በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ የመስጂድ አመራሮች ግድያ እንደተፈፀመባቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ ውስጥ ከትናንት በስቲያ አርብ እለት በመስጂድ ኑር በኢሻ ሰላት ወቅት የታጠቁ ኃይሎች በመግባት የመስጂድ አመራሮችን መግደላቸውን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ የነበሩት የመስጂዱ ዋና ኢማምና የወረዳው መጅሊስ ም/ሰብሳቢ፣ የመስጂድ አመራሮች፣ የመስጂድ ኻዲሞችን አሰቃቂ እና አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ መግደላቸውን ይፋ አድርጓል።
"እነሱም ሸሂድ ሆነዋል አላህ ጀነተል ፍርዶስ ይወፍቃቸው። ጠቅላይ ምክርቤቱ የእምነት ተቋማት የተከበሩ ቦታዎች በመሆናቸው ሊጠበቁ እንጅ እንዲህ አይነት አፀያፊ ተግባር የሚፈፀምባቸው መሆን የለባቸውምና ድርጊቱን በፅኑ ያወግዛል" ያለው ምክር ቤቱ መላው የሃይማኖት ተቋማትም በእምነት ቦታዎች የሚደረጉ ትንኮሳዎች እና በእምነት ተከታዮች ላይ የተቃጣ መሰል የጅምላ ግድያ ሊያወግዙና ሊያስቆሙ ይገባል ብሏል።
አክሎም "ህዝበ ሙስሊሙ ይህንን በሀይማኖት ተቋማት ላይ የተቃጣ አደጋ ለመከላከል መረጃ በመለዋወጥ የሃይማኖት ተቋማትንና አካባቢውን እንዲጠብቅ ጠቅላይ ምክርቤቱ ጥሪውን ያስተላልፋል" ብሏል።
"ብዝሃ ሀይማኖት ባለባት ሀገራችን በተለያየ እምነት ውስጥ ያሉ ህዝቦች ለዘመናት ያቆዩተን ሰላማዊ እና መልካም መስተጋብር ሆን ተብሎ ለመናድና ማባሪያ ያጣ ቀውስ ውስጥ እንድንገባ የሚፈልጉ አካላት የፈፀሙት መሆኑን ጠቅላይ ምክርቤቱ ይገነዘባል" ያለው ምክር የምክር ቤቱ መግለጫ ነው።
በመጨረሻም ሁሉም ሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች ይህ ጉዳይ አብሮ የመኖር እሴት እንዳይሸረሽር ብሎም እንዳያጠፋ ድርጊቱን እንድታወግዙ እንዲሁም በፅኑ እንድትቃወሙ እየጠየቅን መንግስትም ይህንን ተግባር በእምነት ቦታዎችና አባቶች ላይ የፈፀሙት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን ብሏል።
-መሠረት ሚድያ-




