ከስራ መባረርን በመስጋት ከራሳቸው ኪስ እየከፈሉ አዲስ ቡክ የሚያስከፍቱ የባንክ ሰራተኞች ምሬታቸውን ገለፁ
(መሠረት ሚድያ)- አሁን አሁን አሳሳቢ እየሆነ፣ ብዙ ሰዎች ያላስተዋሉት እንዲሁም የሚዲያ ሽፋን ያልተሰጠው ነገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣው የባንክ ሰራተኞች በደል ነው።
የባንክ ሰራተኞች ከሚደርስባቸው በደሎች መሀል የባንኮች አመራሮች የስራ ጫና፣ አዲስ አካውንት የማስከፈት ግዴታ እንዲሁም ከፍ ሲል ስድብ እንደሆነ ሚድያችን ሲያሰባስብ የቆየው መረጃ ያሳያል።
በግዳጅ አዲስ ቡክ አስከፍቱ የሚባሉ የባንክ ሰራተኞች ከስራ መባረርን በመስጋት ከራሳቸው ኪስ እያወጡ አካውንት እንደሚከፍቱ ለሚድያችን ጠቁመዋል።
"በአንዳንድ አመራሮች የሚደርስብን ያልተገባ ንግግር እና የስራ ጫና እንዲሁም በአዲስ አካውንት ማስከፈት ዙርያ የተሰጠን አመታዊ ፕላን እጅግ እየፈተንን ነው፣ ተምረን እንዳልተማረ በየመንገዱ ፀሀይ እና ዝናብ እየተፈራረቀብን ነው" በማለት በአብዛኛው በግል ባንኮች የሚሰሩ እነዚህ ሰራተኞች ያስረዳሉ።
"መርቻንት አክቲቬሽን በሚባል የስራ ሁኔታ ከደሞዛችን በትንሹ እስከ አምስት ሺህ የሚሆነውን እዛው ወጪ እያረግን እንገኛለን" የሚሉት ሰራተኞቹ ለአዲስ አካውንት መነሻ ብር 50 መሆኑን በመጥቀስ አንድ ቅርንጫፍ በቀን በትንሹ አስር አካውንት እንዲከፈት ይገደዳል፣ ይህም በትንሹ 500 ብር መሆኑን ይናገራሉ።
"አሁን ላይ ባለው የአካውንት ክፈቱ ጥያቄ የተማረረው ማህበረሰብ አካውንት ቢከፍት እንኳን መነሻውን ብር ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም፣ ስለዚህ እኛ ሰራተኞች ስራችንን ከምናጣ ብለን ይህንን ብር ከኪሳችን ለመሙላት እንገደዳለን" በማለት ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
"አንድ ሰራተኛ በትንሹ በቀን 150 ብር ለአዲስ አካውንት ያወጣል። በሌላ በኩል መርቻንት የሚባለው አክቲቭ የሚሆነው በአንድ ወር ውስጥ በትንሹ አንድ መቶ ብር ሲገባ ሲሆን በትንሹ ሶስት ትራንዛክሽን ያስፈልገዋል። አንድ ቅርንጫፍ በትንሹ 150 መርቻንት አለው፣ አክቲቭ መርቻንት እንዲባል 15,000 ብር ያስፈልጋል ማለት ነው። ይህም ማለት ለቅርንጫፍ ሰራተኛ ሲከፋፈል 1,500 በትንሹ ይደርስበታል፣ ይህ ደግሞ ሰራተኛውን በኢኮኖሚ እየጎዳው ነው" በማለት አንድ ሌላ የባንክ ሰራተኛ ጉዳዩን አብራርተዋል።
አቶ ፍቃዱ ኤርሱሞ የተባሉ ለዘርፉ ቅርብ የሆኑ ግለሰብ በቅርቡ ለመሠረት ሚድያ በላኩት ፅሁፍ ጉዳዩ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሱን አስረድተዋል።
"የግል ባንኮች ሰራተኞች ላይ ከዲስትሪክት ጀምሮ በየቀኑ እየተደወለ አንዳንዴም ወደ ቅርንጫፎች እየመጡ ሰራተኞቹ ማድረግ የማይችሉትን ትዕዛዝ በመሥጠት ያን ካላደረጉ ደግሞ ከደሞዛቸው ጀምሮ ብዙ ቅጣቶች እንደሚጠብቃቸው እያስፈራሩ ብቻም ሳይሆን እያደረጉትም ይገኛሉ" የሚል አስተያየት አስፍረዋል።
ከባንክ ሰራተኞች በተጨማሪ ባንኮች ውስጥ በሹፌርነት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች እያንዳንዳቸው በድምሩ 4 ሚልየን ብር የሚሆን የባንክ አካውንት እንዲያስከፍቱ ታዘው እንደሚገኙ በቅርብ ማስነበባችን ይታወሳል።
በዚህ ጉዳይ ስሙ የተነሳው አዋሽ ባንክ እንደሌሎቹ ባንኮች ሁሉ ገንዘብ ለማሰባሰብ ሰራተኞቹን በከተማው ከማሰማራቱ ውጪ ሹፌሮቹም እያንዳንዳቸው 4 ሚልየን ብር deposit አስደርጉ መባላቸው በቅርቡ ተሰምቶ ነበር።
"ሹፌሩ መኪናውን በአግባቡ መንዳት ትቶ ስለ ገንዘብ ማሰባሰብ ሲያስብ እና ሲጨነቅ ነው የሚውለው" ያሉን አንድ የተቋሙ ሰራተኛ ሁሉም ሹፌሮች እስከ ሰኔ አጋማሽ ግባቸውን እንዲመቱ (4 ሚልየን ብር ከህዝቡ deposit እንዲያስደርጉ) መታዘዛቸውን ተናግረዋል።
ደህና ኑሮ ይኖራሉ የሚባሉትን ጨምሮ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት በዚህ ወቅት አንድ ሹፌር በምን መልኩ 4 ሚልዮን ብር የሚያወጣ ቡክ ማስከፈት እንደሚችል ለበርካቶች ጭንቀትን ብቻ ሳይሆን አስደማሚ ሆኗል።
-መሠረት ሚድያ-




