በማዕድን ዘርፍ ላይ የተሰማራው ወጣት ለልማት ያዘጋጀው ቦታ ተወስዶበት ለእስር እንዴት ሊዳረግ ቻለ?
(መሠረት ሚድያ)- የድንጋይ ከሰል ለማምረት መሬት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመውሰድ ሲንቀሳቀስ የነበረ አንድ ወጣት ባለሀብት በቅርቡ በቁጥጥር ስር መዋሉ በአንዳንድ ሚድያዎች ሲገለፅ ቆይቷል።
መሠረት ሚድያ በጉዳዩ ዙርያ ጠለቅ ያለ የምርመራ ዘገባ ሲያዘጋጅ የቆየ ሲሆን እሱም እንደሚከተለው ይቀርባል።
አቶ ብርሃነመስቀል ክንፈ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አብዛኛውን እድሜውን የኖረ እና ወላይታ ዞን ውስጥ በስፋት የሚታወቅ ግለሰብ እንደሆነ በርካቶች ይናገራሉ።
የ 'ማራ ማይነርስ' ባለቤት የሆነው ግለሰቡ በቅርብ አመታት ፊቱን ወደ ማዕድን ዘርፍ በማዞር 5.9 ሔክታር መሬት በቅድሚያ የማዕድን ምርመራ ለማድረግ፣ 600 ሔክታር ደግሞ የድንጋይ ከሰል ለማውጣት በክልሉ ማዕድን ቢሮ ፈቃድ እንደተሰጠው ያሰባሰብነው መረጃ ያሳያል።
ይህ ኢንቨስትመንት ሊደረግ የታሰበውም በክልሉ በሚገኘው የጋሞ ዞን፣ ሀምቢሳ ቀበሌ ነበር።
ይሁንና ይህ በድንጋይ ከሰል ምርት ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋታል የተባለለት ፕሮጀክትን ለማሳካት እንደ መንገድ፣ የመሬት ምንጠራ እና የኢንቨስትመንት ዝግጅት በማድረግ ላይ የነበረው ባለሀብቱ በቅርቡ የማዕድን ስፍራው ተወስዶበት ለሌሎች መሰጠቱን እና እሱም ለእስር መዳረጉን ሚድያችን አረጋግጧል።
ሚድያችን ከአቶ ብርሃነመስቀል ቤተሰብ ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ባለሀብቱ ማዕድን የማውጣት ምርመራውን እና ቅድመ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ እያለ 'የአካባቢው ሰዎች እናልማው ብለዋል' በሚል ሰበብ ማስጠንቀቂያ ይደርሰው ነበር።
"ከመንግስት በህጋዊ እና በኢንቨስትመንት አዋጁ መሰረት የተሰጠው ውል ሳይጠናቀቅ ከ600 ሔክታር ውስጥ 10 ሔክታር ውሰድ ተባለ። እሱም እንዴት ይህ ይሆናል በማለት ቅሬታውን አስገባ፣ በዚህ መሀል ውሉ እንዲቋረጥበት ሲደረግ ወደ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ወሰደ" በማለት የቤተሰብ አባላት ያስረዳሉ።
አክለውም "ብርሃነመስቀል ባለማው ስፍራ ላይ በሌሎች እንቅስቃሴ ስለተጀመረ በፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ አደረገ። ታድያ በዚህ መሀል 'የአካባቢው ሰዎች ሊያለሙት ይፈልጉታል' ቢባልም እሱ በኖረበት ሀገር ላይ ከሌላ ቦታ የመጡ ሰዎችን ጨምሮ ለ50 ሰዎች ቦታው ተከፋፍሎ ተሰጠ። ይህ ሁሉ የሆነው እግድ እያለበት ነው" ብለዋል።
የፌደራል የመጀመርያ ፍርድ ቤት በያዝነው አመት ታህሳስ ወር ላይ ድጋሜ እግድ ቢሰጥም እነዚህ አዲስ ቦታው ላይ የሰፈሩ ግለሰቦች ቁፋሮ መጀመራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህ በኋላ 'እግድ ይነሳልን' የሚል ጥያቄ ሲመጣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊስን ጨምሮ በስፍራው ሄዶ ጉዳዩን በማጣራቱ ቆፋሪዎቹ እንዲያስወጣ እና ጉዳዩ ለጥቅምት 2018 ዓ.ም በፍርድ ቤት እንደተያዘ የደረሰን ተጨማሪ መረጃ ያሳያል።
በዚህ መሀል ሀሙስ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም መሳርያ የታጠቁ 20 ገደማ የፀጥታ አካላት አዲስ አበባ ውስጥ አቶ ብርሃነመስቀልን 'አደጋ ሊያደርስ ስለሚችል ያዙ ተብለን ነው' በማለት በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ታውቋል።
ግለሰቡ በተያዘበት ወቅት የደቡብ ክልል ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ጭምር ተገኝተው እንደነበር ታውቋል።
ከዚያም በመጀመርያ ቦሌ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣብያ፣ ከዚያም ወደ ዲላ ከተማ፣ ቀጥሎም አርባ ምንጭ ከተማ፣ አሁን ደግሞ በጎፋ ዞን በሚገኘው ሳውላ ከተማ እስር ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
