የፌደራል ፖሊስ አክቲቪስት ስዩም ተሾመን ፍርድ ቤት ማቅረብ አልችልም ብሎ ምላሽ ሰጠ
(መሠረት ሚድያ)- በዛሬው ዕለት የፌደራል ፖሊስ ለፍርድ ቤት በፃፈው ደብዳቤ አክቲቪስት ስዩም ተሾመን ይዤ ለማቅረብ አልችልም አለ፣ ኮሚሽኑ ግለሰቡን ለማቅረብ ብዙ ጥረት አድርጎ ሳይሳካለት እንደቀረ አስታውቋል።
አክቲቪስቱ በሕግ ቁጥጥር ስር ሆነን ሳለ ስማችንን በማጥፋት ብሎም በፍርድ ቤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው በሚል አቶ ዮሐንስ ቧያሌውና አቶ ክርስቲያን ታደለ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ማመልከታቸው ይታወቃል።
ፍርድ ቤቱ ስዩም ተሾመን የፌደራል ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርበው ለአራተኛ ጊዜ ትዕዛዝ የፃፈ ቢሆንም ፖሊስ ግለሰቡን ማግኘት አልቻልኩም የሚል ምላሽ እስከዛሬ ሲሰጥ ቆይቷል።
ተከሳሾቹ በበኩላቸው ፌደራል ፖሊስ ይህንን ብሎ ለፍርድ ቤቱ ያሳወቀበትን ደብዳቤ ችሎቱ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ዳኛው "ይህ ደብዳቤ ለእናንተ ሰጥተን በተለያየ መንገድ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቢወጣ ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያላቸውን ተስፋ ጨርሶ የሚያጠፋ ስለሆነ ከፍርድ ቤት ውጭ መውጣት የለበትም" ሲሉ መልሰዋል።
አቶ ዮሐንስ ቧያሌው በበኩላቸው "የፍትሕ ሥርዓቱ ጨርሶ እንዲሞት ያደረገው ስዩም ተሾመ ሳይሆን በእሱ ጀርባ ያሉት የመንግሥት ተቋማት ናቸው" ሲሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ ደግሞ "ስዩምን ማቅረብ ያልቻለ የፌደራል ፖሊስ ማረሚያ ቤት ሰብሮ ገብቶ ቁሙ ተነሱ ሲለን ያድራል። የራሳቸውን መንግሥት ሥርዓት እንኳ ማክበር አልቻሉም። የፍትሕ ሥርዓቱ አንድ ጊዜ ሞቷል። ቢያንስ ለእናንተ ለዳኞች ክብር እንኳ ሲባል አዲስ አበባ ተቀምጦ ሲሰድባችሁ የሚውልን ግለሰብ ማቅረብ ነበረበት። ከእኛ ይልቅ የምታሳዝኑኝ እናንተ ናችሁ፣ የሚሰድባችሁን ግለሰብ እንኳ ማቅረብ የሚችል ፖሊስ የለም" ሲሉ አክለዋል።
“ስዩምን ማቅረብ ያልቻለ የፌደራል ፖሊስ ማረሚያ ቤት ሰብሮ ገብቶ ቁሙ ተነሱ ሲለን ያድራል። የራሳቸውን መንግሥት ሥርዓት እንኳ ማክበር አልቻሉም”- አቶ ክርስቲያን ታደለ
በተያያዘ ዜና ከሳምንት በፊት የፌደራል ፖሊስ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን በውድቅት ሌሊት ጥሶ በመግባት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱ እስረኞችን ሜዳ ላይ አንበርክኮ እንዳሳደራቸው መዘገባችን ይታወሳል።
ይህንኑ የሚድያችንን ዜና መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማረሚያ ቤት ድረስ በመሄድ ስለተፈጠረው ሁኔታ እያጣራ መሆኑን ምንጮች ለመሠረት ሚዲያ ገልፀዋል።
መረጃን ከመሠረት!



