ሰራተኞች 'ሲኦል' ሆነብን ያሉት የግል ድርጅት በቅጥር ግቢው ውስጥ ድብደባን ጨምሮ እየፈፀማቸው ያሉት አነጋጋሪ ድርጊቶች
(መሠረት ሚድያ)- አንዳንድ የመንግስትም ይሁን የግል ድርጅቶች ለሰራተኞቻቸው በመመቸትም ይሁን ባለመስማማት ስማቸው አልፎ አልፎ ይነሳል። ዛሬ ሚድያችን የሚዳስሰው ድርጅት ጉዳይ ግን 'እውነት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀም ነው?' እንደሚያስብል ሰራተኞቹ ይናገራሉ።
ሱፐር ደብል ቲ ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር በሸገር ከተማ፣ አለም ገና ውስጥ ካሉ የግል ድርጅቶች አንዱ ሲሆን እንደ ቀለም እና የውሀ ማጠራቀሚያ (በተለምዶ ሮቶ የሚባለው) ያሉ ምርቶችን ለገበያ ያቀርባል።
ድርጅቱ በሚድያዎች ላይ የገዘፈ ጥሩ ስም አለው፣ ከሰራተኞቹ ጋር እንደ የብሔር ብሔረሰብ በዓል፣ የባንዲራ ቀን ወይም ሌሎች በዓላትን ባማረ መልኩ ሲያከብር ይታያል።
"የሰራተኛውን መብትና ጥቅም የማያሰከብር ድርጅት ሁሌም ከትችት አይወጣም። ስለ ሰራተኞቹ የሚያስብና ህግ እና መመሪያ ተከትሎ የሚሰራ ደግሞ ከራሱ አልፎ ለሀገርም ምሰሶ ይሆናል" የሚለውን መልዕክት ድርጅቱ ያስተላለፈው በቅርቡ 'የሰራተኞች ቀን' ብሎ ባከበረው በዓል ላይ ነበር።
ድርጅቱ ከዚህም አልፎ በሸገር ከተማ በገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ ያስገነባውን 'ዋቶ የጤና ኬላ' የዛሬ ዓመት አስመርቆ ነበር። በቅርቡ ለመቄዶንያ ገንዘብ ሲሰባሰብም ሱፐር ደብል ቲ ጀነራል ትሬዲንግ የ500,000 ብር የገንዘብ ስጦታ አበርክቷል።
ታድያ ጉዳዩ ምን ይሆን?
አቶ ፀጋዬ ደበበ የሱፐር ደብል ቲ ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ባለቤት ናቸው፣ በርካቶች ግለሰቡን የአወዛጋቢው ፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ መንፈሳዊ ማኅበር እና ዩትዩብ ቻናል መስራች በመሆናቸውም ያስታውሷቸዋል።
አቶ ፀጋዬ የድርጅታቸው ስም በሚድያ የገነነ እንዲሆን፣ ነገር ግን የስራ ቦታው 'ሲኦል' እንዲመስል እንዳደረጉ መሠረት ሚድያ ያነጋገራቸው በርካታ ሰራተኞች ይናገራሉ።
"ባለቤቱ የፈለጉትን ሰው በፀጥታ አካላት ከማስወሰድ ጀምሮ ድብደባ እንዲፈፀም ማድረግ ይችላሉ። ፖሊሶች ሲጠሩ በደቂቃ መጥተው የተባሉትን አርገው ይሄዳሉ፣ እምቢ ያለ በሚሊሻዎች ታፍሶ ለወታደርነት ወደ ካምፕ በግዴታ ሊገባ ይችላል" የሚሉት አንድ ሰራተኛ ናቸው።
ሁሉም ሰራተኞች ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል።
ሱፐር ደብል ቲ ጀራል ትሬዲንግ አሁን ላይ ከ4 ሺህ እስከ 5 ሺህ የሚደርሱ ሰራተኞች እንዳሉት የታወቀ ሲሆን በርካታ ሰራተኞች ስማቸው ሳይጠቀስ እንኳን ለሚድያ ለመናገር ሲቸገሩ ታዝበናል።
"ከስራ አንድ ደቂቃ ያረፈደ 700 ብር፣ ማስቲካ ያኘከ 1 ሺህ ብር ይቀጣል፣ ስራ መልቀቅ እፈልጋለሁ ያለ ሊደበደብ ወይ ሊታሰር ይችላል። ሁለት ቀን አንገብጋቢ ጉዳይ እንኳን ገጥሞህ ብትቀር ሙሉ በሙሉ ከስራህ ትባረራለህ" የሚሉት ሌላኛው ሰራተኛ የሚከተለውን ድብደባ እና እንግልት በመፍራት ማንም ተመልሶ መብቴ ይከበር እንደማይል ይናገራሉ።
ሰራተኛው አክለውም "መግቢያ ሰዓት ጠዋት 12:20 ሲሆን መውጫ ደግ ማታ ከ12:00 ሰዓት ነው። መቅረት፣ ማስፈቀድ የሚባል ነገር የለም" የሚሉት በርካታ የተቋሙ ሰራተኞች የድርጅቱ ባለቤት አቶ ፀጋዬ በተደጋጋሚ "እያንዳንድሽ ብሬን ቀደሽ አትጨርሺውም፣ ምንም አታመጡም፣ የፈለኩት አረጋለሁ" በሚለው ንግግራቸው እንደሚታወቁ ያነሳሉ።
