የኢሚግሬሽን ቢሮ በውጭ ሀገር ለሚኖሩ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ግለሰቦች አሻራ ሳይሰጡ ፓስፖርት መስጠቱ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- አስቸኳይ ፓስፖርት ለማግኘት ብዙ ብር ከፍሎ ማውጣት አሁን አሁን ህጋዊ እስኪመስል የተለመደ ሆኗል፣ የሚመለከታቸው አካላትም ጉዳዩ የእነሱ እስከማይመስል ድረስ ችላ ያሉት ይመስላል።
የተወሰኑ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኞችና ደላሎች ተመሳጥረው ድርጊቱ ላይ መሰማራታቸውን መሠረት ሚድያ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ማጣራቶች አረጋግጦ ነበር።
ለዛሬ የምንዳስሰው ተያያዥ ጉዳይ የሆነውን ካለ አሻራ ፓስፖርት የመስጠት አደገኛ አሰራርን ነው።
ሚድያችን በዚህ ዙርያ የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው ኢሚግሬሽን ከመመርያ ውጪ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ያለ አሻራ ፓስፖርት እየሰጠ ይገኛል።
"ይህ ጉዳይ ከሀገር ደህንት ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው። አሁን በማረሚያ ቤት የሚገኙት የቀድሞ የተቋሙ አመራሮች ዘብጥያ ካወረዳቸው የወንጀል ፍሬ ዋንኛው ያለ አሻራ ፓስፖርት ሰጥታችኋል የሚለው ክስ ነው" ብለው ለሚድያችን የተናገሩት አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የተቋሙ አመራር ናቸው።
"ያለ አሻራ ፓስፖርት የመስጠት ተግባርን የአሁኑ አመራርም እየፈፀመው ይገኛል፡፡ Double standard ማለት ይሄ ነው፣ የቀድሞን አመራር እስር ቤት ያወረደው ጉዳይ የአሁኖቹን አመራር ንፁህ ሊያደርግ አይገባም" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የፋይዳ መታወቂያ እንኳን አሻራ ሳይወሰድ በማይሰጥበት ሂደት ግለሰቦች በማን አለብኝነት ያለ አሻራ ፓስፖርት እንዴት እንዲወስዱ ተደረገ?
ሌላ ከተቋሙ የደረሰን መረጃ እንደሚያሳየው ይህ ጉዳይ ግለሰቦቹ ስም እየቀያየሩ ፓስፖርት እንዲያወጡ ከማድረጉም ባለፈ ለሀገር የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ የሚሆንበት ዕድል በጣም ከፍተኛ ነው ይላሉ፣ ለዚህም ማስረጃ የሚሆን ዶክመንት ለሚድያችን ደርሷል።
ከዚህም በተጨማሪ በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ውስጥ አላግባብ ሥልጣንን በመገልገል አመራሩ ህገወጥ ተግባራትን እየፈፀመ ነው በማለት ሰራተኞቹ ለሚድያችን አቤት ብለዋል።
"በሪፎርሙ ሰበብ በሙስና ተከሰው ከስልጣናቸው ሲነሱ በመሬት አስተዳደር ቦታ ላይ ሀላፊ የነበረውና በተመሳሳይ የከተማውን መሬት ሸጦ ጨረሰ ተብሎ ተከሶ ከሀላፊነቱ የተነሳውን አቶ ነጋሽ ቱአሻ የተባለውን ግለሰብ የሀዋሣ ኢሚግሬሽን ሀላፊ አደርገው ተሹሟል" በማለት ጥቆማቸውን አቅርበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በተቋሙ ባለሙያዎች ሊበጸለግ ይችል የነበረን ሶፍትዌር ያለ ጨረታ ለአንድ ግለሰብ ተሰጥቷል ይላሉ።
"በውጪ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ አትዮጵያውያን እንዲሁም የውጪ አገር ዜጎችን የኦንላየን ምዝገባ አገልግሎት ሶፍት ዌርን አበልጽጎ አገልግሎት እንዲሰጥ በቀደመው አመራር የተሰጠውን ህገወጥ ውል እያሳወቅናቸው አስቀጥለውታል። እናም አገሪቱ ልታገኝ የሚገባትን የውጪ ምንዛሪ ቢሮ አመቻችተውለት እንዲጋራ እድል ፈጥረውለታል" በማለት ይናገራሉ።
ይህ ብቻ አይደለም፣ በውጭ አገራት ያሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ፓስፖርታቸውን የሚያድሱበት ቀላል እና ምቹ አሰራር ያልተዘረጋ በመሆኑ እና ሂደቱ ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ በቆንስላ የተመደቡ የአመራሮቾ ቤተሰቦች ውስጥ ውስጡን ጉቦ በመቀበል ለተወሰኑት ፓስፖርት የሚሰጥበት ሂደት መኖሩም ሚድያችን ከቆንፅላ ቢሮዎች እና ኤምባሲዎች አገጋግጧል።
