"የጤና ሚኒስቴር በድጋሚ ከድቶናል ስለዚህ የስራ ማቆም አድማው ይቀጥላል"- የኢትዮጵያ ጤና ባለሞያዎች ንቅናቄ ቦርድ
(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ ጤና ባለሞያዎች ንቅናቄ ቦርድ አባላት ከቀናት በፊት ከጤና ሚኒስቴር አማካሪ ጋር ይፋዊ ያልሆነ ንግግር አድርገው ነበር።
በዚህም መሰረት የጤና ባለሞያው ሰኞ ወደ ስራ እንዲመለስ ቦርዱ በመግለጫ የሚያሳውቅ ከሆነ የታሰሩት ባልደረቦቻቸውን እስከ ማክሰኞ ድረስ ለማስለቀቅ እናም ህጋዊ ጥያቄዎቻቸው ብዙም ሳይቆይ በጥቂት ጊዜ እንደሚመለስ እና ለተግባራዊነታቸውም መግለጫው በወጣ ማግስት ተገናኝቶ ለመወያየት በቃል ደረጃ ተስማምተው ነበር።
ይሁንና "ለዚህም 10 ባለሞያዎችን ለውይይት አዘጋጅተን ነበር። የታሰሩት ባልደረቦቻችንን በልባችን በመያዝ እና መልካም ፈቃድና ኃላፊነት ለማሳየት፣ ከሰኞ ጀምሮ ወደ ሥራ መመለሳችንን በማስታወቅ መግለጫ በማውጣት ጥያቄያቸውን አክብረናል" የሚለው ዛሬ ቦርዱ ያወጣው እና ለመሠረት ሚድያ የደረሰው መግለጫ ንቅናቄው መግለጫውን ይፋ ባወጀ ማግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቋሙን ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል ብሏል።
የታሰበውን ቀጣይ ውይይት በመሰረዝ መስሪያ ቤቱ በራሱ አማካሪ በኩል ለጤና ባለሙያዎቹ ቦርድ የሚከተለውን መረጃ መስጠቱ ታውቋል:
1) የባልደረባዎቻቸውን ከእስር ነፃ የማድረግ ዋስትና እንደማይሰጥ።
2) ጥያቄዎቻቸውም እየታዩ ሊመለሱ የሚችሉ እንጂ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የሚሰጥ መልስ እንደማይኖር::
3) ወደ ስራቸው ቢመለሱም ለደህንነታቸው እና ላለመታሰራቸው፣ ለማስፈራሪያዎች፣ ቅጣቶች እና ዛቻዎች ምንም ማስተማመኛ እንደማይሰጥ አስታውቋል።
"ይህ አስደንጋጭ ክህደት እኛ ላሳየነው መልካም እምነትና አክብሮት ንቀትን የሚያሳይ ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን መብቶቻቸውን የጠየቁ የጤና ባለሙያዎችን ለማዳከም እና ለአደጋ ለማጋለጥ ሆን ተብሎ የተደረገ ጥረትንም ያመለክታል" ያለው ቦርዱ ከዚህ የከፋው ደግሞ በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ባሉ ባልደረቦቻቸው ላይ ከተፈፀመው በደል በተጨማሪ ሌላ ማስፈራራት እና አዲስ እስራት ሊደረግ እንደሚችል እና እየተደረገ እንዳለም መረጃ ተሰጥቶናል ብለዋል።
"እኛ እንደ ቦርድ ይህንን ቀውስ በውይይት ለመፍታት ሃላፊነት፣ ትዕግስት እና እውነተኛ ፈቃደኝነት አሳይተናል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግን በድርጊቱ እና በዝምታው በግልጽ እንዳሳየው የሀገሪቱን የጤና ስርዓትን የሚያገለግሉ ባለሙያዎችን ለመጠበቅ፣ ለማዳመጥ ወይም ለመደራደር ፈቃደኛ አለመሆኑን በግልጽ አሳይቷል። ስለዚህ በመላ አገሪቱ የምትገኙ የጤና ባለሙያዎች ይህን ጥሪ እናቀርባለን" በማለት የስራ የስራ ማቆም አድማው እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
"ይህ ክህደት መንፈሳችንን እንዳያደፈርስ ሆኖም ቁርጠኛነታችንን እንዲያንቀሳቅስ እናድርግ። የምንታገለው ለራሳችን ብቻ አይደለም - የምንታገለው ለፍትህ፣ ለክብር እና የጤና ባለሞያው ትክክለኛ መብቱን በመጠየቁ የማይቀጣበት ወደፊትን ለመፍጠር ነው። የታሰሩት ባልደረቦቻችን አሁንም በእስር ላይ ናቸው፣ ብቸኛው 'ወንጀላቸው' ለእውነት መቆማቸው ብቻ ነው። አሁን ደግሞ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እስር እና ማንገላታት እንደሚቀጥሉ ተነግሮናል። ይህ ከአሁን በኋላ ስለ ፍትሃዊ ደመወዝ ወይም የሥራ ቦታ ክብር ብቻ አይደለም:: ይህ ስለደህንነታችን፣ ስለነፃነታችን እና ስለወደፊት ሕይወታችን ነው። የጤና ሚኒስቴር የገባው ቃል ዋጋ እንደሌለው አሳይቶናል። ውይይት ያለ መተማመን ምንም ትርጉም የለውም። በሐቀኝነት ቀርበን በከሃዲነት ተከፍለናል። እኛ ግን ወደዚህ ትግል የገባነው በስነምግባር እና በታማኝነት ነው። ስለዚህም የስራ ማቆም አድማው እንዲቀጥል ወስነናል" በማለት መግለጫው አስታውቋል።
አክሎም "በእኛ ጥሪ መሰረት ሰኞ ስራ ልትጀምሩ ያሰባችሁ ውድ ባልደረቦቻችን ከላይ በዘረዘርናቸው መከዳቶች ምክንያት የተነሳ ስራ ከመጀመር እንድትቆጠቡ አበክረን እናሳስባለን" ብሏል።
መረጃን ከመሠረት!