"የእስር ትዕዛዙ የመጣው ከጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው የሚባል ነገር አለ። ክሱ ደግሞ መንግስት ገቢ እንዲያጣ አርጓል የሚል እንደሆነ ሰምተናል" የሚሉት ጉዳዩን የሚከታተሉ አንድ ምንጫችን እስሩ በመጪው ጥቅምት ፍርድ ቤቱ ለባለሀብቱ ያደላ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል በሚል እሳቤ ከወዲሁ ባለሀብቱን ለማጥቃት የተወሰደ እንደሆነ ብዙዎች እንደሚስማሙ ያስረዳሉ።
መሠረት ሚድያ የተመለከተው አንድ ሰነድ ደግሞ ግለሰቡ የተያዘው በ 'ከፍተኛ የሀገር ሀብት ምዝበራ' ተጠርጥሮ መሆኑን እና በሳውላ ከተማ ተይዞ እንዲቆይ ያዛል።
"አሁን ተይዞ ያለበት እስር ቤት ሽንት ቤት እንኳን የሌለው ነው፣ ምግብ እና መድሀኒት ማግኘት አልቻለም። ጠበቃውን እንኳን ማናገር አይፈቀድለትም" ያሉት የቤተሰብ አባል ለህይወቱ አስጊ ህመም ስላለበት መንግስት ጉዳዩን እንዲመለከት ጠይቀዋል።
'ማራ ማይነርስ' በማዕድን ፍለጋ፤ ምርመራ፤ ማምረትና እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሥራ ላይ የተሠማራ ድርጅት መሆኑ ይነገራል።
ባለቤቱ በሕጋዊ መንገድ የተረከብኩት የማዕድን ፍለጋና ማውጫ ቦታ በሕገወጥ መንገድ ተወስዶ ለሌሎች ባለሃብቶች ለመስጠት በተወሰኑ የመንግስት ባለስልጣናት እየተሰራ ነው በማለት ለመሠረት ሚዲያ ቅሬታቸውን ከወራት በፊትም አቅርበው ነበር።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ፤ በተጨማሪም በወላይታ ዞን አበላ አባያ ወረዳ ማረቃ ቀበሌ ላይ በሰዓት አምስት መቶ ቶን በዓመት ደግሞ አራት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ቶን የድንጋይ ከሰል የማምረት አቅም ያለውና በማምረት አቅሙ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ እንደሆነ በወቅቱ ተገልዖ ነበር።
የድንጋይ ከሠል ማዕድንን ፓልቨራይዝ በማድረግ ኢትዮጵያን ከቀጠናው ብቸኛ የኢንደስትሪ ባለቤት የሚያደርጋት ነው የተባለለት የኢንደስትሪ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክትን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እያከናወነ መቆየቱን የማራ ማይነርስ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃነመስቀል ለመሠረት ሚዲያ ገልጸው ነበር።
ሆኖም ግን የክልሉ ውሃ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ በድርጅቱ ላይ ተደጋጋሚ ጫና በመፍጠር በህጋዊ መንገድ ድርጅቱ የተረከበውን የማዕድን ቦታ በመንጠቅ እና ከኤጀንሲው ጋር የገባውን ውል ከህግ አግባብ ውጪ በማቋረጥ 'የአካባቢ አልሚዎች' ለሚላቸው እና ከቢሮው እና ከክልሉ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር ትስስር ያላቸው ለሚመስል አካላት ለመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራ እንደተደረገ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ምንጮች ይናገራሉ።
"ጥያቄያችን ያልተገባ የፖለቲካዊ እንድምታ እንዲኖረው በማድረግ የህዝብ ሀብት ለህዝብ ጥቅም እንዲውል የሚል ያልተገባ የፖለቲካ ሽፋን በመስጠት የውንጀላ ምላሽ በግልፅ ሲሰጥ ነበር፣ በዚህም የክልሉ ፕሬዝደንት ተሳትፈዋል" ይላሉ የመረጃ ምንጮቹ።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጉዳዩ ላይ ዶክመንተሪ መስራቱን እና በክልሉ ዉሃና ማዕድን ቢሮ ዉስጥ የሚፈፀመዉን ብልሽትና ሌብነት እንዲያጋልጥ አድጎ እንደነበር የታወቀ ሲሆን ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉን አንዳንድ ባለስልጣናት በመንካቱ ባለሀብቱ ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል።
-መሠረት ሚድያ-