"በተለይ ይህን ጉዳይ አሳዛኝ የሚያደርገው በውጭ ሀገራት ከፓስፖርት ዕድሳት ጋር ተያይዞ መፍትሄ አጥተው መብታቸው ተጥሶ ከሁለት አመታት በላይ ያሳለፉት ናቸው" የሚሉት አንድ ሌላ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ዲፕሎማት ናቸው።
"አቤት የሚሉበት እድል አጥተው በስቃይ ውስጥ ናቸው፡፡ ይልቁንም ብዙ ሃዘናቸውን እየገለጹ ለችግር እየተዳረጉ ያሉ ኢትዮጵያውያን እያሉ ከነሱም ውስጥ ውስጡን አንዳንድ ሰው በኢመደበኛ መንገድ በአድልኦ አገልግሎት እየተሰጠው ነው" በማለት ጉዳዩን አስረድተዋል።
የአስቸኳይ ፓስፖርት ማመልከቻ የኦንላየን አገልግሎትን ተገልጋዮች በግልጽ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በማድረግ እና ሥራውን በኢመደበኛ ኔትዎርክ በማከናወን ዜጎች የአስቸኳይ ፓስፖርት መደበኛ ዋጋ ከዕጥፍ በላይ ክፍያ እንዲፈፅሙ በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ አላግባብ ጥቅም የማሳደድ ሥራ በግላጭ በየዕለቱ እየተካሄደ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።
የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለአስቸኳይ ፓስፖርት ለ 2 ቀን ቀጠሮ 25 ሺ ብር፣ ለአምስት ቀን ቀጠሮ 20 ሺ ብር በማስከፈል በኦንላይን በሚሞላ ፎርም አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወቃል፡፡
ተቋሙ ሲስተሙ ይሰራል በማለት ለህዝብ ቢያሳውቅም ኦንላይን የሚሞላው ፎርም ግን በማንኛውም ጊዜ ሲከፈት 'There is no available appointment date, Please check Later!' የሚል ጽሁፍ እያመጣ እየሰራ እንዳልሆነ ማንም ማረጋገጥ የሚችለው ሀቅ ነው፣ ይህ ደግሞ ለወራት የዘለቀ ችግር እንደሆነ ይታወቃል።
አሁን ላይ ከተቋሙ ግቢ ውጪ ያሉ አካላት እና የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ተመሳጥረው ለአስቸኳይ ፓስፖርት እስከ 35 ሺህ ብር እያስከፈሉ ሲሆን በተቋሙ ውስጥ ከሚሰሩ አንዳንድ የአይቲ ባለሙያዎች ጀምሮ እስከ አመራሮች የሚሳተፉበት ኔትወርክ በመዘርጋት ሲስተሙን ከእነርሱ ጋር ተመሳጥረው የሚሰሩ ግለሰቦች ብቻ ማግኘት እንዲያደርጉ በማመቻቸት ዜጎችን እየበዘበዙ ይገኛሉ፡፡
መሠረት ሚድያ አዲስ አበባ በሚገኘው ዋናው የኢሚግሬሽን ቢሮ የሚሰራው ይህ ህገወጥ አሰራርን ተመልክቷል።
ጉዳዩ እንዲህ ነው፣ አስቸኳይ ቀጠሮ የሚባለው አገልግሎት አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተዘግቶ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች የሆኑ የተቋሙን ሲስተም አድሚን (admin) የሚቆጣጠሩ ሰራተኞች በውስጥ መስመር ከደላሎች ጋር በመመሳጠር ህዝቡን 35,000 ከተቀበሉ በኋላ እነዚህ አድሚኖች ከ5,000 ብር እስከ 6,500 ብር ይቀበላሉ።
ድረ-ገፁ ለህዝብ ዝግ ተደርጎ እንዲህ ውስጥ ለውስጥ የሚሰራው የፓስፖርት ብዛት ከፍተኛ መሆን አዲስ መረጃ ባይሆንም በዚህ መጠን አንድ ግለሰብ ብቻ ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ማግኘት መቻሉ ለምን ችግሩን መቅረፍ እንዳልተፈለገ ማሳያ ነው።
በኢሚግሬሽን ሰርቨር ላይ ተቀምጠው ይህን ድርጊት የሚፈፅሙት አካላት ከሚያገኙት ገንዘብ ላይ ለበላይ አመራሮች ያካፍሉ እንደሆን በአንድ ወቅት የጠየቅናቸው አንድ የተቋሙ ሰራተኛ "ካለ እውቅና እና ካለ ቡጨቃ የሚሰራ ስራ የለም" የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተው ነበር።
-መሠረት ሚድያ-