ሚድያችን እንዳረጋገጠው በተለይ ልምድ ያላቸው ሰራተኞች ለህይወታቸው እስከሚሰጉ ድረስ ከድርጅቱ መውጣት እንደማይችሉ ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ይደርሳቸዋል።
"እወጣለሁ ያለ ልምድ ያለው ሰራተኛ ካለ ይታሰራል ወይም ይደበደባል። ሲታሰሩ ደግሞ ከአንድ ሚልዮን ብር ጀምሮ ቁጥር ይጠራና ብር ሰርቋል ወይም ሰርቃለች ይባላል። በውሸት መስክር ትባላለህ፣ 20 ሺህ ብር ይከፈልሀል፣ እምቢ ካልክ አንተም ትታሰራለህ" የሚሉት አሁን ድረስ ከፍተኛ ስጋት ላይ የሚገኙት ሰራተኞች ናቸው።
ምንጮቻችን እንደጠቆሙት በዚህ ምክንያት ስራ ለቀዉ ወደ ገጠር ከሄዱ በኋላ ከዛም ተይዘው የመጡ ይገኛሉ።
"ግለሰቡ ይኸን የሚሰራዉ ደግሞ ከፖሊስ አካላት ጋር በመተባበር። ደግሞ የሚገርመዉ ስንት ሰቃይ ተማሪዎች ጥሩ እየመሰላቸዉ እየገቡ ህይወታቸዉ የተበላሸ አሉ" በማለት የተናገራችው ሌላዋ ሰራተኛ ከአካል ድብደባው በላይ የአእምሮ ቁስል የሚሆን ስድብ በርካቶች ሲሰደቡ ይውላሉ በማለት ገልፃለች።
አለም ገና በሚገኘው ፋብሪካ ውስጥ ሰራተኞች ገብተው የሚደበዱቡበት ስፍራ እንዳለ እና ስራ ሲሰሩ ደክሟቸው ቆም ያሉ ጭምር ዱላ እንደሚከተላቸው ታውቋል፣ በዚህም ምክንያት በአንድ ቀን ውስጥ ሰው ሳይደበደብበት በማይውል ቀን እንደሌለ ሰራተኞች ጠቁመዋል።
"ምንም ሳታጠፋ ተላላኪዎች ይመደቡና አጥኑት ይባላል እያንዳንዱን ሰዉ። በወሬ ስንቱ ታሰረ፣ ስንቱ ተደበደበ! ደግሞ በጣም የሚያሳዝነዉ ዉጭ ላይ ሚዲያ ላይ እንደሱ ያለ ጥሩ ያለ አይመስልም" የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሰራተኞች ናቸው።
በግለሰቡ በተገነባው ሆስፒታል ውስጥ ደግሞ በእርዳታ መድሀኒት እና ዊልቼር እንደሚገባ የታወቀ ሲሆን መድሀኒቱ እና ዊልቼሩ ግን በውድ ተመልሶ ለተጠቃሚ እንደሚሸጥ ተሰምቷል።
"ማንም ሆስፒታል የሌለ መዳኒት እዚህ ሊገኝ ይችላል፣ የእርዳታዉንም በነፃ ያስገባሉ ግን በእርዳታ ስም ይቸበቸባል፣ ይህ ማለት ሀገሪቱ እየተበዘበዘች ነው" የሚሉት ደግሞ በሸገር ከተማ አስተዳደር የሚሰሩ አንድ አመራር ናቸው።
"እንደምንሰማው ብዙ ችግር በሰራተኞች ይነሳል፣ ለምሳሌ የመብት አለመከበር ጥያቄ እና የስራ ልምድ እንኳን ሲጠየቅ የመከልከል። ግለሰቡ ለብዙ ሰው የስራ እድል የከፈቱ ናቸው፣ ግን ደግሞ የደሀ ልጅ ሰቆቃ ይብቃ ማለት ይገባል" በማለት አመራሩ ተናግረዋል።
"አንዳንዴ ይኼ ነገር አገር ዉስጥ ነዉ አይደለም እንዴ? ብለህ ታስባለህ። ስራ አጥፍተህ ከሆነ ተቀጣ፣ ገንዘብ ነዉ። የሰዉ ልጅ ግን መጫወቻ ለምን ይሆናል? እስከ መቼ ስድብ፣ ዱላ፣ እስር እና ማስፈራርያ? ለምን?" በማለት አንድ ሰራተኛ ጥያቄያቸውን ሰንዝረዋል።
በሱፐር ደብል ቲ ጄነራል ትሬዲንግ በአለም ገና ከተማ በ1999 ዓ.ም የሙከራ ምርቱን የጀመረ ድርጅት ነው።
በዚህ ዙርያ የባለቤቱን የአቶ ፀጋዬን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
-መሠረት ሚድያ-







በእሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ (ሀገሬ ብዬ ለመጥራት የሚያሳፍር እስኪመስለኝ ደርሻለሁ) የማይሰማ ነገር የለም:: ይህ የባርነት ግዞት እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም:: ሰውም መብት ማስኩብር ንፀነት ዩሚባል ቅንጦት አርጎታል:: ሁሉም ድምፅ ሁኑን እንጂ መብቴን እራሴ ማስከበር አለብኝ ካላለ ማንም አይደርስለትም በጥይም አሳዛኝ ዘመን የተሰለበ ትውልድ