የነዳጅ ዘርፍ የሌብነት እና የሙስና ሰንሰለት ሲመረመር
(መሠረት ሚድያ)- በነዳጅ ዘርፍ የሚታየውን ብልሹ አሰራር ለመቅረፍ እንዲሁም ለኮንትሮባንድ ንግድ አላማ በየቦታው የተገነቡ አዳዲስ የነዳጅ ማደያዎች እየበዙ በመምጣታቸው በመንግስት ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አማካኝነት ለአዳዲስ የነዳጅ ማደያዎች አገር አቀፍ ጥናት እስኪቀርብ ድረስ ፍቃድ መስጠት ከቆመ ሰነባብቷል።
ይሁንና ጠ/ሚር አብይ አህመድ የዛሬ አመት ተኩል ገደማ ቤተ መንግስት ውስጥ ባለሀብቶችን ሰብስበው ባወያዩበት ወቅት በተነሳ ጥያቄ መሰረት እየታየ እና እየተጠና ለኮንትሮባንድ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ለነዳጅ ማደያዎች ፈቃድ እንዲሰጥ የጠ/ሚር ቢሮ የፈቀደው የዛሬ አራት ወር ገደማ ጥቅምት 5/2018 ዓ.ም ነበር።
ሚድያችን ከምንጮቹ ያገኘው አንድ በጠ/ሚር ፅህፈት ቤት ሀላፊ በሆኑት አለምፀሐይ ጳውሎስ የተፃፈ ደብዳቤ እንደሚለው የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተገንብተው ከቆሙ 384 የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ 117ቱ በልየታ ወደ ስራ እንዲገቡ ጠይቆ ነበር።
ይህን ጥያቄ መሰረት አድርጎ ጠ/ሚር ቢሮ ፈቃድ የሰጠ ሲሆን ችግሩም እዚህ ጋር እንደሚጀምር መረጃዎች ያሳያሉ።
"ይህን ስራ እንዲያስፈፅሙ በወቅቱ ስብሰባ ውስጥ ለነበሩት ለንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ ተሰጥቶ ነበር። ይሁንና ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤት እስከ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ድረስ መስመር በመዘርጋት ለ117 የነዳጅ ማደያዎች በጥናት ተለይተዋል በማለት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት አስፈቅደዋል" የሚሉት አንድ ከፍተኛ የመንግስት ምንጫችን ናቸው።
ሁኔታውን ሲያስረዱም "ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስከ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ድረስ በተዘረጋው የሙስና ሰንሰለት እንዴት 117 የነዳጅ ማደያዎች ተመረጡ የሚለው ነው?" ይላሉ።
መሠረት ሚድያ ከሁለት ወራት በፊት ባስነበበው አንድ ዘገባው በነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን የነዳጅ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ዲበራ ፉፋ አማካኝነት አዳዲስ የነዳጅ ማደያ ፈቃድ ጠያቂዎች ሲመጡ ከ5 ሚልዮን እስከ 10 ሚልዮን ብር እንደሚጠየቁ አስነብቦ ነበር።
ያሰባሰብናቸው ተጨማሪ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህን ያህል ብር በመጠየቅ የተስማሙትን ስም በመያዝ ለሚኒስቴሩ በማሳወቅ 117 ማደያዎች ውስጥ እንዲካተቱ ተደርገዋል።
"አንዳንድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ሀላፊዎች በውጭ በኩል የራሳቸው ደላላ በማሰማራት ገንዘብ የከፈሉትን ከሚፈቀድላቸው 117 የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ እንዲካተቱ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ አሰራር መሰረት በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት የተፈቀደላቸው ማደያዎች ፈቃድ የወሰዱ ሲሆን ይህ ገንዘብ የጣፈጣቸው እነዚህ የመንግስት ሀላፊዎች ከ117 የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ከሚያውቃቸው ውጪ በተለይ ለጥቁር ገበያ እና ለኮንትሮባድ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ማለትም አሶሳ፤ ጋምቤላ፤ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወዘተ 1 ሊትር ናፍጣ እስከ 550 ብር የሚሸጥበት እና ቀጥታ ነዳጅ የሚሻገርበት ቦታ ተፈቅዶላቸው ይገኛሉ" የሚሉት ደግሞ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሌላ ምንጫችን ናቸው።
"ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት እውቅና ውጪ ተፈቅዶላቸው የኮንትሮባንድ ስራቸውን የሚያሯሩጡ በርካታ ማደያዎች አሉ፣ የሚመለከተው የመንግስት መስሪያ ቤት ባለሥልጣኑ ቢሮ ድረስ በመምጣት ማጣራ ይቻላል" በማለት ጥቆማ ሰጥተዋል።
ይህን እንቅስቃሴ የንግድ እና ቀጠና ትስስር ሚኒስትሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ በደንብ እንደሚያውቁት የሚጠቁሙት ምንጮች የኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታው መኳንንት ገንዘብ ክፍፍሉ ላይ ባይኖሩም ትዛዝ በመቀበል ድርጊቱን እያስፈፀሙ ይገኛሉ ብለዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዲበራ ፉፋ እና የፈቃድ ክፍል ስራ አስፈፃሚ አቶ አበላ ግዛው (በአቶ ዲበራ የተሾመ) ነዳጅ ለጫነ በተለምዶ 'ቦቴ' ለሚባል መኪና የአቅጣጫ ለውጥ (ዳምፒንግ) ብር እንደሚቀበሉ በርካታ ምስክርነቶች ተሰጥተዋል።
"ይህ ማለት ኮንትሮባንድ ከሚጭኑ ኩባንያዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር 1.5 ሚሊዮን ብር፤ ለቀጥታ ተጠቃሚ ነዳጅ ለመፍቀድ 1 ሚሊዮን ብር በካሽ የምትቀበል እዛው መስሪያ ቤት የምሰራ አንድ ግለሰብ አለች" በማለት ሌላ የመስሪያ ቤቱ ምንጫችን ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል የነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎችን ለመቆጣጠር ተብሎ ሁሉም ቦቲዎች ጂፒኤስ እንዲያስገጥሙ በማድረግ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ኮንትሮባንድ እቆጣጠራለሁ በሚል ከኢትዮጵያ ቴሌኮም ጋር በመሆን ሲስተም አስገብቶ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚህ አሰራር መሰረት ከመዳረሻቸው ውጪ የሚንቀሳቀሱ ነዳጅ የጫኑ ቦቲዎችን በመያዝ በአዋጁ መሰረት ነዳጁን እና ተሸከርካሪውን በመውረስ ለመንግስት ገቢ በማድረግ እንዲሁም ይህን ያደረገ ባለሀብት 3 አመት የማሰር ስልጣን ተሰጥቷል።
"እነዚህን ቅጣቶች እንዲፈፀሙ ለማድረግ የነዳጅ ባለስልጣን ሲስተም ቢያስገባም ም/ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዲበራ በገንዘብ መደራደር ሕገ ወጥ ተግባር የፈፀሙትን እና ቦቲውን ከመውረስ እና ህገወጥ ድርጊት የፈፀመውን ነጋዴ ከማስቀጣት ይልቅ በ10 ሚሊዮን ብር በመደራደር ህገወጥ ተግባሩ እንዲበረታታ እያደረጉ ይገኛሉ" የሚሉት ምንጮች ናቸው።
"በዚህም የተነሳ ለአዲስ አበባ ከተማ የተጫነው ነዳጅ ወደ ጋምቤላ፤ አሶሳ እና ወደ ሃላባ ከተማ በብዛት እንዲሄድ በማድረግ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚፈጠረው የነዳጅ ወረፋ ሰልፍ ዋና ምክንያቱ ይሕ ነው" ብለዋል።
በቅርብ ወራት በአንዳንድ ስፍራዎች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን የነዳጅ ሰልፍ እና ዋጋ እየተስተዋለ ይገኛል።
ለምሳሌ በያዝነው ሳምንት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ አንድ ሊትር ነዳጅ ከ500 እስከ 550 ብር እየተሸጠ እንደሆነ የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
"በኦሮሚያ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ነዳጅ እንደፈለገው አያልፍም፣ አጭሩ እና ቀላሉ መንገድ ግን ይህ ነበር። በዚህ ምክንያት የነዳጅ ማደያዎች ባለቤቶች ለታጣቂዎች ከፍተኛ ብር በመክፈል ጭምር እያስገቡ አሶሳ ላይ በሌትር እስከ 550 ብር እየሸጡ ይገኛሉ" የሚሉት የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ባልደረባ ናቸው።
አክለውም "በዚህም ምክንያት ከነዳጅ ማደያ ሰው ቢቀዳም የሚከፍለው የጥቁር ገበያ ዋጋ ወይም ከዛ የበለጠ ገንዘብ ነው። በዚህ ዙርያ ከመንግስት አካላት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያረግነው ሙከራ 'ስብሰባ ላይ ናቸው' በሚል ምክንያት ሊሳካ አልቻለም።
-መሠረት ሚድያ-





