለት ነው፣ ማስረጃ አለን" ብለው ለጠ/ሚሩ ፅፈዋል።
ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ ሌላ የድርጅቱን አሰራር የሚያውቁ ግለሰብ ደግሞ የታክስ ማጭበርበሩ ሰፊ ስራ እንደሆነ ያነሳሉ።
“በአንድ አይሱዙ መኪና ከ15% እስከ 20% ደረሰኝ ብቻ ሊቆረጥ ይችላል፣ ይህ ማለት የአንድ ሚልዮን ብር ምርት ካስጫኑ ሴልሶች የመቶ ሀምሳ ሺህ ብር ደረሰኝ ነው የሚሰጣቸው፣ ይህ ማለት 800 ሺ ብር እቃ ያለ ደረሰኝ ነው የሚልከው። ማንም የመንግስት አካል ቢያጣራ ሀሰተኛ ደረሰኝ ድርጅቱ እንደሚጠቀም ይደርስበታል። በፖስታ፣ በፖስታ አድርገው አስተካክለው ነው መኪኖች የሚወጡት” በማለት ያስረዳሉ።
አክለውም “ሽያጭ ሰራተኞቹ ደረሰኝ እንዳንጠይቅ ካደረጉ 5% ይታሰብላቸው ይባላሉ፣ በትክክል ግን ደሞዝ እራሱ አይደርሳቸውም፣ ስልክ አላነሳህም ተብለው ከ1000-8000 ሺህ ብር ይቀጣሉ። ለምሳሌ ዛሬ 700 ሺ መላክ ኖሮብህ ለደንበኛ ካላከልህ እና 650 ሺ ብር ወደ ቴዎድሮስ እውነቱ እና ናሆም ወርቁ ወደተባሉ የግል አካውንቶች ካላክም 2000 ብር ትቀጣለህ” ይላሉ።
“ለምሳሌ እኔ ሮቶ ፈልጌ ወደ ድርጅቱ ብደውል በትክክል ያወሩኝ እና ከተማዬን ይጠይቁኛል፣ ከዛ የድርጅቱን ሴልስ ይልካሉ፣ ያለደረሰኝ እናምጣልህ ይላሉ፣ ትንሽ ይቀንሳሉ ያለ ደረሰኝ ባለመግዛቴ። መንግሥት በእርግጠኝነት በቀን በኢትዮጵያ ደረጃ ከ4 እስከ6 ሚልየን ብር ግብር ያጣል በሱፐር ደብል ቲ” ብለዋል።
ሚድያችን ያረገው ምርመራ እንደሚያሳየው ቴዎድሮስ እውነቱ እና ናሆም ወርቁ በተባሉ ግለሰቦች የንግድ ባንክ አካውንት ቁጥር ሁሉም የድርጅቱ ገንዘብ እንደሚገባ እና ጭራሽ በድርጅቱ ዋና አካውንት ይህ ነው የሚባል ገንዘብ እንደማይንቀሳቀስ ያሳያል።
ተበዳዮቹ በተማፅኖ ደብዳቤያቸው ላይ "ይሄ ሁሉ በደል እየደረሰብን ነገሮችን በመነጋገር ለመፍታት በምንሞክርበት ግዜ በድርጅቱ ባለቤት በአቶ ፀጋዬ ደበበ ዛቻ በሚመስል መልኩ የሰበታ አካባቢ ህጉም ሆነ የህጉ አስፈፃሚ ኪሴ ውስጥ እንዳለ ገንዘቤ ናቸው፣ ምንም አታመጡም እንባላለን። እንዲሁም ከሸገር ፖሊስ ማንን ልጥራላችሁ? እነሱም ኪሴ ውስጥ ናቸው ብሎ ይዝትብናል። ከፈለጋችሁ በወቅታዊ ጉዳይ ልከሳችሁ እችላለሁ" እንደሚባሉ አስረድተዋል።
ባለሀብቱ የድርጅቱ ባለቤት በግላቸው 'አደጋ መከላከል' በሚል ያደራጇቸውን የፌደራል ፖሊስ ልብስ የሚለብሱ ሀይሎች "ማንኛውም ሰራተኛ እናንተ ባዘዛችሁት መሰረት መታዘዝ አለበት፣ እምቢ የሚል ካለ ከወገቡ በታች በሉት፣ መንግስት የሰጠኝ 14 ክላሽ አለኝ" እንደሚሉ በደብዳቤው ላይ ተገልጿል።
ባለሀብቱ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በርካታ በእስር ላይ የሚገኙ የቀድሞ ሰራተኞች ላይ ከአምስት አመት በላይ እንዲፈረድ እያስደረጉ መሆኑ ታውቋል።
አዳዲስ የድርጅቱ ታሳሪ ሰራተኞች ወደ ፉሪ፣ ሸገር ማረሚያ ቤት እና ዳለቲ እስር ቤቶች በብዛት መግባት መቀጠላቸውን የመንግስት ምንጮች ለሚድያችን ተናግረዋል።
"ጌታቸው ገቢሳ የሚባሉ የሸገር ሲቲ ዳኛ ፓኬጅ በሚመስል መልኩ አንድ አይነት ፍርድ እየፈረዱ ይገኛሉ፣ የሚፈርዱትም ሌላ ክፍል ዉስጥ እያስገቡ ነው። መከላከያ ምስክር ከበቂ በላይ ሲቀርብም ሆነ የሰነድ የሚታይ ማስረጃ ሲቀርብ ይሰማሉ እንጂ አያዳምጡም" በማለት አንድ የፍርድ ቤት ምንጭ ይናገራሉ።
በዚህም መሰረት ባሳለፍነው አርብ እለት ብቻ ዘጠኝ ወጣቶች 5 አመት ከ3 ወር እንደተፈረደባቸው ታውቋል።
"ይሄንንም ነጻ ከተባሉ ሌላ ክስ ይመጣል፣ ዘመድ ያለው ታራሚ በር ላይ ጠብቀዉ ይዘው ወደቤታቸው ይሄዳሉ። ደሀዎቹ ታሳሪዎችስ? መናጢ የድሀ ልጆች ናቸው የትም መሄጃ የላቸውም" በማለት ተናግረዋል።
"ባለሀብቱ እናንተን ለመልቀቅ ፍርድ ቤት ሊያዘን አይችልም ይሉናል፣ ከፖሊስ በኩልም የተረዳነው ከበላይ ትእዛዝ እንደሚቀበሉ ነው። በወጣትነታችን ራሳችንንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ለመርዳት እንዲሁም ሰርተን ለመብላት በምንችልበት ግዜ ያለ ምንም ጥፋት እና ምክንያት ከስራ ገበታችን ተፈናቅለን፣ ቤተሰቦቻችን ተበትነው፣ ልጆቻችን ትምህርት አቋርጠው፣ መኖር እስኪያቅተን ድረስ በዚህ እድሜያችን እየባከንን እንገኛለን። እጅግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆኑን ህዝብ እና መንግስት እንዲያውቅልን ኡኡታችንን እናሰማለን" በማለት ለጠ/ሚሩ ፅፈዋል።
ተበዳዮች በይግባኝ ነፃ ተብለው ሲወጡ እንዲሁም ግዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ የግል ድርጅቱ ከሸገር ማረሚያ ቤት መዝገብ ቤት ጋር በመነጋገር የሮዳስ ጉዳይ በልዩ ሆኔታ ተይዞ እንዳለ እና ፖሊሶች 'ወጥተህም የትም አትሄድም፣ ሌላ ክስ እናመጣለን' ብለው ተደጋጋሚ ክሶች እያወጡባቸው መሆኑ ታውቋል።
በዚህ አሰራር አምስት እና ስድስት ክስ ተመሳሳይ ክስ እየተመሰረተባቸው ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት እየቀያየሩ የሚገኙ ዜጎች እንዳሉ ታውቋል።
በሌላ በኩል ሁለት መንግስታዊ ተቋማት ድርጅቱ ላይ ምርመራ ቢጀምሩም በባለሀብቱ ጣልቃ ገብነት እና 'እጀ ረዥምነት' የታሳሪዎቹ ጉዳይ የትም ሊሄድ እንዳልቻለ ታውቋል።
ምርመራቸው እንዳይስተጓጎል ስማቸውን የማንጠቅሳቸው እነዚህ ተቋማት በእስር ቤት ተገኝተው ታሳሪዎችን ቢያነጋግሩም 'ባለሀብቱ እጀ ረዥም በመሆናቸው' ጉዳያቸው የትም ሊሻገር እንዳልቻለ የደረሰን መረጃ ያሳያል።
-መሠረት ሚድያ-











መንግሥትና ሕግ ባለበት ሀገር እንዲህ የስብአዊ መብት ጥሰትና ወንጀል ሲፈጸም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ ምን እየሰሩ ናቸው? መሰረት ሚዲያ ይህን የወንጀል ድርጊት ይፋ በማድረጉ እናመሰግናለን።
ፀጋዬ ደበበ ለፍርድ እስካልቀረበ
ድረስ ኢትዮጵያ ላይ ፍትህ አለ
ፍትህ ይኖራል ብዬ አላስብም